"ተንከራታች ህልሞች" በናትናኤል መኩሪያ
ዓርብ፣ ሐምሌ 4 2017ናትናኤል መኩሪያ «ተንከራታች ህልሞች» የተሰኘ እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመረኮዘ የግል ህይወቱን የሚመለከት መፅሀፍ ፅፏል። ይህንንም መፅሀፉን ባለፈው እሁድ በጀርመኗ ኮሎኝ ከተማ አስመርቋል። ጀርመን ሀገር ነዋሪ የሆነው ናትናኤል ተወልዶ ያደገው ኢትዮጵያ ሲሆን 33 ዓመቱ ነው። ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገራቸው ይሰደዳሉ ፤ የናትናኤል ምክንያት እናቱ ነበሩ። « የመጀመሪያም ልጅ ስለነበርኩኝ። እናቴን ለማገዝ ብዙ ነገሮችን እሞክር ነበር። » የሚለው ናትናኤል ብዙ ወንድም እና እህቶች አሉት። እናም እርዳታውን በቂ ሆኖ አላገኘውም። ስለሆነም «ያለኝ አማራጭ ምን አይነት መንገድ ተጠቅሜ እናቴን ላግዛት እችላለሁ የሚል ነበር» ይላል።
ስደትን እንደ መጨረሻ አማራጭ ያየው ናትናኤል ጀርመን ሀገር እስኪገባ ድረስ የመጀመሪያዎቹን ሶስት ዓመታት በስደት ጉዞ አሳልፏል። ስደትን እንደ አማራጭ በወቅቱ እንዲያይ የገፋፋው« ልጅነት» እና ነገሮች «ቀላል መስለው» ስለታዮት እንደሆነ ይናገራል። ይሁንና ጉዞው እንዴት ፈታኝ እንደነበር ከመፅሀፉ ተቀንጭቦ የተወሰደው ታሪክ ያሳያል።« በስደት በራብ ፤መጠማት እና መድከም እንዳለ ሰምቻለሁ። የማላውቀው ግን ውሻ የሞተበትን የገማ ውኃ መጠጣት እንዳለ ነው። እናቴ ይህን ብታይ ምን ትል ይሆን ብዬ አሰብኩ»
የስደት ፈተናዎች
መራብ፤ መጠማት እና ብቸኝነት የናትናኤል ዋና ፈተናዎች ነበሩ። ከዚህም ሌላ በስደት ጉዞው ላይ የመን ውስጥ በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር። «እኔ መሄድ የፈለኩት አውሮፓ ነው የሄድኩት ግን የመን ነው። ይህንን ረጅም ጉዞ እንድሄድ ምክንያቱ ትክክለኛ መረጃ አለማግኘት ነው። ይዞን የሄደው ልጅ የሆነ ቦታ ላይ ተለያየን። እኔም ጉዞዬን ቀጠልኩ። እዛ ተይዘን እስር ቤት ገባን። ወንጀል ሰርተን አይደለም። ህገ ወጥ ተጓዥ በሚል ነው። ህገ ወጥ ተጓዦች ገንዘብ ከፍለው ይወጣሉ። ይህንን የማይከፍል ደግሞ ተመላሽ ይሆናል። እዛ ብዙ ነገሮች አሳልፌያለሁ። ስለዚህም በጥልቀት መፅሀፉ ላይ ተፅፏል።»
ናትናኤል ይህንን መፅሀፍ ለመፃፍ የገፋፋው የእራሱን ታሪክ እንዲያስታውስ ያደረጉት በርካታ አጋጣሚዎች ናቸው። ወጣቱ ጀርመን ሀገር ከመጣ ፣ ቋንቋ እና የሙያ ትምህርት ከተማረ በኋላ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአንድ የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ ይሰራ ነበር። እዛም ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ አፍሪቃውያን በጉዟቸው የገጠማቸውን ፈተና ሰምቷል። እንደው « ከእኔ የባሰ» ፈተና የምትለው አጋጣሚ ካለ ሲባል ፤« ከየት ልጀምር? በጣም ብዙ አሉ።…. »ይላሉ።
ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች ምን አይነት መልዕክት ማስተላለፍ ይፈልጋል?
ናትናኤል ጀርመን ሀገር ላይ በሁለት እግሩ መቆም ችሏል። ከስደተኛ ጣቢያ ስራው ጎን ለጎን ከኢትዮጵያ ቡና እያስመጣ ጀርመን ሀገር ላይ ይሸጣል። ወደፊት ሙሉ ትኩረቱንም እዚህ ላይ ማድረግ ይፈልጋል። «ስደተን ማስቆም አይቻልም። አትምጡ ማለትም አይቻልም ኑ ማለትም አይቻልም። ያ ሰው ራሱ ነው የሚወስነው። ያለውን ትክክለኛ እውነታ ግን እናገራለሁ። ወጣቱ የሚሰደደው ወዶ አይደለም። አትሰደድ ማለቱ ወጣቱን አይጠቅመውም። ስደት አስከፊ ነው ስንል ደግሞ በአንፃሩ ለወጣቱ ያስፈልገዋል የምንለውን ነገር መስራት መቻል አለብን።»
ትምህርትን እንደ አማራጭ
ለዚህ ደግሞ ናትናኤል አንዱ መፍትሔ ነው የሚለው ትምህርት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የመማር እድል ያላገኙ ወጣቶች እንዲማሩ ትምህርት ቤት እያስገነባ ይገኛል። « ሰሜን ሸዋ ነው። አካባቢውን አላውቀውም ነበር። በጓደኛዬ አማካኝነት ወደእዛ ሄድኩኝ። ሰዎቹ ለትምህርት ያላቸው ፍላጎት የተለየ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ትምህርት ለመማር እንዴት እንደዚህ ይቸገራል፣ ይንገበገባል የሚል ሀሳብ አደረበብኝ» ሲቀጥል ደግሞ ናትናኤል የአባቴ ሀገር ያለው «ሲዳማ» ውስጥ ፕሮጀክቶች ማስቀጠል ይፈልጋል።
"ኢትዮጵያውያን ብዙ እድሎች አምልጧቸዋል"
ጀርመን የስደተኞች ፖሊሲዋን እያጠናከረች ትገኛለች። በተለይ ወደ ጀርመን የሚመጡ ስደተኞችን ከሀገሬው ዜጎች ጋራ ተዋህደው እንዲኖሩ የማድረጉ ሁኔታ ትልቅ ፈተና እንደሆነ ቀጥሏል እና ጀርመንን እንደ ሁለተኛ ቤታቸው ለመረጡ የውጭ ሀገር ዜጎች፤ ከስደተኛ ኢትዮጵያውያን ናትናኤል ምን እንደሚጠበቅ ሲናገር «ኢትዮጵያውያን ብዙ እድሎች አምልጧቸዋል» ይላል። «እያንዳንዷን ደቂቃ እና ቀን መጠቀም የእኛ ኃላፊነት ነው። አብዛኛው ስደተኛ ኢትዮጵያዊ የመንግሥት ጥገኛ ነው። ጀርመን በብዙ ሺ የሚቆጠር ስደተኛ ነው የሚፈልስባት እና ከዚህ አንፃር ብዙ ነገሮች ለውጥ አሳይተዋል። ብዙ ነገሮች ከባድ ሆነዋል ። እዚህ ያሉ ሰዎች ያለውን ጭላንጭል እድል ሊጠቀሙበት ይገባል። »
ናትናኤል ባለፈው እሁድ «ተንከራታች ህልሞች» የተባለው መፅሀፉን ሲያስመርቅ የዶይቸ ቬለ ጋዜጠኛ ነጋሽ መሀመድ በዝግጅቱ ላይ ተካፍሎ ነበር። የናትናኤልንም መፅሀፍ አንብቧል። ከስነ ጹሁፍ አኳያ እና ከቃላት አጠቃቀም አኳያ እንዴት ይገመግመዋል?
«የናትናኤል መፅሀፍ ሁለት አይነት የስደት መንገዶችን ያሳያል።» የሚለው ነጋሽ «አፃጻፉ በጣም ጥሩ ነው። ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገው በየምዕራፎቹ በሁለት መንገድ ፅፎታል። አንደኛው አሁን ባለታሪኩ መግለፅ የሚፈልገውን ነገር የሚተርክነት ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ በምልሰት በልጅነቱ ያሰበውን ያሰበውን የሚተርክበት ነው። እና ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላኛው ሲያልፍ አይሰለችም። የቋንቋ አጠቃቀሙ አልፎ አልፎ የእሱ ትውልድ የሚጠቀምባቸው የአዲስ አበባ ቃላት አሉ። እኔ እየወደድኳቸው ነው ያነበብኳቸው። » ይላል።
ልደት አበበ
እሸቴ በቀለ