በኢትዮጵያ እየደበዘዘ ነው የተባለው የሚዲያ ሚና እና ሙያዊነት
ቅዳሜ፣ መጋቢት 3 2014በኢትዮጵያ ለአመታት ፈተና ውስጥ ያለፈው የመገናኛ ብዙሃን ሚና እና የጋዜጠኝነት ሙያ አሁንም ላይ ከህዝብ ይልቅ ቡድኖችን ማዕከል ማድረጋቸው ለሙያው ዕድገት መቀጨጭ አይነተኛ ሚና እተጫወተ ነው የሚሉ አሉ፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የሚዲያ ባለሙያዎች ዘርፉ ለአገር እድገትና ግንባታ የሚጫወተውን ሚና ከፍ ለማድረግ የሙያውን ነጻነት መጠበቅና በመርህ መምራት ይገባልም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ከሶስት ዓመታት በፊት በ2010 ዓ.ም መንግስታዊ ለውጥና ሪፎርም ሲካሄድባት በውል እምርታን ካሳዩ ዘርፎች የሚዲያ ኢንደስትሪ በጉልህ ተጠቃሽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አንድም ጋዜጠኛ ያላሰረችና የመገናኛ ብዙሃን ሙያዊነትና ነጻነት ጉልህ ተስፋን ማሳየቱም የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በመዲናዋ አዲስ አበባ እንዲዘጋጅም አበቃት፡፡ ይሁንና «ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያዩ ጎራዎችን የያዘ የሚመስለው አሁናዊ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ጠባይ የሚዲያ እና ጋዜጠኝነትን ዓለማ የሚጻረሩ ነው» ይላሉ ባለሙያዎች፡፡ ጋዜጠኛ ታምሩ ጽጌ በኢትዮጵያ ለዓመታት በዘርፉ ተሰማርቶ ያገለገለና አሁንም በሙያው ያለ ነው፡፡
በጂማ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶ/ር ደመላሽ መንግስቱ በበኩላቸው የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከመተቸትና ማሞካሸትም በላይ ነው ይላሉ፡፡ ያለሙያቸው በዘርፉ የተሰማሩ መብዛታቸውን እንደ ስጋት የሚያነሳው ጋዜጠኛ ታምሩ ጽጌ በማስተማር፣ በማዝናናትና ህብረተሰብን በማንቃት ጉልህ ሚናን የሚጫወተው ሙያው በዚህ ከቀጠለ አደገኛነቱንም ያነሳል፡፡ ዶ/ር ደመላሽ መንግስቱም ሃሳቡን ይጋራሉ፡፡
ስዩም ጌቱ
ልደት አበበ