በአዲስ አበባ የጎርፍ አደጋ፣ ስጋት እና ጥንቃቄው
ዓርብ፣ ሐምሌ 18 2017
ባለፈዉ ሮብ አዲስ አበባ ውስጥ መስቀል አደባባይ እና ግዮን ሆቴል አካባቢን ያጥለቀለቀዉ ጎርፍ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ጎርፉ ባካባቢዉ የነበሩ በርካታ መኪኖችን አጥለቅልቋል፤ የዉኃ መዉረጃ ቱቦዎች፣ በግንባታ ላይ የነበሩ ቦዮችንና የቤት ቁሳቁሶችንም አበላሽቷል።የጉዳቱ ትክክለኛ መጠን ግን እስካሁን በዉል አልተነገረም።በአደጋዉ ምክንያት «የኮሪደር ልማት« እና «የወንዝ ዳር ልማት» የተሰኙ ግንባታዎች የሚከናወንባት አዲስ አበባ ለክረምቱ የተደረገላት ጥንቅቃቄ መኖር-አለመኖሩ እያነጋገረ ነዉ።
ከትናንት በስቲያ መሃል አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ዙሪያ ያለው ወንዝ ተፈጥሮዋዊ ማፋሰሻውን ለቆ በመውጣት በርካታ ነብረቶች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ በትናንትናው እለት እና ዛሬ በአከባቢው ላይ ቅኝት ባደረግንበት ወቅትም በተለይም በስፍራው ካገኘናቸው በወንዝ ዳር የልማት ፕሮጀክት ስራ ላይ ከተሰማሩት የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እንደተረዳነው አደጋው የተከሰተው የከተማዋ ላይኛው አከባቢ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የመጣ ደራሽ ጎርፍ የዉሃ መውረጃ ቦይ ግምብ ደርምሶ ወደ ውጪ በመውጣቱ አደጋ አስከትሏል፡፡
የጎርፍ አደጋው በዙሪያው ቆመው የነበሩ በርካታ ተሽከርካሪዎችን ላይ ጉዳት ማድረሱንና አንዳዶቹ ደግሞ ከጥቅም ውጪ ማድረጉንም የአይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ “እኔ በዚሁ ነበርኩኝ በአይነ አይቻለሁ፡፡ እንደው ፈጣሪ በስራው ቀላሉን አደረገልን እንጂ ውሃው ፈጥኖ ባያልፍ ከዚህም የከፋ አደጋ ነበር የሚስከትለው” በማለት በዋናነት በላይኛው የከተማዋ ክፍል የጣለው ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ ለአደጋው አብይ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሌላም አስተያየት ሰጪና የጎርፉ ተጎጂ ባካፈሉን አስተያየታቸው፤ “የኔም መኪና ሰለባ ነበር፡፡ እስከ ወገቡ ውሃ ሞልቶበት ነበርና ዛሬ ነው ተጎትቶ የወጣው፡፡ እስጥፋኖስ ፊት ለፊት ባለው ነዳጅ ማደያ ስር የመኪና ማጠቢያ አለና በዚያም ውሃ ሞልቶበት ሰነዶችም በውሃው መውደማቸውን ተገንዝበያለሁ” ብለዋል፡፡
አስተያየት ሰጪው የአይን እማኝ በከትናንት በስቲያ ጎርፍ የጠፋ የሰው ህይወት መኖር አለመኖሩን ባያረጋግጡም ሰዎች ከተሸከርካሪዎች ውስጥ እየተጎተቱ ስወጡ መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ “መኪናቸው በውሃ መልቶ ከመኪናቸው ውስጥ የነበሩ እየተጎተቱ ወጥተው በአምቡላንስ የተወሰዱ አሉ” ሲሉም የተመለከቱትን አጋርተዋል፡፡
በጎርፍ አደጋው ብያንስ ከ10 በላይ ተሽከርካሪዎች በጎርፉ በመዋጣቸው አደጋን ስለማስተናገዳቸውም በመግለጽ በርካታ በወንዙ ዙሪያ ያሉ ቤቶች ውስጥ በተለይም በወለሎቹ የነበሩ ንብረቶች ስለመውደማቸውም አስረድተዋል፡፡ ዛሬ ከጎርፍ አደጋው ስፍራ ተጎትቶ የወጣውን ተሸከርካሪያቸውን መስቀል አደባባይ አጠገብ ስያጸዱ አግኝተን ያነጋገርናቸው ባለንብረት የደረሰባቸው ያልታሰበ ኪሳራ እና ወጪ ቀላል ባይሆንም ለዚህ ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም ይላሉ፡፡ “ይሄው ማን ዞር ብሎ ያይሃል፤ ኢንሹራንሱም አልሸፍን አለ፡፡ ለብቻው የውሃ አደጋ ኢንሹራንስ መግባት ነበረባችሁ አለን፡፡ ሾፌሩ በእንዝላልነት ያመጣውም አደጋ አይደለም፡፡ እሱ አቁሞ ስራ በሚሰራበት ቦታ ነው እንዲህ ያለ አደጋ የደረሰው” በማለት ግንባታውን የሚከናውን አካል መኪና ከደለሉ ውስጥ የማውጣት ስራ ብቻ ነው የሰራ ብለው ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች እና የጎርፍ አደጋው የአይን እማኞቹ በክረም ወቅት መሰል የጎርፍ ስጋቶች ሰፊ በመሆናቸው የተለየ ጥንቃቄ መውሰድ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ “በክረምት ወቀት ጎርፍ ይመጣል ብለን መጠንቀቅ አለብን” የሚሉት አስተያየት ሰጪ በርካታ ወንዞች ባላት መዲናዋ አዲስ አበባ እንኳ ከፍተኛ የጎርፍ ስጋት መኖሩንም አስረድተዋል፡፡
ዶይቼ ቬለ በከተማዋ በክረምት ወቅት በተለይም እየተሰሩ ካሉት የግንባታ ስራዎች አኳያ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመቀነስ እየተሰሩ ያሉት ስራዎች ብሎም እስካሁን የደረሱ አደጋዎች ላይ ከከተማ አስተዳደሩ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ፣ የእሳትና አደጋ ኮሚሽን እንዲሁም ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ለዛሬ አልተሳካም፡፡
ሆኖም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትናንት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ “ረቡዕ ሃምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም. መዲናዋ ውስጥ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ጊዮን ሆቴል አካባቢ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ የወንዝ ዳርቻ ልማት ግንባታውን በመሙላቱና የተሰራለትን ጊዜናዊ ግድብ ጥሶ በመውጣቱ የተፈጠረ አደጋ ሆኖ ሳለ ከአውዱ ውጪ ትርጉም እየተሰጠው ነው” ሲል በማህበራዊ ሚዲያ የተንሸራሸሩ ሃሳቦችን ኮንኗል፡፡
አዲስ አበባ አሁንም በበርካታ ግንባታዎች ላይ መሆኗን የገለጸው የከተማ አስተዳደሩ መግለጫ፤ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ህብረተሰቡ ምንጩ ካልታወቀ “የተዛበ” መረጃ እራሱን እንዲጠብቅ እና ከተማ አስተዳደሩ በሚያደርገው የጎርፍ መከላከል ሥራ ተባባሪ እንዲሆን ብጠይቅም በጎርፍ አደጋው ስለደረሱ ጉዳቶች ግን ምንም የለው ነገር የለም፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ