በደቡብ ወሎ የተፈናቃዮች መጠለያ የህክምና አገልግሎት ማጣት
ረቡዕ፣ ሰኔ 4 2017
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በሐይቅ ጃሪ የስደተኞች ጣቢያ የሚገኙ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ባለፉት ስድስት ቀናት ምንም አይነት ህክምና ባለማገኘታቸዉ ህሙማን በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸዉ ተነገረ። ባለፉት አምስት ዓመታት በዮኒሴፍ አማካኝነት በመጠለያ አገልግሎት ይሰጥ የነበረዉ ክሊኒክም በበጀት እጥረት ምክንያት ሥራዉን አቋርጦል።
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮቹ በእርዳታ ላይ የተመሰረተ ኑሮ ስላላቸዉ በራሳቸዉ አቅም መታከምም ሆነ መድኃኒት መግዛት አንችልም ብለዋል። በመጠለያው ዉስጥ የሚገኙ ሕጻናት የሳምባ ምች በሽታ በተደጋጋሚ የሚጠቁ ሲሆን ወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችም የተፈናቃዮቹ ችግሮች ናቸው። በተመሳሳይም በመካነ ኢየሱስና ጃራ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያም ችግሩ አለ ተብሎል።
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በሀይቅ ጃሪ የስደተኞች ጣቢያ የሚገኙ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ባለፉት ስድስት ቀናት ምንም አይነት ህክምና ባለማገኘታቸዉ ህሙማን በከፍተኛ ችግር ዉስጥ መሆናቸዉ ተነገረ።
ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በአማራ ክልል ተሁለደሬ ወረዳ እና ሐይቅ ከተማ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ባለፉት አምስት ዓመታት በረድኤት ደርጅቶች እና በመንግሥት ድጋፍ ሲያገኙት የነበረው የህክምና አገልግሎት መስተጓጎል እንደገጠመው ገለፁ። የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮቹ በመጠለያ ጣቢያዎች የተሟላ መሰረተ ልማት አለመኖር የምግብ እጥረት እና የመጠለያ ጣቢያዎቹ የተመሰረቱበት አካባቢ ከከተማው ውጭ መሆን በቀላሉ በተላላፊ በሽታ እንዲጠቁ ምክንያት መሆኑን ነው የሚናገሩት። በተሁለደሬ ወረዳ የሚገኘው የጃሪ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በባለፉት ሦስት ዓመታት በጣቢያው የህክምና ተቋም ከፍቶ አገልግሎት ሲሰጣቸው የነበረው ዩኒሴፍ በመጠለያ ጣቢያ ይሰጠው የነበረውን ህክምና አገልግሎት በማቋረጡ ምክንያት ህሙማን ህክምና ማግኘት እንዳልቻሉ ይናገራሉ።
የረድኤት ተቋማት የህክምና ሥራ ማቆም
በተመሳሳይም በሐይቅ ከተማ የሚገኙ የመካነ ኢየሱስ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ያሉ የሀገር ውስጥ ስደተኞች ምንም እንኳን ምርመራን በተመለከተ የከተማው ጤና ጣቢያ የነፃ አገልግሎት ቢሰጠንም መድኃኒት ማግኘት ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል።
በመጠለያ ጣቢያዎቹ ያለ የወረርሽኝ ስጋት
በዩኒሴፍ በኩል ይሰጥ የነበረው የህክምና አገልግሎት መቋረጥ ተደጋጋሚ ወረርሽኞች እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች በሚያጠቋቸው መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የህክምና አገልግሎት መቆም የተፈናቃዮችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነው የሚሉት ስማቸው እንዳይጠቀስ እና ድምፃቸው እንዲቀየር የጠየቁ የአንድ የረድኤት ድርጅት ተቋም ሠራተኛ ናቸው።
«‹የሚኖሩበት ቦታ በጣም የተጨናነቀ ነው፤ አንድ ቤት ላይ እስከ 40 ሰው የሚኖር አለ። ሳል ካለ ሁሉም የመያዝ እድላቸው ሰፊ ነው። ሌሎችም በሽታዎች በዚያው ልክ ይተላለፋሉ።››
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮቹ እንዲሰፍሩበት የተደረጉበት ቦታ ከተቋምና ከከተማ የራቀ ነው የሚሉት የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና ምላሽ ቡድን አስተባባሪ አቶ እሸቱ ይማም ዩኒሴፍና የዓለም ጤና ድርጅት በበጀት ምክንያት በመጠለያ ጣቢያዎቹ ይሰጡት የነበረውን ህክምና ማቋረጣቸው ችግር ሆኗል ይላሉ።
የህክምና ባለሙያዎችን መመደብ አለመቻሉ
የረድኤት ተቋማቱ ያቋረጡትን የህክምና ሥራ ለማስቀጠል በጤና ጣቢያ ደረጃ የሰው ሀብት እጥረት በመኖሩ ህክምና መስጠት ባይቻልም ዞኑ ጉዳዩን ለአማራ ክልል ጤና ቢሮ አሳውቆ የሰው ሀይል ለመቅጠር እየተጠባበቀ መሆኑንም አቶ እሸቱ ይማም ተናግረዋል።
በመጠለያ ጣቢያዎቹ ከዚህ ቀደም የኩፍኝ ወረርሽኝ ተከስቶ በመንግሥትና በረድኤት ተቋማት እገዛ መቆጣጠር ቢቻልም አሁን ግን ወባ፣ እንዲሁም በሕጻናት ላይ ደግሞ የሳንባ ምች ህመሞች የመጠለያ ጣቢያዎቹ ነዋሪዎች ፈተና መሆናቸው ተነግሯል።
ታሪኩ ኃይሉ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ