ማሕደረ ዜና፤ የእስራኤል-ዩናይትድ ስቴትስና የኢራን ዉጊያ፣ ሕግ አልባዋ ዓለም
ሰኞ፣ ሰኔ 16 2017
ፕሬዝደንትን ላንድአፍታ።ጥቅምት 2024 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዝደንትና የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ።«መካከለኛዉ ምሥራቅ ዉስጥ ሠላም እንዲሰፍን እፈልጋለሁ።እዉነተኛ ሠላም።ይሕ ደግሞ ይሆናል።በዕዉነቱ በጣም ርግጠኛ ነኝ።»
ጥር 2025።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ።«አኩሪ ታሪኬ፣ ሰላም አስፋኝና ሕብረትን ፈጣሪ መሆን ነዉ።መሆን የምፈልገዉ ይኽን ነዉ።ሠላም አስፋኝና ሕብረት ፈጣሪ።»
ጊዜዉ አይሮጥም።ግን የመሪዎችን የቃልና ድርጊት ተቃርኖ ያጋልጣል።የሰላም አርበኛ፣የትብብር-አንድነት መስራች ነኝ ባዩ ትራምፕ በቀደም ጦረኝነታቸዉን አረጋገጡ።ቅዳሜ ለዕሁድ አጥቢያ።«ጥቃቶቹ አስደናቂ ወታደራዊ ድል ናቸዉ።የኢራን ቁልፍ የኑክሌር መሥሪያ ተቋማት ሙሉ በሙሉና ምንም ሳይቀር ወድመዋል።»
የእስራኤልና የአሜሪካ መሪዎች ወዳጅነት
የቀድሞዉ የፍልስጤም ነፃ አዉጪ ድርጅት (PLO) ሊቀመንበር ያሲር አረፋት እስራኤልን በጣሙን መሪዎቿን «የአሜሪካ ቀበጥ፣ ብልሹ ልጆች» ይሏቸዉ ነበር አሉ።ግን ልጅ ወላጆቹን ያዝ ይሆን? የቀድሞዋ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ጎልዳ ሚር በ1970ዎቹ በእስራኤል የዩናይትድ ስቴትስ አምሳደርን ሲያነጋግሩ «አሉት» የተባለዉ መልስ ሳይሆን አልቀረም።
ጎልዳሚር «የሁለታችንም (የእስራኤልም፣ የአሜሪካም) ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች የሁዲዎች ናቸዉ።» አሉ።«ልዩነቱ» ቀጠሉ ዕዉቋ የፖለቲከኛ-የሰሙ እንደ ፃፉት።«የኛ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ከናንተ የተሻለ እንግሊዝኛ መናገሩ ነዉ።» አከሉ።
ያኔ የእስራኤል ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ደቡብ አፍሪቃ ተወልደዉ፣ ብሪታንያ አድገዉ ዕዉቅ እስራኤላዊ ፖለቲከኛ የሆኑት አባ ኢባን ነበሩ።የዩናይትድ ስቴትስ አቻቸዉ ደግሞ ጀርመን ተወልደዉ-አድገዉ፣ አሜሪካዊ የሆኑት ሔንሪ ኪሲንጀር።ስደተኞች።በ50 ዓመታት ሒደት ዓለም ብዙ ተለዉጣለች።በአረፋት ቋንቋ የእስራኤል መሪዎች «ቅብጠት» ወይም በጎልዳሚር አገላለፅ የእስራኤል ፖለቲከኞች ከአሜሪካ አቻዎቻቸዉ የመብለጣቸዉ ዕዉነት ግን ባሰ እንጂ ቀነሰ ማለት ያሳስታል።
የኔታንያሁ ሥልት፣ የትራምፕ ቃል-ቅጥፈት
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ባለፈዉ ሰኔ 13 የኢራንን የጦር ጄኔራሎች፣ ፖለቲከኞች፣ ሳይቲስቶች በየተኙበት፣ከነ ልጅ-ሚስቶቻቸዉ እንዲገደሉ፣ ኢራን እንድትወድም ያዘዙት የቴሕራንና የዋሽግተን ዲፕሎማቶች ለ6ኛ ጊዜ ለመወያየት የያዙት ቀጠሮ አንድ ቀን ተኩል ሲቀረዉ ነዉ።
የኢራንና አፀፋፃ ኔታንያሁ እንዳሰቡት በቀላሉ የሚቋቋሙት እንዳልሆነ ሲታወቅ ግን የአሜሪካ መሪዎችን ጎትተዉ ከዉጊያዉ ጨመሩ።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከምረጡኝ ዘመቻቸዉ እስከ በዓለ-ሲመታቸዉ ድረስ ከፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ እስከ ጆ ባይደን የነበሩ የአሜሪካ መሪዎችን በጦርኝነት ሲወቅሱና ሲከስሱ ነበር።ጦርነትን ለማስቆም ቃል ያልገቡበት ጊዜም አልነበረም።
«ስኬታችን የምንለካዉ በምናሸንፈዉ ዉጊያ ሳይሆን በምናስቆም ጦርነት፣ ምናልባትም ጨርሶ ከጦርነት ባለመግባታችን ጭምር ነዉ።አኩሪዉ ታሪኬ ሰላም አስፋኝና ሕብረት መሥራች መሆን ነዉ።»
የትራምፕ መስተዳድር የኢራንን የኑክሌር መርሐ ግብር በሰላም ለማስቆም መደራደሩም ሰዉዬዉ ቃላቸዉን ገቢር የማይደረጋቸዉ ምልክት መስሎ ነበር።ይሁና የእስራኤል መሪዎች ድርድሩን አጨናግፈዉ ኢራንን ሲደበድቡ ትራምፕ የመሰለዉን ሁሉ አፍርሰዉ የኢራንን መደብደብ ደገፉ።የኢራን አፀፋ የሐማስ፣ የሒዝቡላሕ፣ የሁቲ ወይም የሶሪያ ዓይነት አንዳልሆነ ሲታወቅ፣ ወይም የጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁን የአርባ ዘመን ሕልም-ምኞትን በዉርደት እንደሚቀይር ሲታወቅ የኃያሊቱ ሐገር ኃያል መሪ ከዉጊያዉ ተመሰጉ።
«አላማችን የኢራንን ኑክሌር የማበልፀግ አቅሟን ለማዉደምና አሸባሪነትን በመርዳት የዓለም አንደኛ የሆነችዉ (ሐገር) የደቀነችዉን የኑክሌር ሥጋት ለማስወገድ ነዉ።»
ትራምፕ ኔትንያሁን ለመርዳት የአሜሪካ የሥለላ ድርጅት ዘገባን «ዉሸት» አሉት።የዓለም አዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት መረጃ፣ ማስጠንቀቂያና ምክርን፣ የአሜሪካ ሕግን፣ ዓለም አቀፍ ሥምምነትን አሽቀንጥረዉ ጣሉት።ከሁሉም በላይ ቃላቸዉን አጠፉ።ደጋፊ-መራጮጫቸዉን አሳፈሩ። የዋሽግተኑ ወኪላችን አበበ ፈለቀ እንደሚለዉ የትራምፕ ርምጃ ለሌላዉ ዓይደለም ለራሳቸዉም ግራ አጋቢ ነዉ።
«ትራምፕ ለመመረጣቸዉ ይኸ ሜክ አሜሪካን ግሬት የሚለዉ እንቅስቃሴ ዉስጥ ወሳኝ የሚባሉ ደጋፊዎቻቸዉ፣አሜሪካ በማያገባት ጉዳይ ዉስጥ መግባት የለባትም።ሁሉን ነገር በሰላም ማከናወን ይቻላል።ሌሎች ሐገሮች እየተለካከሱ የሚፈጥሩት ጦርነት የኛ ጦርነት አይደለም።----እሳቸዉም ከዚሕ ቀደም የነበሩ ማቆሚያ የሌላቸዉን ጦርነቶች እየተቹ---አሁን የወሰዱት ርምጃ ለራሳቸዉም ግራ የሚያጋባ ነዉ የሚመስለኝ።---»
የእስራኤል ድል ምንነት፣ የአሜሪካ የማይናወጥ ድጋፍ ጥቅም-ጉዳት
ዘገቦች እንደ ጠቆሙት የጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያ መንግሥት ከጋዛ እስከ ሰነዓ፣ ከደማስቆ እስከ ቤይሩት ለከፈተዉ ጦርነት ዩናይትድ ስቴትስ 23 ቢሊዮን ዶላር ከስክሳለች።የእስራኤል ጦር ጋዛን ማጥቃት ሲጀምር እርምጃዉ ሶስት ግቦች እንዳሉት ኔታንያሁ አስታዉቀዉ ነበር።
«ሐማስን ማጥፋት፣ ታጋቾቹን ማስለቀቅና ጋዛ ለወደፊቱ እስራኤልን እንዳታሰጋ ማድረግ»
ደቡባዊ እስራኤል የወረደባት የግድያ-እገታ፣ ሽብር ትክክለኛ መንስኤ ዛሬም በግልፅ ምርመራ አልተረጋገጠም።ትንሺቱ የፍልስጤሞች ግዛት ጋዛ ከሰዎች መኖሪያነት ወደ ሰዎች ቄራነት ተቀይራለች።የሐማስና የሒዝቦላሕ መሪዎች፣ ፖለቲከኞችና ታጣቂዎች ተገድለዋል።ዓመት ከዘጠኝ ወሩ።ሐማስ፣ ሒዝቡላሕ፣ ሁቲ ጠፍተዉ ይሆን? ከሐማስ ጋር በተደረገ ድርድር ከተለቀቁት ዉጪ የተለቀቀ ታጋች ግን የለም።
የጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ መንግሥት በተለይ ጋዛ ዉስጥ የነብስ አድን ሠራተኞችን፣ ሐኪሞችን፣ ዕርዳታ አቀባዮችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ሕፃናትን፣ ሴቶችን አቅመ ደካሞችን፣ ርዳታ ጠባቂዎችን ሳይቀር መግደሉን እንዲያቆም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተደጋጋሚ ጠይቋል። የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጮኸዋል።የዓለም ፍርድ ቤቶች ወስነዋል።የየሐገሩ ሕዝብ ባደባባይ ተማፅኗል።
ከዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች በተሰጣቸዉ ልዩ ፍቃድና ዙሪያ መለስ ድጋፍዉግዘት፣ ጥያቄ፣ጩኸት፣ዉሳኔዉን ዉድቅ ያደረጉት የእስራኤል መሪዎች ቴህራንን፣አሕቫዝን፣ ካራዥ፣ኢስፋሐን፣ ቆምና ሌሎችንም የኢራን ከተማ፣ መንደር፣ መስሪያ ቤቶችን እያስጋዩ ነዉ።የኢራን ሚሳዬሎችም ቴል አቪቭ፣ኢላት፣ ራማት ጋን፣ ሪሾን ሌሲዮን፣ ሐይፋን፣ እየሩሳሌምን ሌሎችንም ከተሞች እያነደዱ ነዉ።
የኢራን አፀፋ ምን ሊሆን ይችላል?
የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ከእስራኤል ጎን ተሰልፎ ኢራንን ከደበደበ ወዲሕ ደግሞ ኢራን የሆርሙስ ወሽመጥን ለመዝጋት እየዛተች ነዉ።የሆርሙስ ሰርጥ በቀን 20 ሚሊዮን በርሚል ነዳጅ ዘይት የሚያልፍበት የባሕር መስመር ነዉ።ኢራን፣ ኢራቅን ጨምሮ መካከለኛዉ ምሥራቅ ዉስጥ የሠፈረዉን የአሜሪካንን ጦር በቀጥታ ወይም በደጋፊዎቿ በኩል ልታጠቃ ትችላለችም።ከዓለም አቀፉ የአዉቶሚክ ሥምምነት እራስዋን አግልላ አሥፈሪዉን ቦምብ መሥራትዋን ልተቀጥልም ትችላለች።
የትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣናት የኔታንያሁን ልብ ካራሱ በኋላ ብቀላዉን ለማስቀረት «ሰላም እንፈልጋለን» እያሉ ነዉ።ግን ከዚሕ በፊት የገቡትን ቃል ባፈረሱ ማግስት አዲስ የሚገቡትን ቃል የሚምን ካለ እሱ በርግጥ ጅል ነዉ። እንደገና አበበ።
«አንተን መሬት ላይ አጋድሜ----ራሳቸዉ ትራምፕ፣ ምክትላቸዉ፣ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹሞች ጥምረት ሊቀመንበርም ከኢራን ጋር ጦርነት አንፈልግም---»
የዶናልድ ትራምፕ ዋና ደጋፊ የሚባሉት የአሜሪካ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ አቀንቃኞች በበኩላቸዉ ፣ አበበ ፈለቀ እንዳለዉ ዩናይትድ ስቴትስ በኔታንያሁ ጦስ ዘላ መግባት አልነበረባትም ባይ ናቸዉ።
«ኔታንያሁ በኢራቅ ጦርነት ጊዜም፣ ኢራቅ የሌላትን ጦር መሳሪያ አላት ብለዉ የተናገሩ።ከ1995 ጀምረዉ በመካከለኛዉ ምሥራቅ ላይ አሜሪካ ጣልቃ እንድትገባ ጥረት የሚያደርጉ----»
«ኃይል ልክ ነዉ» የኃይለኞች ዓለም
የቀድሞዉ የዶናልድ ትራምፕ የፀጥታ አማካሪ ጆን ቦልተን ባንድ ወቅት «የዓለም ማሕበረሰብ የሚባል ነገር የለም።ያለችዉ አንድ ልዕለ ኃያል ሐገር ናት-ዩናይትድ ስቴትስ።» ብለዉ ነበር።አላበሉም።ዓለም የጋራ ማሕበር፣ ፍርድ ቤት፣ ሕግ፣ ደንብ፣ ሥምምነት የሚኖራት ለአሜሪካና ለእስራኤል እስከጠቀመ ብቻ ነዉ።ባይሆን ኖሮ እስራኤል የኑክሌር ቦምብ መታጠቋ የአደባባይ ሚስጥር በሆነበት በዚሕ ዘመን ኢራን «ሰላማዊ» ያለችዉ የኑክሌር መርሐ-ግብር የሚያስወነጅልበት ምክንያት በርግጥ በምክንያት ለሚያምኑ ግራ አጋቢ ነዉ።
ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯ ከተወገዘ፣ በማዕቀብ ካስቀጣ፣ለዩክሬን ዙሪያ መለስ ድጋፍ ካሰጠ እስራኤልና አሜሪካ ሊባኖስን፣የመንን፣ ሶሪያን፣ኢራንን መደብደባቸዉ፣ታጣቂዎችን ከሕሙማን ሳይለዩ መግደላቸው የማያስወገዝ፣ የማያስጠይቅ፣ የማያስቀጣበት ምክንያት የለም።ነገ ቻይና ታይዋንን፣ ወይም ጃፓንን፣ ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያን ቢወርሩ ዓለም አቀፍ ሕግን አፈረሱ ይባል ይሆን?
የቴሕራን ገዢዎች ለሚደርስባቸዉ ጥቃት አፀፋ ከመሰንዘር ባለፍ እስካሁን ዉጊያ ለመጀመር ወይም ለማባባስ የፈለጉ ወይም የቻሉ አይመስልም።የኢራኖች ፍርሐት፣ብልጠት ይሁን ሥልታዊ እርምጃ የዋሽግተን እየሩሳሌም መሪዎችን እብሪት እያጋለጠ፣የአዉሮጶችን «ሽባነት» ገሐድ እያወጣ፣ ምናልባትም ታዛቢዎች እንደሚገምቱት ሩሲያ፣ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ፓኪስታንን፣ ቱርክና ሌሎች መንግሥታትን ከጎኗ ሊያሰልፍ ይችላል።ዓለም ግን በርግጥም የሕግ ሳትሆን የጉልበተኞች ተገዢ ናት።
ነጋሽ መሐመድ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር