በደቡባዊ ትግራይ የተፈጠረዉ ዉጥረት እንደቀጠለ ነዉ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 20 2017
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር በክልሉ ደቡባዊ ዞን ያደረገዉ ሹም ሽር በዞኑ ዉጥረት ማስከተሉን ነዋሪዎች እና የአስተዳደር አካላት ገለፁ።የፀጥታ ሐይሎች ወደ ማይጨው እና ሌሎች አካባቢዎች መግባታቸው ተናግረዋል።የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ደቡባዊ ዞን ነባር አስተዳዳሪ እንዲሁም የስምረት ፓርቲ አባልን በማንሳት የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባል የሆኑትን አቶ ዝናቡ ገብረመድህን የዞኑ አስተዳደር ተደርገው መሾማቸው ተገልጿል።
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በክልሉ የደቡባዊ ዞን አስተዳደር አካላት ማንሳታቸው ተከትሎ ዳግም በአካባቢው የፀጥታ ስጋት ተከስቶ ይገኛል። ባለፈው ወር የዞኑ አስተዳደር አካላት መውረዳቸው የተቃወሙ የዞኑ ነዋሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ቅሬታቸው ሲያቀርቡ የነበሩ ሲሆን ይሁንና ይህ ተቃውሞ በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ተፈርሞ የወጣ ደብዳቤ እንደሚያመለክተው አቶ ዝናቡ ገብረመድህን የትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተዳዳሪ ሆነው መሾማቸው ያመለክታል። ይህ ተከትሎ ዛሬ በማይጨው ከተማ ተቃውሞ መከሰቱ ነዋሪዎች እና የአስተዳደር አካላት ገልፀዋል። የነባሩ የዞኑ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ፅሕፈት ቤት ምክትል ሐላፊ አቶ ግርማይ ፀጋይ ዛሬ ጠዋት በማይጨው ጎዳናዎች መንገድ መዝጋት፣ ጎማ ማቃጠል የመሳሰሉ የተቃውሞ እንቅስቃሴ መታየታቸው ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ይህ ውሳኔ ለማስፈፀም በርካታ ታጣቂዎች በትግራይ ደቡባዊ ዞን መሰማራታቸው የገለፁት አቶ ግርማይ ፀጋይ፥ በአንዳንድ አካባቢዎች ከሚሊሻዎች ጋር ግጭት ተከስቶ እንደነበረ ጨምረው ገልፀዋል።
ከማይጨው ውጪ በሞኾኒ ያለው ሁኔታ የነገሩን የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሀፍቱ ካሕሳይ በበኩላቸው በተለይ ወጣቶች ወደከፋ አማራጭ እንዳይገቡ ስጋት መኖሩ አብራርተዋል።
በተለይም የህወሓት ክፍፍል ተከትሎ በአቶ ጌታቸው ረዳ ከሚመራው ሐይል ጋር የተሰለፉት የትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተዳደር አካላት፣ የቀድሞ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ከስልጣን የተወገደበት አካሄድ፣ የትግራይ ሐይሎች ለአንድ የህወሓት ክንፍ በማዳላት የወሰዱት አቋም እና እርምጃ እንዲሁም በጀነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ካቢኔ አወቃቀር እና ሌሎች አካሄዶች በማንሳት በግልፅ ሲተቹ ነበር።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ