በአማራ ክልል ከ100 በላይ ሠዎች በወባናበ ኮሌራ በሽታዎችw ህይወታቸው አልፏል
ማክሰኞ፣ ግንቦት 19 2017
በአማራ ክልል ባለፈው አንድ ዓመት በኮሌራና በወባ በሽታዎች ከ100 በላይ የሠዎች ህይወት ማለፉን የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ተቋም አስታወቀ፣ የኮሌራ በሽታ ስርጭትን መቀነስ ቢቻልም የወባ ስርጭት ግን የክረምቱን መግባት ተከትሎ እየጨመረ መሆኑን ተቋሙ አመልክቷል፡፡
በአማራ ክልል ባለፍው በጀት ዓመት የኮሌራና የወባ በሽታዎች በተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ የኮሌራ በሽታ እየተወሰደ ባለው ክትትል እየቀነስ እንደሆነና የወባ በሽታ በአንፃሩ እየጨመረ እንደሆነ በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የአንዳሳ ቀበሌ ነዋሪ ይናገራሉ፡፡
ነዋሪው እንዳሉት አንዳሳ የፀበል ቦታ በጊዜያዊነት አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ከተደረገ በኋላ የኮሌራ ታማሚ በአሁኑ ሰዓት እንደሌለ አመልክተዋል፣ አካባቢው ወባማ በመሆኑ ደግሞ የወባ ታማሚዎች ቁጥር በአንፃሩ መጨመሩን ገልጠዋል፡፡
“የወባ ስርጭት እየጨመረ ነው” ነዋሪዎችና የጤና ኃላፊዎች
በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሳህላ ሰየምት ነዋሪ ወ/ሮ ሙሉ ሞገስ በበኩልቸው የወባ በሽታበአካባቢው መጨመሩን ተናግረዋል፣ የዝናብ መቆራረጥና ሙቀት መጨመር ለወባ ስረጭት መነሻ ሆኗል ብለዋል፡፡
በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሳህላ ሰየምት ወረዳ ጤና ጽ/ቤት የወባ መከላከል ባለሙያ ወ/ሮ ፍቅርተ አሰፋ በወረዳው 13ቱም ቀበሌዎች የወባ በሽታ መከሰቱን ተናግረዋል፣ ስርጭቱ ከሳምንት ሳምንት ጭማሪ እያሳየ መሆኑንም ገልጠዋል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ይስማው ለዶይቼ ቬሌ እንደገለፁት ደግሞ ብሔረሰብ አስተዳደሩ ከሚገኙ 16 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች መካከል ቻግኒ ከተማ አስተዳደር፣ ዚገም፣ አዮ፣ ጓንጓና ጃዊ ወረዳዎች ወባማ ናቸው፡፡ እነኚህ ወረዳዎች አጠቃላይ የብሔረሰብ አስተዳደሩን 82 ከመቶ የወባ ሽፋን የሚይዙ ሲሆን አሁንም ስርጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን አቶ አየለ አስረድተዋል፡፡
የኮሌራ ስርጭትን በተመለከተ አሁን በብሔረሰብ አስተዳደሩ አዲስ ታማሚ እንደሌለም የገለፁት፣ ኃላፊው፣ በሚቀጥሉት 45 ቀናት አዲስ የኮሌራ በሽተኛ ካልተመዘገበ ብሔረሰብ አስተዳደሩ ከበሽታው ነፃ መሆኑ በይፋ እንደሚገለፅ ገልጠዋል፡፡
2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሠዎች በወባና በኮሌራ ታምመው ህክምና ስለማግኘታቸው
የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በበኩላቸው በክልሉ ተከስቶ የነበረውን ኮሌራ ወደ “ዜሮ” ማውረድ እንዳልተቻለ ጠቁመው፣ ከታህሳሰ 2017 ዓም ጀምሮ እስካሁን 2ሺህ 316 ሠዎች በበሽታው ተይዘው ህክምና አግኝተዋል ብለዋል፡፡ 15 ሠዎች ደግሞ በበሽታው ህይወታቸው ማለፉን አመልክተዋል፣ በሽታውን የመከላከል ሥራው በተቀናጀ ሁኔታ እንደቀጠለም ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የኮሌራ ስርጭቱ በ6 ወረዳዎች እንዳለም አስረድተዋል፡፡
በአማራ ክልል በየሳምንቱ ከ24ሺህ በላይ ሠዎች በወባ ይያዛሉ
የወባ ስርጭትን በተመለከተ ባለፈው ዓመት በክልሉ 1.8 ሚሊዮን የክልሉ ነዋሪዎች በበሽታው ተይዘው ህክምና የወሰዱ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ በላይ 91 ሠዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል ብለዋል፣ አሁን የክረምቱን መግባት ተከትሎ በየሳምንቱ በአማራ ክልል ከ22ሺህ በላይ ሠዎች በወባ በሽታ እንድሚጠቁ ዳይሬክተሩ አመልክተው ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ሲነፃፀር ከፍ ያለ ነውም ብለዋል፡፡
የኮሌራ በሽታን ለመከላከል ወደ ፀበል የሚሄዱ ሠዎች ከሌላ ቦታ በሽታውን ይዘው ወደ ፀበል ቦታ ስለሚመጡ ዋናው ምክንያት እሱ በመሆኑ ለጊዜው የፀበል ቦታዎችን ለማስቆም ቢሞከርም ቁጥጥሩ የላላ በመሆኑ ስርጭቱን ሙሉ በሙሉ ማስቆም እንዳልተቻለ አቶ በላይ ገልጠዋል፡፡ በአማራ ክልል ከ50 በላይ የፀበል ቦታዎች እንዳሉም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ የወባ በሽታን ለመከላከልም ሠፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተው ከሚወሰዱ የመከላከል ሥራዎች መካከል 4 ሚሊዮን የወባ መከላከያአጎበር ማቅረብ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህን ተግባራዊ ለማድረግም ተቋማቸው በግዥ ሂደት ላይ መሆኑን ገልጠዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ