በዓመት 11ሺህ ያክል ሠዎች “በሕገ ወጥ መልኩ ከሀገር ይወጣሉ” ተባለ
ዓርብ፣ ሰኔ 20 2017በዓመት 11ሺህ ያክል ሠዎች “በሕገ ወጥ መልኩ ከሀገር ይወጣሉ” ተባለ
በየዓመቱ 11ሺህ ህፃናትና ወጣቶች በምዕራብ ጎንደር መተማ በኩል በህገወጥ መንገድ ከሀገር እንደሚወጡ የዞኑ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታውቋል፣ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት የትግራይና የደቡብ ክልል ወጣቶች እንደሆኑም መምሪያው ገልጧል፣ አንድ የፖልቲካል ሳይንስና ዓለማቀፍ ግንኙነት ምሁር “ለስደት ገፊና ሳቢ ምክንያቶች አሉ” ብለዋል፡፡
ከሀገር ለመውጣት እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ለደላላ ይከፈላል ስለመባሉ
የምዕራብ ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ የህፃናት መብትና ደህንነት ማስጠበቅ ቡድን መሪ አቶ አበበ ሲሳይ ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ እንደተናገሩት ከመላ አገሪቱ በህገወጥ መንገድ በመተማ ዮሐንስ በኩል ወደ ሱዳን የሚወጡ ወጣቶችና ህፃናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡ በዓመት እስከ 11 ሺ ወጣቶች በዚህ መስመር እንደሚወጡ የጠቆሙት አቶ አበበ ወጣቶቹ የቤተሰቦቻቸውን ንብረት በመሸጥ ጭምር እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ለደላላ በመክፍል በህገወጥ መልኩ ከሀገር ይወጣሉ ብለዋል፡፡ በዚህ መንገድ ከሀገር ከሚወጡት መካክል ከደቡብክልል በተለይ ከወላይታ ዞንና ከትግራይ ክልል የሚመጡት ከፈተኛውን ቁጥር ይይዛሉ ነው ያሉት፡፡ ከሶማሌ ክልል፣ ከምስራቅ አማራ ዞኖች ከወሎና ከሰሜን ሸዋ፣ ከኦሮሚያ አርሲ ዞን እንዲሁ በርከት ያሉ ሠዎች በመስመሩ ለመውጣት እንደሚመጡ አስረድተዋል፡፡ በሚደረግ ጥንካራ የቅንጅት የመከላከል ሥራ ደግሞ በየዓመቱ ከ3ሺህ እስከ 4ሺህ የሚሆኑትን እሰከቤተሰቦቻቸው የማድረስ ሥራ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ ወደ ውጪ ትሄዳላችሁ በሚል በኤጄንሲ የሚጭበረበሩ ሰዎች ጉዳይ
“በ62 ሀገወጥ የሠዎች አዘዋዋሪዎች ላይ እስከ 25 ዓመት የእስር ቅጣት ተላልፏል” የምዕራብ ጎንደር ዞን
ባለፈው ዓመት በነበረው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት በህገወጦች ላይ ብዙ የተሠራ ሥራ ባይኖርም፣ በ2015 እና በ2017 ዓ ም 62 የሚደርሱ ህገወጥ አዘዋዋሪዎች በፍርድ ቤት ተከሠው ከ17 እስከ 25 ዓመት በሚደርስ የእስር ቅጣት እንደተወሰነባቸው ቡድን መሪው ገልጠዋል፣ ፡፡
ለዶይቼ ቬሌ አስተያየታቸውን የሰጡን የአማራ ክልል ነዋሪዎች ያለውን ወቅታዊ የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት በማድርግ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት በአንዳንድ አካባቢዎች መጨመሩን አመልክተዋል፡፡ በተለይ የህፃናት ጋብቻ በሚያስፈራ ሁኔታ ማደጉን ነው የሚናገሩት፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የህፃናት መብትና ደህንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር አቶ አሻግሬ ዘውዴ ህገወጥ ዝውውረን ጨምሮ የህፃናት ጥቃቶች በአንዳንድ አካባቢዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፣ በተለይ ያለእድሜ ጋብቻ ቀደም ሲል የነበረ ቢሆንም አሁን ከፍ እያለ መምጣቱን ነው የተናገሩት፡፡
“በዚህ በጀት ዓመት እስከ 500 የሚደርሱ ያለ እድሜ ጋብቻዎች መመዝገባቸውን ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡” ብለዋል፡፡
“ለህገወጥ ፍልሰት ገፊና ሳቢ ምክንያቶች አሉ” የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር
ለህገወጥ ዝውውር ሁለት ገፊ ምክንያቶች መኖራቸውን ደግሞ በአማራ ክልል የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የፖልቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙንት መምህር አቶ ሰለሞን እሽቱ ይናገራሉ፡፡በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ግፍ ያየችዉ ስደተኛዋ ደራሲ
ለስደት ገፊ ምክንያቶች የሚባሉት፣ የሠላም መደፍረስ፣ አለመረጋጋት፣ የኢኮኖሚ ችሮችና የመተጋገዝ እሴቶች መዳከም መሆናቸውን ያስረዱት አቶ ሰለሞን ሳቢ ምክንያት ናቸው ያሏቸው ደግሞ በሌሎች አገሮች የተሻለ ገቢና ኑሮ አለ ብሎ ማሰብ፣ ከአገር ውስጥ የሌሉ ምቹ ሁኔታዎች አሉ ብሎ ማሰብና ሌሎችንም ምክንያቶች ጠቅሰዋል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የህፃናት መብትና ደህንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር አቶ አሻግሬ እንደገለፁት እየታዩ ያሉ የህፃናት መብት ጥሰቶችን፣ ህገወጥ ዝውውርንና ሌሎችንም ጥቃቶች ለመከላከል ከሚመለከታችው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር