በአማራ ክልል ያለው ጦርነት በኤች አይ ቪ ህክምና አሰጣጥ ላይ ጫና መፍጠሩ
ዓርብ፣ መጋቢት 19 2017
የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ለበሽታው ስርጭት አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል
በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት የእንቅስቃሴ ገደቦች መኖር፣ በርካታ ትምህርት ቤቶች መዘጋትና የሥራ አማራጮች አለመኖር ለበሽታው ስርጭት አመቺ ሁኔታን ሊፈጥር እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የወጣቱ መዘናጋትና ቸልተኝንት፣ ተዘዋውሮ የግንዛንቤ ትምህርት ለመስጠት ያለው ተነሳሸንት መቀነስና የሁኔታዎች አስቸጋሪነትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተደማምረው የበሽታውን የመከላከል ሥራ አዳጋች እንዳደረገው ነው የሚገልፁት፡፡በአማራ ክልል የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት መባባስ
በዚህ ዙሪያ አስተያየታቸውን ከሰጡን ወጣቶች መካከል ብርሀነመስቀል ሲሳይ በደሴ ከተማ የአዲስ ተስፋ በደማቸው ኤች አይ ቪ ያለባቸው ወጣቶች ማህበር ሰብሳቢ አንዱ ነው፡፡
“... ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እኛ ክልል ያሉ ግጭቶች በተለይ የፀረ የኤች አይ ቪ መድኃኒት በሚወስዱ ወገኖች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፣ በተለይ ወጣቱን ስንመለከተው የመዘናጋት ሁኔታ አለ፣ ሴቶች ወደ ሴተኛ አዳሪነት፣ ወንዶች የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት የማቋረጥ ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡” ብሏል፡፡በአማራ ክልል የመድሃኒት እና የህክምና ግብአት አቅርቦት መስተጓጎል
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የቲቢ፣ የስጋደዌና ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር አቶ ገብሬ ንጉሤ ደግሞ የመከላከሉን ሥራ አስቸጋሪ ያደረጉ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ ይላሉ፡፡
የእንቅስቃሴ ገደብ ለበሽታው ስርጭት ሌላው ምክንያት ነው
እንደ ዳይሬክተሩ ወደ ህብረተሰቡ ተንቀሳቅሶ ግንዛቤን ማሳደግ አለመቻል፣ አለማንቃት፣ የሚጠቀሱ ምክንያቶች ሲሆኑ ይህም ከከልሉ ወቅታዊ የፀትታ ችግር ጋር ተያይዞ የእንቅስቃሴ ገደብ የፈጠረው ችግር መሆኑን አቶ ገብሬ ያስረዳሉ፡፡ ተኩስ ሲኖር መንገዶች እንደሚዘጉ የሚጠቅሱት ዳይሬክተሩ፣ በዚህም ሰበብ መፈናቀሎች እንደሚኖሩና እነኚህም ለኤች አይ ቪ መስፋፋት መንገድ ከፋች ናቸው ብለዋል፡፡የአማራ ክልል ግጭትና የወባ በሽታ ስርጭት
“... አሁን ባለው ሁኔታ ለኤች አይ ቪ የሚያጋልጡ ብዙ ምቹ ሁኔታዎች አሉ፣ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ትምህርት ላይ አይደሉም፣ ቀደም ሲል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁትም ብዙዎቹ ሥራ ፈላጊዎች ናቸው፣ ከበኦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሥራ የሚሰሩ ሠዎች በተላያዩ አካባቢዎች ሲኖሩ እነኚህ ሁሉ ለኤች አይ ቪ አጋላጭ ነው” ሲሉ ተናግርዋል፡፡
በደንበጫ ከተማ መኖር ተስፋ በደማቸው የኤች አይ ቪ ኤድስ ያለባቸው ወገኖች ማህበር ሰብሳቢ አቶ በልስቲ ተገኝ በበኩላቸው አሁን ያለው የፀጥታ ሁኔታ ተንቀሳቅሶ የግንዛቤ ሥራ ለመስራት አስቸጋሪ ቢሆንም ፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት መውሰድ ያቋረጡ ሠዎች መድኃኒቱን እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡”
የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት የሚያቋርጡ ሠዎች ቁጥር ጨምሯል
በምዕራብ ጎጃም ዞን የደንበጫ ወረዳ አንድ የህክምና ባለሙያ የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት የሚወስዱ ሠዎች ቁጥር በተለያዩ ምክንያቶች እየቀነሰ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት የሚያቋርጡ ሠዎች እንዳሉ የሚናገሩት እኚህ አስተያየት ሰጪ በወረዳቸው 900 ያክል የኤች አይ ቪ /ኤድስ ያለባቸውና መድኃኒት የሚወስዱ ሠዎች ቢኖሩም 80 ያክሉ መድኃኒት መውሰድ ያቋረጡ እንደሆኑ አስረድተዋል፣ ምክንያቱ ደግሞ ራሳቸውን ደብቀው ቀደም ሲል ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው ከተማ መድኃኒት ይወስዱ የነበሩ ሠዎች አሁን ባለው የፀጥታ ችግር ያን ማድረግ ባለምቻልላቸው ነው ሲሉ ገልጠዋል፡፡
“የበሽታው ስርጭት እንዳይጨምር የሚቻለው ሁሉ ይደረጋል” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የቲቢ፣ የስጋደዌና ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር አቶ ገብሬ ንጉሤ በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ መድኃኒት ከማዕከል ለማምጣት፣ ከባህር ዳር ወደ ወረዳዎች ለማድረስ ፈተና መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በአጠቃላይ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ወቅታዊ ሁኔታው ጫና የፈጠረ ቢሆንም በሚቻለው መንገድ ሁሉ በሽተኞችን ለመድረስና በሽታው ስርጭቱን እንዳያሰፋ እየተሰራ እንደሆነ ገልጠዋል፡፡
በአማራ ክልል 173ሺህ 442 ሠዎች በደማቸው ኤች አይ ቪ በደማቸው ያለ ሲሆን 158ሺህ ያክሉ የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት የሚወስዱ ናቸው ብለዋል፡፡ 3ሺ 530 የሚሆኑት በመንገድ መዘጋጋትና በመድኃኒት መዘግየት ህክማና አቋርጠው የነበረ ቢሆንም በተደረገ የጋራ ርብርብ ህክማናወን እንደገና ማስጀመር እንደተቻለ አቶ ገብሬ አስርድተዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ