በኖርዌይ የትውልደ ኢትዮጵያዊት ማህበራዊ ሰራተኛ ግድያ
ዓርብ፣ ነሐሴ 23 2017በኖርዌይ የትውልደ ኢትዮጵያዊት ማህበራዊ ሰራተኛ ግድያ
ባለፈው ዕሁድ ሌሊት ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ተሚማ ኒብራስ ጁሃር በአንድ በኖርዌይ ኦስሎ በሚገኝ የታዳጊዎችና ወጣቶች ማዕክል (rihablitation center) በስራ ላይ እንዳለች በቤቱ ከሚኖሩትና ከሚገለገሉት በአንዱ በግፍ መገደሏ ድፍን ኖርዌይን ያስደነገጠና በርካታ ጥያቄዎችን ያስነሳ ኁኗል፡
የ34 አመቷ ወጣት ተሚማ ኒብራስ ጁሀር የተወለደችው ኢትዮጵያ ይሁን እንጂ እድገቷና ትምህርቷ በዚሁ በኖርዌይ ነው። በተለያዩ ምክኒያቶች ከቤተሰብ ጋር ያልተግባቡ ወይም የተነጠሉ ወይም ሌሎች ችግሮች ያሉባቸው ታዳጊዎችና ወጣቶች የስነልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ እያገኙ በሚኖሩበት የወጣቶች ቤት የማህበራዊ ሰራተኛ (ሶሻል ዎርከር) ሆና የምትሰራው ተሚማ፤ የተገደለችው ባለፈው ዕሁድ ሌሊት የማታ ሺፍት ተረኛ በነበረችበት ግዜ ነው። ጋዜጦችና መገናኛ ብዙሀን ታሚማን ስራዋን የምትወድ፤ ቅን፤ ተግባቢና ሩህሩህ የነበረች ስለመሆኗ የስራ ባልደሮበቿንና ወጣቶችን በመጥቀስ በሰፊው ጽፈዋል።
የገዳዩ ማንነትና የወንጀሉ አይነት
ፖሊስ በገዳይነት ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው የ18 አመቱ ወጣት የዚያው ታማኒ የምትሰራበት የወጣቶች መኖሪያ ቤት ኑዋሪ መሆኑ ታውቋል። በሌሊት እቢሮዋ ግብቶ በስለት እንደገደላት ፖሊስ የገለጸ ሲሆን፤ የግድያው ምክኒያት እየተጣራ መሆኑን አስታዉቋል፤። ሆኖም ግን ግድያው ተራ ወንጀል እንዳልሆነና የፖለቲካ ፍላጎት ያለበትና ታስቦ የተፈጸመ ስለመሆኑ ፖሊስ ፍንጭ የሰጠ መሆኑን ጋዜጦችች የፖሊስን መረጃ ዋቢ አድርገው አስታውቀዋል።
የኖርዌይ መንግስትና ህዝብ ግድያውን ማውገዙ
በግድያው መላ የኖርዌይ ህዝብ የደንገጠና ያዘነ ስለመሆኑ መገናኛ ብዙሀን እየገለጹና እያስተጋቡም ነው።፡ የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስተር ሚስተር ዮናስ ሀር ስቶር ግድያውን አውግዘው የተስማቸውን ሀዘን ለሟች ታሚማ ኒብራስ ጁሀር ቤተሰቦችና የስራ ባልደረቦች ገልጸዋል። ምናም አይነት የፖለቲካ አላማ ያለው ግድያ በኖርዌይ ሊኖር አይገባውም በማለት ፖሊስ የወንጀሉን ምክኒያትና ሰበብ መርምሮ የሚያሳውቅ መሆኑንም አሳታወቀዋል።
በተለይ የኢትዮጵያና ኤርትራ ማህበረሰብ አባላት ስብራትና ሀዘን
በኖርዌይ የሚኖሩ የልዩ ልዩ አገሮች ማህብረሰቦችና በተለይም የኢትዮጵያና ኢርትራ ማህበረሰብ አባላት በድርጊቱ በጣም ማዘናቸውና መደንጋጣቸው እየተገለጸ ነው። በኦስሎ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መጋቢ ዳዊት ሳሙኤል ይህንኑ የማህበረሰቡን ስብራትና ሀዘን ለዲደብሊው በስልክ ገልጸዋል።
የኦስሎ የበርካታ አመታት ኑዋሪና በኖርዌይ የስደተኖች ካውንስል የስደተኖች አማካሪ የሆኑት አቶ ሙመድ ብርሀንም የታሚማ ህይወት ህልፈት በተለይ በኢትዮጵያና ኤርትራ ማህበረሰብ አባላት ዘንድ የፈጠረው የሀዘን ስሜት ልዩና ጥልቅ መሆኑን ነው የገለጹት።
የኖርዌይ ጠቅላላ ህዝብ ብዛት ከ6 ሚሊዮን እንደማይበልጥ የሚገለጽ ሲሆን፤ በርክታ የውጭ አገር ሰዎችንም ተቀብላ በማስተናገድ ትታወቃለች። አገሪቱ ሰላማዊ፤ የህግ የበላይነትና እኩልነት የሰፈነባት ስለመሆኗ የሚነገር ቢሆንም፤ አልፎ አልፎ ግንበዘረችነትና ጥላቻ ላይ የተመሰረቱ ግድያዎች እንደሚፈጸሙም ይገለጻል። የትውልደ ኢትዮፕያዊቷ ታሚማ ጁሀር ገዳይ ወንጀሉን የፈጸመበት ምክኒያት ገና በምርመራ ላይ ቢሆንም፤ ግድያው በማህበራዊ ስራዋ ላይ እንዳለች በሌሊት መፈጸመ መሆኑ ግን ወንጀሉን ልዩና በኖርዌይ የዌልፌር ስራት ላይም ያነጣጠረ አድርጎታል ነው የሚባለው። የኖርዌይ መንግስት ከዚህ አሳዛኝ የወንጀል ድርጊት በመማር በተለይ በማህበራዊ ሰራተኖች ደህንነት ላይ ተጨማሪ ስራ ሊሰራና ሰራተኞችም ልዩ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ በሰፊው እተገለጸና እየተጠይቀ መሆኑ ታውቋል።
ገበያው ንጉሴ
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ