በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ልጆቻቸውን ለመታደግ ከነብር ጋር ትግል የገጠሙ አባት
ረቡዕ፣ ነሐሴ 21 2017ክስተቱ ባለፈው ሳምንት ምስራቅ ሀራርጌ ጉርሱም ወረዳ ጎባ ቀበሌ የተከሰተ ነው፡፡ ተጎጂው ሙስጠፋ ረሺድ ይባላሉ፡፡ ክስተቱ የተከሰተው ሙስጠፋ እንደ ሁልጊዜውም በሰርክ ተግባራቸው ላይ ውለው ከስራም ደክመዋቸው ወደ ቤት ስመለሱ ነው የተከሰተው፡፡
የሁለት ታዳጊ ልጆች አባት የሆኑት ሙስጠፋ ከባለቤታቸው ጋር ሆነው በአንድ ቤት ውስጥም ነበሩ፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት ተጎጂው በሰዓቱም የሆነውን እንዲህ ሲሉ ማስረዳት ጀመሩ
“ያጋጠመኝ ነገር ያው ፈጣሪ ኑር ካለ ያኖርሃል ነው እንጂ ህይወትን የሚያስቀጥል ነገር እንኳ አልነበረም፡፡ አስፈሪው የዱር እንስሳ ነበር ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ አከባቢ ከምሽቱ በግምት 1፡30 አከባቢ ከቤተሰቦቼ ጋር ቤት ውስጥ እያለን ነው ከተፍ ብሎ ወደ ቤት ዘልቆ የገባብን፡፡ አስብ ምንም ዝግጅት አላደረግንም፡፡ ስታየው የሚስፈራ ቁጡ የዱር እንስሳ ነው ነበር፡፡ በዚያ ላይ በእርሻ ማሳ ውስጥ ስለፋ ነው የዋልኩኝ፡፡ ልክ እግሮቼን ታጥቤ አረፍ ስል ነው ይህ የሆነው፡፡ በጀርባዬ የወንድሜ መኖሪያ ሀት አለ፡፡ ነብሩ ዘለል አለና ከፍ ያለች ቤት ውስጥ ባለች አልጋ ነገር ላይ ቁጭ አለ፡፡ ነብር ልጆች ያጠቃል ስለሚባል ልጆቼን እንዳያጠቃብኝ ስጋት ገባኝ፡፡ እናም የሆነ ነገር ማድረግ አለብኝ አልኩ፡፡ ያገኘሁትን ዱላ ነገር አንስቼ ላስወጣው ስል ግን ዘሎ ተከመረብኝ” ሲል የገጠመውን ክስተት ከነስሜቱ ማስረዳት ቀጠለ፡፡
ነብሩ እንዲወጣም አስቀድመን ተማጽነናል የሚለው ሙስጠፋ እንስሳው ከባለቤቱ ልጆች ለመንጠቅ ይመለከት ስለነበር ከነብሩ ጋር መግጠብ ግድ መሆኑን አስታውሷልም፡፡ ነብር ለወትሮ ፍየሎችን ለማደን ወደ ሰው ቤት ጎራ እንደሚል የሚታወቅ ቢሆንም አሁን ፍየል እንኳ በሌለበት ይህ የዱስ እንስሳ ለምን ወደ ገጠራማው የሰዎች መኖሪያ ቤት እንደገባም እንግዳ ነገር መሆኑንም ተጎጂው አስረድተዋል፡፡
አዲስ መፅሐፍ በሀረርጌ ኦሮሞ ታሪክ ፣ ባህል እና እሴት ላይ
የተቆጣው ነብሩም በሁለት ልጆች አባት ሙስጠፋ ላይ በንክሻ እና መቧጨር ጉዳት ማድረሱን ተያያዘ፡፡ “ቤት ውስጥ ፍየል የለም፡፡ እኔና ቤተሰቦቹ ነበርን ቤት ውስጥ፡፡ አከባቢችን ደን አለ፤ ግን ነብር ወደ ሰው እንዲህ ገብቶ ሰው ላይ በማነጣጠር ጥቃት ስያደርስ እምብዛም የተለመደ ነገር አልነበረም፡፡ እነ ባልጋፈጠው ግን ልጆቼን አነጣጥሮባቸው ነበር፡፡ ዘሎ እንደወጣብኝም አናቴን በመቧጨር እናበተለይም ይሄ ግራ እጄን ቀፍድዶ በመንከስ በጣም ነው የጎዳኝ፡፡ አሁን እራሴን ተሸሎኛል፤ እጄን ግን ምንም ማንቀሳቀስ አልቻልኩም፡፡ ሀኪም ቤት ሄደ ህክምና ባገኝም አሁንም ውስጡ እያመመኝ ነው” በማለት የደረሰበትን ጉዳት ገልጿል፡፡
ከነብር ጋር ትግል የማይታሰብ እና ከአቅሜ በላይ ነው የሚሉት ሙስጠፋ፤ ጎረቤቶቻቸው ባይደርሱላቸው የሱና የመላው ቤተሰቦቹ ህይወት በዚያች እለት ስጋት ላይ ወድቀው እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ ነብሩን ለመግጠም ያነሳሁት ዱላ የትእንደደረሰም ሳላውቅ ነብሩ አናቴ ላይ እንደሰፈረ ብቻ ነው የማስታውሰው የሚሉት ተጎጂው ጎረቤቶቹ እንዴት ደርሰው እንዳስጣሉትም ስያስታውስ፤
“ሰው እንደደረሰልኝ እንደገና ቤቱን ለቆ ከመውጣት ይልቅ ወደ ቤቱ ጣሪያ ዘሎ ወጣ፡፡ በቃ የፈለገው ሰው ላይ ጥቃት ማድረስ ነው፡፡ በተለይም ህጻናትን እንደሚያጠቃ ነው የሚነገረው፡፡ እነ የያዝኩት ዱላ የት እንኳ እንደገባ አላስታውስም፡፡ ከላዬ ላይ ለመወርወር ስታገል ግንድ ጋር እንደመታገል ነው የሆነብኝ በጣም ጠንካራ ነው፡፡ ሰዎች ስደርሱልኝ ለቆኝ ወደ ጣሪያ ወጣ፡፡ በር ብንከፍትም አልወጣ አለ፡፡ ከዚያን በኋላ ነው ባጡ ላይ በጥይት ገድለውት እፎይ ያልነው” ብለዋል፡፡
ያጋጣሚ ነገር ሆኖ እንጂ እንዲህ ያለ ነገር ስደጋገም አይሰማም የሚለው መስጠፋ ልጆቹንና ቤተሰቦቹን ለማዳን ሲል መስዋእትነት ብከፍለም በዚህ ግን ደስተኛ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ከዚያች እለት ጀምሮ ማህበረሰቡ ላይ በተፈጠረው የስጋት መንፈስ ከመሸ ሁሉም ሰው በሩን በመዝጋት እንደሚቀመጥም ሙስጠፋ አስረድተዋል፡፡
ክስተቱን ያረጋገጠው የጉርሱም ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን የጥንቃቄ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡ በቅርቡም ከአንድ ወር ግድም በፊት በዚሁ ተመሳሳይ ዞን ሸነን ዱጎ ወረዳ ነብር በእኩለ ሌሊት በመተኛት ላይ ባሉ አንድ ቤተሰብ ላይ ባደረሰው ጥቃት የአንድ ታዳጊ ህይወት አልፎ ሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት ማድረሱ ተመግሯል፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሠ