በኮሮና ሰብብ ጀርመን ድንበሯን እንደማትዘጋ ተገለፀ
ረቡዕ፣ መጋቢት 2 2012የጀርመን መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የኮሮና ተሐዋሲን ሥርጭት ለመቀነስ የጀርመን ድንበሮችን መዝጋት መፍትሄ አይሆንም አሉ። ሜርክል ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ ከዚያ ይልቅ የተሐዋሲው ሥርጭት ከተስፋፋባቸው ሃገራት የሚመጡ ሰዎች ቤታቸው እንዲቆዩ ማድረጉ ይመረጣል ብለዋል። ለተሐዋሲው ሥርጭት የሚያጋልጡ ሌሎች ኹኔታዎችን መግታትም ሊተኮርበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
«በእኛ እምነት ኮሮና ያመጣቸውን ተግዳሮቶች ለመከላከል ድንበር መዝጋት ተገቢ እርምጃ አይደለም። ሆኖም ኮሮና በአደገኛ ሁኔታ ከተስፋፋባቸው ሃገራት የሚመጡ ሰዎች ከ955 በላይ ሰዎች በሚሰባሰቡበት ስፍራ እናዳይገኙ ፣ ወይም ቤታቸው እንዲቆዩ ማድረግ ወይም ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ ጠቃሚ ነው።»
ሜርክል ኦስትሪያ ከኢጣልያ የሚመጡ ጎብኝዎች ሃገርዋ እንዳይገቡ መከልከልዋን ተቃውመዋል። እስካሁን ክትባትም ሆነ መድኃኒት ባልተገኘለት በኮሮና ተሐዋሲ በጀርመን ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚደርስ ህዝብ ሊያዝ እንደሚችልም የመስኩ ባለሞያዎች መናገራቸውን ሜርክል ገልጸዋል። በጀርመን እስካሁን 1300 የሚሆኑ ሰዎች በተሐዋሲው ተይዘዋል። የሞቱት ደግሞ 3 ናቸው። ሜርክል ዛሬ በርሊን ውስጥ እንዳሉት አሁን ትኩረቱ የተሐዋሲውን ሥርጭት በመቀነስ ላይ ሊሆን ይገባል። ኢጣልያ ከአውሮጳ ተሐዋሲው በተገኘባቸው ሰዎች ብዛት የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በኢጣልያ ከ10ሺህ በላይ ሰዎች ኮሮና ተገኝቶባቸዋል፤ ኮሮና 631 ሰዎችንም ገድሏል በኢጣልያ። በጀርመን ተነባቢው ቢልድ ጋዜጣ ሜርክል ስለ ኮሮና ምንም አልተናገሩም አላደረጉምም ሲል ከወቀሳቸው በኋላ በሰጡት በዚሁ መግለጫ የአውሮጳ መሪዎች ኮሮናን ለመከላከል ጥሩ እና ውጤታማ ርምጃዎች የትኛዎቹ እንደሚሆኑ መነጋገራቸው አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል። እስካሁን ኮሮና በ113 አገራት ተገኝቷል። በዓለማችን በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 120 ሺህ እየተጠጋ ነው። የሞቱት ቁጥር ደግሞ 3158 ደርሷል።
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ