በትግራይ ክልል ድህነት፣ ሥራ አጥነትና የወጣቶች ስደት መበራከት
ረቡዕ፣ የካቲት 26 2017በትግራይ ክልል ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው መዳከሙን ተከትሎ ድህነት፣ ሥራ አጥነት እና የወጣቶች ስደት መበራከቱ ተገለፀ። ከጦርነት በኋላ ይጠበቅ የነበረ ዳግመ ግንባታ ይሁን የኢኮኖሚ ማነቃቅያ ሥራዎች በሚጠበቀው ሁኔታ የሉም ሲሉም የኢኮኖሚ ዘርፍ ምሁራን ይገልፃሉ። ከዚህ በተጨማሪ በጦርነቱ ለወደመ ሀብት፣ የባንክ ብድር እና ወለድ ለመክፈል ያልቻሉ በትግራይ ክልል ለሚገኙ ባለሀብቶች መንግስት መፍትኄ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል።
የትግራዩን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶርያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በክልሉ በጦርነት ምክንያት የደረሰውን ውድመት የሚተካ ዳግመ ግንባታ እንዲሁም የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ሥራዎች ይከወናሉ ተብሎ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም፤ እስካሁን ይህ ነው የሚባል ተግባር አልተፈፀመም ሲሉ በትግራይ የሚገኙ የተለያዩ ሲቪክ ማሕበራት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ ይገልፃሉ።
የትግራይ ንግድ ዘርፍ ማሕበራት ምክርቤት በበኩሉ፥ መንግስት የንግድ ማሕበረሰቡ የሚደግፍ የተለየ ፖሊሲ መከተል ሲገባው በጦርነት ለወደመ ሀብት፣ የባንክ ብድር እና ወለድ እንዲከፍል ጫና እየፈጠረ ይገኛል ሲል ቅሬታው ያቀርባል። በዚህም ምክንያት በትግራይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተዳክሟል፣ ስራ አጥነት ሰፍኖል፣ ,ጣቶች በገፍ እየተሰደዱ እንደሚገ ተገልጿል። የትግራይ ፋይናንስ ግብረሐይል የተባለ በክልሉ የፋይናንስ እና ንግድ ዘርፍ ያሉ ችግሮች ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ መፍትሔ እንዲያገኙ የሚሰራ ተቋም ባዘጋጀው መድረክ ወቅታዊ ሁኔታ የሚገመግም ጥናት ያቀረቡት የኢኮኖሚ ምሁሩ ተስፋይ አረጋዊ ከጦርነቱ በኃላም ቢሆን የትግራይ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የሚያግዝ ስራ እየተከወነ አይደለም ይላሉ።
አቶ ተስፋይ አረጋዊ "የንግድ ማሕበረሰቡ ጥያቄ እና አጠቃላይ የትግራይ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቆ ይገኛል። በጦርነት የወደመ ሀብት ለመካስ፣ ኢኮኖሚ ለማነቃቃት እና ለማበረታታት ከመስራት ይልቅ፥ በዓለም ካለው ልምድ በተፃራሪ በጦርነት የወደመ ሀብት የንግድ ማሕበረሰቡ እንዲከፍል፣ ወስዶት የነበረ ብድር ከነቅጣቱ እንዲመልስ ተፈርዶበት ይገኛል። ይህ ኢኮኖሚያዊ ጫና በነጋዴው ላይ ብቻ አይደለም ችግር የፈጠረ፥ በአጠቃላይ በህዝብ እና በክልሉ ላይ ነው ጫና የፈጠረው" ይላሉ።
በትግራይ በተለይም በግል ዘርፉ ኢኮኖሚ የደረሰ ጉዳት የሚዳስስ ጥናት ተሰርቶ ለዓለም ባንክ መቅረቡ ያነሱት ሌላው የኢኮኖሚ ምሁር ዶክተር ሙዑዝ ሓዱሽ በበኩላቸው፥ ይሁንና በትግራይ የቀጠለው ፖለቲካዊ ቀውስ ለትግራይ ዳግመ ግንባታ እና የኢኮኖሚ ማነቃቅያ ስራዎች አቅድ ማስፈፀም ፈተና እንደሆነ ገልፀዋል።
የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዝዳንት በሪሁ ሀፍቱ በበኩላቸው የትግራይ ሁኔታ የሚመጥን የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ከመንግስት ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል። የደረሰው ጥፋት በሁላችን ቤት እና በእያንዳንዳችን ጭንቅላት ላይ አለ። በያዝነው መንገድ ትግራይ ወዴት እያመራች መሆኑ መመልከቱ ቀላል ነው። በየቀኑ ስደት እየከፋ እየሄደ ነው። የትግራይ ህዝብ ኑሮ ምን ያክል እየከፋ መሆኑ እያየነው ነው። በዚህ ከቀጠልን እንደ ህዝብ የምንበተንበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል እያየን ነው" ሲሉ አቶ በሪሁ ጨምረው ገልፀዋል።
በትግራይ የሚገኙ ከባንኮች ብድር ወስደው የነበሩ ባለሀብቶች በጦርነቱ በደረሰ ውድመት እና ኪሳራ ምክንያት፥ ያለባቸው ብድር መመለስ እንደተቸገሩ በመግለፅ የፌደራሉ መንግስት የተለየ መፍትሔ እንዲያበጅ ጥያቄ ማቅረባቸው ተመላክቷል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ