በኢትዮጵያ አሳሳቢው የተፈናቃዮች ይዞታ ፣ተስፋና መፍትሄው
እሑድ፣ ሰኔ 8 2017ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው ተፈናቅለው በየስፍራው የተጠለሉ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በተመድ የሰብዓዊ እርዳታዎች ማስተባበሪያ ቢሮ በምህጻሩ OCHA የቅርብ ጊዜ መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ በጦርነትና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ከመካከላቸው አብዛኛዎቹ በጊዜያዊ መጠለያዎችና በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኝ ኅብረተሰብ ጋር ተጠግተው የሚኖሩ ናቸው ሲልም ገልጿል። ይህም እንደ ኦቻ በሀገሪቱ ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል። የኖርዌይ የስደተኞች ካውንስል የተባለው ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት፣ በዓለም ላይ የተዘነጋ የመፈናቀል ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ ካላቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን ሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።
በግጭቶችም ይሁን በሌሎች ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ከመኖሪያቸው ከተፈናቀሉ ሰዎች መካከል በተጠለሉባቸው ስፍራዎች መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው እንዳልተሟሉላቸው ከዚያም ብሶ የምግብ አርዳታ እንደተቋረጠባቸው የህክምና አገልግሎትም እንደማያገኙ በምሬት የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው። በኢትዮጵያ አሳሳቢው የተፈናቃዮች ይዞታ ተስፋና መፍትሄው የዚህ ሳምንት እንወያይ የመነጋገሪያ ርዕስ ነው።
በዚህ ርዕስ የሚወያዩት በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተፈናቃዮችና የስደተኞች ጉዳይ ክፍል ሃላፊ ወይዘሪት እንጉዳይ መስቀሌ ፣ የሰሜን ወሎ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለሙ ይመር አቶ ተስፋለም በርሄ ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች የተባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሃላፊ እንዲሁም ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ የዶቼቬለ የመቀሌ ዘጋቢ ናቸው። በተፈናቃዮች ይዞታ ላይ የፊደራል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የተለያዩ ሃላፊዎችን ለመሳተፍ ብዙ ሙከራና ጥረት ብናደርግም አልተሳካልንም።
ኂሩት መለሰ