ማሕደረ ዜና፣ የሱዳን ትዩዩ መንግስት፣ ጦርነቱና የዉጪ ጣልቃ ገብነት
ሰኞ፣ የካቲት 17 2017ሁሉም ሱዳኖች ናቸዉ።ሁሉም ለሱዳን አንድነት፣ ለሉዓላዊነቷና ለሕዝቧ ሠላም ቆመናል ይላሉ።ግን እንደ ተጠፋፉ ለመቀጠል ይዛዛታሉ።የዘንድሮዉ የሙስሊሞች ቅዱስ የፆም ወር ረመዳን በዚሕ ሳምንት ይጀመራል።እኒያ የሱዳንን ሕዝብ ለሁለት ዓመት ያክል በጦርነት፣ ረሐብና ሥደት የጠበሱት ኃይላት ዘንድሮም ለረመዳን በአንድ ቀን-ትናንት ዕሁድ።ሶስት ሥፍራ-ናይሮቢ፣ኤል ጊታንያ እና ካይሮ-ሶስት የተስፋ ትያትሮች አቀረቡለት።የትዩዩ መንግሥት ምሥረታ፣ የመከላከያ ጦር ድልና የካርቱም ካይሮዎች ዉግዘትን ።የአንድ ቀኑ ሶስት ሁነት መነሻ፣ የናይሮቢ-ካይሮዎች ጣልቃ ገብነት ማጣቃሻ፣ ለሱዳን ሕዝብ መጥቀም መጉዳቱ መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።
ትናንት ናይሮቢ ዉስጥ የትይዩ መንግስት መሠረትን ያሉት ቡድናት ብዙ ናቸዉ።በጦር ሜዳዉ ሽንፈት እየገጠመዉ የመጣዉ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር (RSF) ከሱዳን ብሔራዊ ዑማ ፓርቲ በተለይም ብሉናይልና ሌሎች የደቡባዊ ሱዳን ግዛቶች ዉስጥ በርካታ አካባቢዎችን ከሚቆጣጠረዉ ከሱዳን ሕዝብ ነፃ አዉጪ ንቅናቄ-ሰሜን (SPLM-N) ጋር መተባበሩ ለብዙ ታዛቢዎች አስገራሚ፣ የሱዳንን የፖለቲካ ምሥቅልቅል አደናጋሪ አድርጎታልም።
ጉባኤተኞቹ እንዳሉት ዓላማቸዉ የሱዳንን አንድነት፣ የሕዝቧን ሠላምና ደሕንነት በጋራ ማስከበር ነዉ።የጉባኤተኞቹን ዉሳኔ በንባብ ያሰሙት የፍትሕና የእኩልነት ንቅናቄ መሪ ሳንዳል ሐጋር እንዳሉት ደግሞ ጦርነቶችን በሙሉ ለማቆም ቆርጠዋልም።
«የጋራ ትብብርን በመፍጠሩ እሳቤ መሠረት እኛ የዚሕ (ቻርተር) ፈራሚዎች ለእናት ሐገራችንና ለሕዝባችን ያለብንን ታሪካዊ ኃላፊነት እንገነዘባለን።ሁሉንም ጦርነቶች ለማቆም፣ለየቀዉሶቹ ተገቢዉን መፍትሔ ለመስጠት በፅናት ቆመናል።አዲሲቱን ሱዳን ለመፍጠር በፅናት እንደምን ቆም ቃል እንገባለን።ለሱዳን አንድነት፣ ለግዛትዋ መከበርና ለሕዝቡ ደህንነት በፅናት እንቆማለን።»
የትብብሩ ፋይዳ፣ የሐምዲቲ ትርፍ
ተባባሪዎቹ በአማላይ ቃላት የከሸኑትን ሥምምነትና ትብብር ገቢር ማድረግ አለማድረጋቸዉ በርግጥ አጠያያቂ ነዉ።ፈጥኖ ደራሹ ጦር ከቀድሞ ቀንደኛ ጠላቶቹ በተለይም ከSPLM-N ጋር መወዳጀቱ ግን የወታደራዊ ጉዳይ ተንታኞች እንደሚሉት ከምዕራባዊ ሱዳን እስከ ደቡብ ሱዳን ድንበር ጥግ፣ ከሊቢያ ጠረፍ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር በሚደርሱ አካባቢዎች ለመንቀሳቀስ ይጠቅመዋል።
የሱዳንን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥነትን ሥልጣን ከሐገሪቱ ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበርነት ጋር ደርበዉ የያዙት ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን ከቀድሞዉ ምክትላቸዉ ከጄኔራል መሐመድ ሐምንዳን ዳግሎ ጋር እንደተጣሉ የምክትል መሪነቱን ሥልጣን የሾሙት መሊክ አጋርን ነዉ።ግንቦት 2023 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)
ከሰሜን ሱዳን የሚወለዱት አል ቡርሐን ከአጋር ጋር ሲወዳጁ የደቡባዊ ሱዳንን ፖለቲካ የመቆጣጠራቸዉ ምልክት ተደርጎ ነበር።አሁን ደግሞ የዘር ግንዳቸዉን ከምዕራብ ሱዳን ዳርፉር የሚመዙት ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐምዲቲ) የደቡባዊ ሱዳን ፖለቲከኞችን ከጎናቸዉ ማሰለፋቸዉ ለአል ቡርሐን-አጋርን ትብብር ትልቅ ፈተና ነዉ።
የአጋር ሚና፣ የSPLM-N አቋም
አጋር የባላባት ልጅ፣ ብልጥ ፖለቲከኛ፣ የሽምቅ ጦር አዋጊ ናቸዉ።በነፍጥ-የሚዘወረዉን የሱዳንን ፖለቲካ ከተቀየጡበት ጊዜ ጀምሮ ከደቡብ የጆን ጋራንግን፣ ከሰሜን የዑመር ሐሰን አል በሽርን የፖለቲካ-ወታደራዊ ሥልት፣ብልጠትና ሴራን ተሳትፈዉበት ጠንቅቀዉ ያዉቁታል።
የሱዳን ሕዝብ ነፃ አዉጪ ንቅናቄን (SPLM)ን ከተቀየጡበት ከ1983 ጀምሮ በፖለቲካ-ሽምቅ ዉጊያ-ድርድር የተመረዘዉን አደገኛ የፖለቲካ ባሕርን እየዋኙ ዓመታት አስቆጥረዉ ደቡብ ሱዳን በ2011 ነፃ ስትወጣ የሱዳን ሕዝብ ንቅናቄ-ሰሜን (SPLM-N) የተሰኘዉን አማፂ ቡድን መሠረቱ።
ከ2017 ጀምሮ ከቅርብ ጓዳቸዉ አብዱል አዚዝ አል ሒሉ ጋር ተጋጭተዉ SPLM-N የአጋርና የሒሉ በሚል ለሁለት ተከፍሎ በሚዋጋበት መሐል የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ተመሠረተ።የካቲት 2021።አጋርም ብሉ ናይል ግዛትን ትተዉ ካርቱም ዉስጥ ዕዉቅ ፖለቲከኛ ሆኑ።የምክር ቤቱ አባል እስከሆኑበት ጊዜ ድረስ ግን ለጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐንም፣ ለጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎም «ጠላት» ባይሆኑ እንኳን ወዳጅ አልነበሩም።አጋር የፖለቲካ መሰላሉን ሽቅብ ሲረማመዱ የአብዱል አዚዝ አል ሒሉ እና ሶስተኛ የ SPLM-N አንጃ የመሠረቱት የያሲር አርሚን ጠብ ቀጠለ።አጋር በ2023 የጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን ምክትል ሲሆኑ ደግሞ «የጠላትሕ ጠላት---» በሚለዉ ሥልት የSPLM-N አንጃዎች መሪዎች የቀድሞ ጠላታቸዉን የጄኔራል ሐምዲቲን ወዳጅነት ያማትሩ ያዙ።ትናንት ተሳካላቸዉ።ወይም የተሳካላቸዉ መሰለ።
የጦር ሜዳዉ ድል-የካርቱምና የካይሮ ወዳጅነት
ይሁንና ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎና አዲስ ወዳጆቻቸዉ ናይሮቢ ላይ ያገኙን ፖለቲካዊ ድል አጣጥመዉ ሳያበቁ፣ የሱዳን መከላከያ ጦር ኤል ጊታንያ በተባለችዉ ከተማና አካባቢ የሠፈረዉን የፈጥኖ ደራሽ ጠላቱን ደምስሶ ከተማይቱን ተቆጣጥሯል።የሱዳን መከላከያ ጦር አዛዦች እንዳሉት ጦራቸዉ ኤል ኡቤይድ የተባለችዉን የሰሜን ኮርዶፋን ግዛት ዋና ከተማን የከበበዉን የፈጥኖ ደራሽ ጦርን ከበባ ሰብሮ ከተማይቱን ከሌሎች ከተሞች ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን ከፍቷልም።
ኤል ጊታንያና ኤል-ዑቤት የተባሉት ከተሞች የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ባለፈዉ ሳምንት ሲያንስ 200 ሲበዛ 400 ሰላማዊ ሰዎች ገድሎባቸዉል ከተባሉት አካባቢዎች በቅርብ ርቀት የሚገኙ ናቸዉ።አል ቡርሐን የጦራቸዉን ድል በአካል ለማየት ከካርቱም 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ አንድ የነዳጅ ማጣሪያ ተቋማን ሲጎበኙ ትናንት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉ ካይሮ ነበሩ።
ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዓሊ አሕመድ ዩሱፍ አል ሸሪፍ ከግብፁ አቻቸዉ ከበድር አብድላቲይ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ እንዳሉት የሱዳን ጦር ኃይልና ተባባሪዎቹ ያሸንፋሉ።የናይሮቢ ጉባኤተኞችን ደግሞ «እጅ ከመስጠት ሌላ-ሌላ አማራጭ» የላችሁም ብለዋል።
«ጦርነቱ በሱዳን ጦር ኃይልና በተባባሪዎቹ በሕዝባዊ ኃይላት አሸናፊነት ይጠናቀቃል።እነዚሕ ኃይላት የፈጥኖ ደራሹን ሚሊሺያ ኃይላት ሲያሸንፉ ጦርነቱ ይቆማል።ከዚሕ ዉጪ ጦርነቱን ሊያስቆም የሚችለዉ አማራጭ እጅ መስጠት ብቻ ነዉ።»
የሱዳኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ከግብፅ አቻቸዉ ጋር ከጋዛ ቀዉስ እስከ ሶሪያ የወደፊት ሥርዓት፣ ከአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ ዉሳኔዎች እስከ የሕዳሴዉ ግድብ ያሉ ጉዳዮችን አንስተዉ መነጋገራቸዉ ተነግሯል።በተለይ የፈጥኖ ደራሹን ጦር ትረዳለች የምትባለዉ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እጇን እንድትሰበስብ የካይሮዎችን ድጋፍ በድጋሚ መጠየቃቸዉ አልቀረም።
ይሁንና የሱዳኑ ትልቅ ዲፕሎማት የካይሮ ጉዟቸዉ ዋና ዓላማ አቡዳቢ ወይም ናይሮቢዎች ከፈጥኖ ደራሹ ጎን የቆሞቱን ያክል ካይሮዎች ከመከላከያዉ ጦር ጎን መቆማቸዉን ለወዳጅም ለጠላትም ለማሳየት ነዉ።ተሳካላቸዉ።
የግብፅ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በድር አብድልላቲይትዩዩ ሥርዓት አያስፈልግም አሉ።የሱዳን የግዛት አንድነትም ለግብፅ ቀይ መስመር ነዉ።
«የሱዳን የግዛት አንድነትና ደሕንነት ለግብፅ ቀይ መስመር ነዉ።ይሕንን በቀላሉ አናየዉም።ሱዳን ዉስጥ አሁን ያለዉን ሥርዓት የሚፃረር አዲስ ሥርዓት እንዲመሠረት የሚደረገዉን ጥሪ እንቃወማለን።ሱዳን በዚሕ ሁኔታና ቀዉስ ባለችበት ባሁኑ ወቅት ሙሉ ድጋፋችንን እንደምንሰጥ እናረጋግጣለን።ሱዳን ከቀዉሱ እንደምትወጣ እርግጠኞች ነን።አዲሲቱን ሱዳን ለመገንባት በሚደረገዉ ጥረት፣ ኢንሻአላሕ ፣ግብፅ ቀጥተኛና ግንባር ቀደም ሚና ትጫወታለች።»
የካይሮዎችን ሙሉ ድጋፍ ባደባባይ በማግኘታቸዉ የተደፋፈሩት የሱዳን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዓሊ የሱፍ አሕመድ አል ሸሪፍ መንግሥታቸዉ ለትይዩዉ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ለትይዩዉ መንግሥት ድጋፍ ለሚሰጡ መንግሥታት ጭምር ዕዉቅና አይስጥም።
«(የግብፁ) ሚንስትር ትዩዩ የሚባል ሥርዓት የለም ሲሉ፣ አሁን ካለዉ ከሱዳን መንግሥት ጋር የሚፃ,ረር ወይም ትዩዩ የሚባል መንግስት የለም ማለታቸዉ ነዉ።ይሕ የግብፅ ግልፅና የተረጋገጠ አቋም መሆኑን ሚንስትሩ ነግረዉናል።እኛ ሱዳኖችም እንደ ሐገር፣ ትይዩ ለሚባለዉ መንግስት ዕዉቅና ለሚሰጡ መንግሥታት እዉቅና አንሰጥም።»
የዉጪ ጣልቃ ገብነት በግልፅ እየታየ ነዉ
የሱዳኑ የርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረበት ከሚያዚያ 2023 ጀምሮ የጦርነቱ ዳፋ ለሌች የአካባቢዉ ሐገራት እንደሚተርፍ፣ ሌሎች ሐገራትም እጃቸዉን ማስገባታቸዉ እንደማይቀር ያልተናገረ ተንታኝ አልነበረም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ባለፈዉ ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ደገሙት
ከአረብ ሐገራት ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያና ቀጠር የሱዳን መከላከያ ጦር ኃይልን፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ባንፃሩ የፈጥኖ ደራሽ ኃይልን እንደሚረዱ በሰፊዉ እየተዘገበ ነዉ።ምዕራባዉያን መንግሥታት ባብዛኛዉ የሁለቱን ኃይላት ድል-ሽንፈት ራቅ ብለዉ መመልከት የመረጡ መስለዋል።ሩሲያ ግን ከሱዳን መከላከያ ጦር ጎን መቆሟን በቅርቡ በግልፅ አሳይታለች።
ከአፍሪቃ ሐገራት እስካሁን ከቻድ እስከ ኤርትራ፣ ከኢትዮጵያ እስከ ዩጋንዳ፣ ከኬንያ እስከ ሶማሊያ የሚገኙ መንግሥታት ስደተኞችን በማስተናገድ፣ተዋጊ ኃይላትን በቀጥታም፣ በተዘዋዋሪም በመደገፍ ወይም በመቃወም እጃቸዉ ተነካክቷል ተብለዉ ይታማሉ።
አሁን ግን ኬንያ ከሱዳን ተፋላሚዎች አንዱን መደገፏን በግልፅ አስመስክራለች።ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦርና የተባባሪዎቹን ተወካዮች በመመንግስት የመሰብሰቢያ አዳራሽና ሕንፃ ዉስጥ እንዲሰበሰቡ የመፍቀዳቸዉ ድፍረትን የገዙት፣ አልተረጋገጠም እንጂ፣ «በአቡዳቢዎች ዶላር ነዉ» ይባላል።
በአቡዳቢዎች ዳረጎት፣ በሩቶ ፈቃድና ይሁንታ ከናይሮቢ፣ በአል-ሲሲ ትብብርና ፍላጎት ከካይሮ የተንቆረቆረዉ ቃል፣ዉሳኔና ዛቻ የሚላስ የሚቀመስ ለሚጠብቀዉ 30 ሚሊዮን ሱዳንዊ ዘካተል ፊጥር ሊሆን ፈፅሞ አይችልም። ለሱዳን፣ ለኬንያ፣ ለአፍሪቃ አንድነትና ሠላም መጥቀሙም ብዙዎች እንደሚሉት አጠራጣሪ ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር