ስለ አደንዛዥ እጽ ሱሰኝነትን ወጣቱ ምን ይላል?
ዓርብ፣ ሚያዝያ 3 2017ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፦ የሜክሲኮ ጎዳናዎች ወደ ግዙፍ የቡጢ ስፖርት መወዳደሪያ የተቀየሩ መስለው ነበር ። የተደራጁ የማፊያ ወሮበላ ቡድኖች ቁም ስቅሏን በሚያሳዩዋት ሜክሲኮ የሜክሲኮ ሲቲ ከተማ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ከአደንዛዥ እጽ ሱስ ለማላቀቅ በሚል የአደባባይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተደርጓል ። በዚህ ሺህዎች በተሳተፉበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይ የታደሙት የሜክሲኮ ፕሬዚደንት ክላውዲያ ሼይንባው «ወጣቶች እምቢ ለሱስ በሉ» ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል ።
«ወጣት ሜክሲኮያውያን እምቢኝ ለነውጥ እምቢኝ ለሱሰኝነት በሉ ።»
ይህን የአገሪቱ ፕሬዚደንትን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የተሳተፉበት የቡጢ ስፖርት እንቅስቃሴ የመሩት የቀድሞ የቡጢ ስፖርት ባለሞያዎች ኹሊዮ ሴዛር ሻቬስ እና ዖስካር ድ ላ ሆያ ናቸው ። የአገሪቱ ፕሬዚደንት ከስፍራው ያስተላለፉት መልእክት ለሜክሲካውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም መሆኑንም ገልጠዋል ።
«እዚህ መሰባሰባችን ለሜክሲኮ እና ለዓለም አንዳች መልእክት አለው ። እዚህ ሜክሲኮ ሰላም እንገነባለን፤ ብልጽግና እናመጣለን፤ ነጻ፤ የማንም ጥገኛ ያልሆነ ሉዓላዊ አገር መሆንንም እንመርጣለን ።»
ለመሆኑ እንደ ሜክሲኮው በርካቶች እንደተሳተፉበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከአደንዛዥ እጽ ሱሰኝነት ለመላቀቅ በእኛስ አገር ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል ትላላችሁ? ሱሰኝነትስ ለመከላከል ከቤተሰብ፤ ከወጣቶች እና ከሚመለከታቸው አካላት ምን መደረግ አለበት ትላላችሁ? ሐሳባችሁን አካፍሉን ስንል በይፋዊ ማኅበራዊ መገናኛ አውታራችን መልእክት አስተላልፈን ነበር ። አስተያየት ከሰጡን መካከል ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወጣት መሰል እንቅስቃሴዎች ጠቃሚ መሆናቸውን ገልጧል ። ሆኖም ግን የአንድ ጊዜ የዘመቻ ሥራ ሁነው ከቀሩ ዘላቂ መፍትኄ አይገኝም ብሏል ።
«እሱ መፍትኄ ሊያመጣ ይችላል፤ ግን በዋናነት እኔ እንደ ግል ብትጠይቀኝ ያ የአንድ ጊዜ ፤ የአንድ ቀን ወይንም የአንድ ወይንም የሁለት ሳምንት ሥራ ነው እሱ ። ስፖርታዊው እንቅስቃሴም ሊሆን ይችላል ዐይተኸው ከሆነ እሱ ነገር የአንድ ቀን ዘመቻ ነው ። ወይ በዓሉ ሲመጣ ነው፤ ወይ ደግሞ ያ ነገር ምክንያት በማድረግ የሚሠራ ሥራ ነው እንጂ ቀጣይነት የለውም ።»
በርካቶች የሚሳተፉበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከአደንዛዥ እጽ ሱሰኝነት ለመላቀቅ ፋይዳው
የኮሮና ወረርሺኝ ተስፋፍቶ በነበረበት ወቅት ወጣቱን ጨምሮ በጋራ በአደባባይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንደነበር በመጥቀስ ያ የአንድ ሰሞን ወረት ሁኖ መቅረቱ ተገቢ አይደለም ሲል አስተያየቱን አክሏል ። ሌላ በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ለዶይቸ ቬለ ከደረሱ አስተያየቶች መካከል «በሱ» በሚል የቴሌግራም ተጠቃሚ ቀጣዩን መልእክት አስተላልፈዋል።
«ሰላም ዶይቸ ቬለ፦ መንግሥት በሱስ ሕይወት ዉስጥ ላሉ ወጣቶች ትኩረት መስጠት አለበት» ብለዋል የቴሌግራም አስተያየት የላኩልን ግለሰብ ። ቀጠል አድርገውም ባሰፈሩት ጽሑፍ፦ «ለ12 ዓመታት በሱስ ሕይወት ዉስጥ» ያሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል ። «ብዙ ተስጦዎች ነበሩኝ» ሲሉም በጽሑፍ ያስተላለፉት መልእክታቸው ይቀጥላል ።
«ብዙ ተስጦዎች ነበሩኝ፣ በትምህርቴም ከዩኒቨርስቲ በድግሪ ተመርቄ ወጥቻለሁ፣ የተለያዩ ሞያዎችም ነበሩኝ፤ ነገር ግን የሱስ ሕይወት ሽባ አድርጎኝ ምንም አይነት ተፅእኖ መፍጠር የማይችል ከንቱ ሰዉ አድርጎኛል ። በጣም የሚገርመዉ አብዛኞቹ ሱሰኞች ምሁራን ናቸዉ፤ በጣም የተማሩ ብዙ ነገር ማድረግ የማችሉ፤ ብዙ ተስጥዖ ያላቸዉ ናቸዉ ። እነዚህ ወጣቶች በመንግስት እገዛ ከዚህ ሕይወት ቢላቀቁ ለራሳቸዉ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ ምሁራን ናቸዉ ። እኔ ይሄንን ስል እራሴን ጨምሬ ነዉ የምናገረዉ ። የመንግሥት ድጋፍ በጣም ያስፈልገናል ።»
ሜክሲኮ አደገኛ እጽ አዟዟሪ የተደራጁ ወሮበሎችን እየታገለች ነው
በሺህዎች የሚቆጠሩ ታዳሚያን በተሳተፉበት የሜክሲኮው የአደባባይ ቡጢ ከፕሬዚደንቷ ባሻገር ታዋቂ ሰዎችም ታድመዋል ። አሰልጣኝ ዣቪዬር ቶሬስ በብሔራዊ የቡጢ ምክር ቤት ከሁለት ዐሥርተ ዓመታት በፊት አሸናፊ ነበሩ ። በቅዳሜው የጋራ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ላይ የተገኙት ወጣቶችን ለማበረታታት መሆኑን ጠቅሰዋል ። «የሚፈጥረው ስሜት እጅግ ከፍ ያለ ነው ። ለዚያም ነው በአደንዛዥ እጽ ወጥመድ ውስጥ የወደቁ ወጣቶችን ለማበረታታት እዚህ የተገኘነው ።»
በእርግጥም ሜክሲኮ የአደንዛዥ እጽን ለማዘዋወር ሕገወጥ የወሮበላ ቡድኖች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በየጊዜው ሰላሟ ሲናጋ ይስተዋላል ። እነዚህ አደገኛ ሕገወጥ አዟዟሪ የተደራጁ ቡድኖች በሜክሲኮ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራትም ረዣዥም እጆቻቸውን ይዘረጋሉ፥ ሲላቸው ያሻቸውን ያግታሉ፣ ያሰቃያሉ፤ ባስ ሲልም ይገድላሉ ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2006 ብቻ በዚሁ አደንዛዥ እጽ በፈጠረው ነውጥ 120,000 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በሜክሲኮ ።
ጃገማ አበበ ከአደንዛዥ እጽ ለመላቀቅ ያሉትን መፍትኄ በፌስቡክ ገጻችን ልከውልናል፤ እንዲህ ይነበባል ። «አነቃቂ እጽዋቶችን ወይም መድኃኒቶች የሚጠቀሙ ሱሰኞች ከሱሰኝነት ለመላቀቅ ከፈለጉ ቁርጠኞች፣ ሠራተኞች፣ ተመጋቢዎች፣ ከአልኮን ነጻ የሆኑ ፈሳሾችን በብዛት መውሰድ የሚችሉ መሆን አለባቸው ።» የኑሮው እየተወደደ መምጣት ጓደኞቹን አልኮል መጠጦችን ከመገባበዝ እንደገታቸው የገለጠው የአዲስ አበባ ነዋሪ ወጣት ጓደኞቹ ከአደንዛዥ እጽ ነጻ መሆናቸውን ተናግሯል ።
«አሁን እኔ አሉ ጓደኞቼ የማውቃቸው ። በፊት የሚገባበዙ የነበሩት አሁን ያም ቀረና አሁን ምን መጣ? በጣም እየጨመረ ሲሄድ በራሳቸው ጊዜ ማቆም ጀመሩ ። መኖር ስላልተቻለ ማለት ነው ። ያው ሱስ ሱስ ነው ዙሮ ዙሮ ። አደንዛዥ እጽን በምናይበት ጊዜ እሱ የተደበቀ ነገር ነው ። እንደዚህ ገንኖ የወጣ ነገር አይደለም ። ወጣቶቹ አሉ የሚጠቀሙ ። አደንዛዥ እጽን ይኼን ያክል የሚጠቀሙ ጓደኞች የሉኝም ።»
እናንተስ በያላችሁበት ወጣቱ ወደ ሱሰኝነት እንዳይገባ ከገባም ከአስቸጋሪ የሱስ አዙሪት እንዲላቀቅ ምን መደረግ አለበት ትላላችሁ? በያላችሁበት እንድትወያዩበት እንጋብዛለን ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ