በተስፋ ብቻ የቀረው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ምስራቃዊ ወረዳዎች ፀጥታ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 10 2017በተስፋ ብቻ የቀረው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ምስራቃዊ ወረዳዎች ፀጥታ
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖ ምስራቅ ሸዋን በሚያዋስኑና በአከባቢው በሚገኙ ወረዳዎች በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች የተስተዋለው የፀጥታ ይዞታ አለመስተዋሉን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ከዚህ በፊት በተራዘመው የፀጥታ መቃወስ ውስት እንደነበሩ የሚገልጹት ነዋሪዎቹ አሁን ላይ በክልሉ ማዕከላዊ አከባቢ እየሰፈነ ነው የሚባለው መረጋጋት እንዳልጎበኛቸውና በጫካ መንግስትን የሚወጉ ታጣቂዎች በገፍ አለመመለሳቸውንም አስረድተዋል፡፡ ይህም በግጭቱ መዘዝ የተስፋፋውን የኑሮ መቃወስ ዕድሜ እንዳራዘመባቸው ነው ያመለከቱት፡፡
በደቡብ ምዕራብ ሸዋ በዞኑ ምስራቃዊ አከባቢዎች ላይ በሚገኙ በተለይም በአራት ወረዳዎች ባለፉት ዓመታት በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች መካከል በሚደረግ ፍትጊያ ነዋሪው ህብረተሰብ ክፉኛ መሰቃቱ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ተዘግቧል፡፡ ሰደን ሶዶ፣ ሶዶ ዳጪ፣ ቶሌ እና ቀርሳ ማሊማ ወረዳዎች በሚባሉ በነዚህ ወረዳዎች አሁን ላይ በተለይም በማዕከላዊ የኦሮሚያ አከባቢዎች ታጣቂዎች በስፋት እየገቡ ነው በሚባልበት እስካሁን ወቅት ግድያ እና ንጥቅያው እንዳላባራ ይገልጻሉ፡፡
እልባት ሳያገኝ አሁንም ድረስ ዘልቋል በተባለው አሁናዊ ችግሩ ምክንያት ለደህንነታቸው በመስጋታቸው ስማቸውን እንዳንጠቅስና ድምጻቸውን እንድንቀይር የጠየቁን አስተያየት ሰጪ፤ “እንግዲህ የታጣቂዎች መግባት በአንዳንድ የኦሮሚያ ወረዳዎች በተለይም በዚህ በምዕራብ አከባቢ ይታያል” ያሉት አስተያየት ሰጪው በሰደን ሶዶ፣ ሶዶዳጬ፣ ቶሌ እና ቀርሳ ማሊማ ወረዳዎች ከጢቂት ታጣቂዎች በስተቀር እንደሌላው አከባቢ ታጣቂዎቹ ሰልፍ ይዘው ስገቡ አይስተዋልም ሲሉ የችግሮቹን መቀጠል አስተረድተዋል፡፡ በነዚህ ወረዳዎች የተወሰኑ መሻሻሎች ብኖሩም ሰው በነጻነት ወደ መንቀሳቀሱ የሚያመጣው ለውጥ ግን መሬት ላይ አለመፈጠሩንም አንስተዋል፡፡ “እንደውም በርካታ ሰዎች ተገድለዋል” ያሉት የዓይን እማኙ በተለይም ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ከመንግስት ጋር ትሰራላችሁ በሚል ንጹሃን ዜጎች በሌሊት በሚመጡ ታጣቂዎች ያለርህራሄ ይገደላሉ ነው ያሉት፡፡
አስተያየት ሰጪው እንደሚሉት የአከባቢው ማህበረሰቡ በግጭቱ እጅጉን ተማሯል፡፡ በግጭቱ የተነሳ ኢኮኖሚውም ተዳክሞ በጣሙን ተሰላችቷል፡፡ እናም ታጣቂዎቹን ወደ ሰላም መምጣት በተስፋ ይጠብቃል። “እውነት ለመናገር ህዝቡ ገና ወሬውን በሚዲያ ስሰማ እፎይታ አገኘን ብሎ እርቅ እንዲወርድና ታጣቂዎችም እንዲገቡ ነው መሻቱ፡፡ የሰላም እጦቱ የሰለቸው ህዝብ ምንም አይፈልግም፤ ዴሞክራሲም ይሁን ነጻነት የሚባለው ከህልውና በታች ናቸው በሚል ህዝቡ በህይወት መኖሩን ነው የሚፈልገው” ሲሉ እስካሁን የተናፈቀው የታጣቂዎች እና መንግስት ሰላም ማውረድ እንዳልተሳካ አስረድተዋል፡፡
አስከፊ የፀጥታ ስጋት አለብን ያሉ ሌላም የሶዶ ዳጪ ወረዳ ነዋሪ ስማቸውንም ሆነ ድምጻቸውን በዘገባው እንዳንጠቀም ተማጽነው ከሰሞኑ እንኳ ብርካቶች የተለያየ ምክንያት እየተፈለገ ሰላማዊ ሰዎች በሌሊት እየተወሰዱ መገደላቸውን አንስተዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ የሚሞቱት ፍጹም ሰላማዊ ሰዎች ናቸው፡፡ “ፍጹም ሰላማዊ ሰዎች ናቸው እየሞቱ ያሉት፡፡ ገበሬዎች ናቸው፡፡ምን አያውቁም ፖሊቲካ ውስጥ የሌሉ ናቸው” ብለዋልም፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም “የአሁኑ የሚከፋው ከሚወስዱት ልቅ ገድለው የሚሄዱት እየበዛ ነው” በማለት ስጋቱን ተስፋ አስቆራች ሲሉ ገልጸውታልም፡፡
ነዋሪዎቹ ስላነሱት ስጋትና ክስተቶች ከአከባቢው ባለስልጣናት በተለይም ከዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ለማረጋገጥና ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ በታጣቂዎቹ በኩል ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አዛዥ ዋና አማካሪ ጅሬኛ ጉደታ ደውለን በነዋሪዎቹ ምሬት ላይ አስተያየታቸውን ጠይቀናል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ