ሙኒክና አካባቢዉ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የባህል ማኅበር 30ኛ ዓመት
ሐሙስ፣ ግንቦት 21 2017ሙኒክና አካባቢዉ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የባህል ማኅበር 30ኛ ዓመት
በደቡባዊ ጀርመን በባቫርያ ግዛት ሙኒክ ከተማ እና አካባቢዉ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን ያቀፈዉ የባህል ማኅበር የተመሰረተበትን 30ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች እና ዉይይቶች አከበረ። በቅርቡ የማህበሩን የሊቀመንበርነት መንበር የተረከቡት አቶ ኃይሉ ማሞ፤ ማህበሩ በቅብብሎሽ እዚህ መድረሱን ተናግረዋል። በሙኒክ ከተማ እና አካባቢዉ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን ያቀፈዉ የባህል ማኅበር 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር በዝግጅቱ ላይ ኢትዮጵያዉያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን፤ ጀርመናዉያን ብሎም ዓለምአቀፍ ወዳጆቻቸዉ ተገኝተዋል። በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት ተጋባዥ ከነበሩት መካከል ደግሞ፤ የባቫሪያ ግዛተ- መንግስት የውህደት ኮሚሽነር ሚስተር ካርል ስትራውብ፣ የሙኒክ ከተማ የፍልሰት ጉዳይ አማካሪ እና የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዲሚትሪና ላንግ፣ በሙኒክ ከተማ የወንጌላዊት የዉህደት ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ጎትፍሪድ ሮሽ፣ እንዲሁም በበርሊን ነዋሪ የሆኑት ትዉልደ ኢትዮጵያዊዉ የኤኮኖሚና የአስተዳደር ምሁር ዶክተር ፀጋዩ ደግነህ ይገኙበታል። በማኅበሩ 30ኛ ዓመት ክብረ በዓል እጅግ የተደሰቱት የባቫሪያ ግዛት መንግስት የውህደት ኮሚሽነር ሚስተር ካርል ስትራውብ፣ የሙኪክ ከተማና አካባቢዉ የኢትዮጵያዉያን ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ኃይሉ ማሞን የባቫርያ መንግሥት ፓርላማ የዉህደት ምክር ቤት አባል አድርገዉ ሾመዋቸዋል። በሙኒክ እና አካባቢዉ የኢትዮጵያዉያን የባህል ማኅበር እንኳን አደረሳችሁ፤ እንዴት ነበር ዝግጅቱ ማኅበሩስ በጥንካሪ እንዴት እዚህ ደረሰ ስንል የማኅበሩን ሊቀመንበር አቶ ኃይሉ ማሞን ጠይቀናቸዋል።
«እዚህ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን ባህላቸዉን የናፈቁ ፤ ብሎም ባህላቸዉን እንዲያዉቁ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ ማህበሩ ያሰባስባል። በጀርመን ስንኖርም በዉህደት ለመኖርና ኑሮን ለማቅለል፤ በጋራ እንሰራለን። ሌላዉ የኢትዮጵያን ባህል እዚህ ከሚኖረዉ ከዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን ባህልን ማስተዋወቅ ልምድን መለዋወጥ ነዉ። ሙዚቃችን ፤ሥነ ጥበባችን፤ ቱፊታችን ፣ ባህላችን ይህ ማህበሩ ከሚሰራቸዉ ጥቂት እና ዋንኛ ከሚባሉት ነገሮች መካከል የሚጠቀሱት ናቸዉ።» የኢትዮ ኮለኝ የስፖርትና የባህል ማኅበር ዓመታዊ በዓል
በሙኒክ እና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን ያቀፈዉ የባህል ማኅበር 30ኛ ዓመቱን ሲያከብር፤ በክብር እንግድነት ከተገኙት መካከል በበርሊን ነዋሪ የሆኑት ትዉልደ ኢትዮጵያዊዉ የኤኮኖሚ እና የአስተዳደር ምሁር ዶክተር ፀጋዩ ደግነህ ናቸዉ። ዶ/ር ፀጋዬ በኢትዮጵያዉያኑ ማኅበር በጣም መኩራታቸዉን አጫዉተዉናል። በዝግጅቱ ላይ ስለኢትዮጵያ እና ህዝቦችዋ ረዘም ያለ ገለፃም ማድረጋቸዉን ተናግረዋል።
« በዝግጅቱ ላይ ወደ አርባ ደቂቃ የሚፈጅ ንግግር እና ገለፃ አድርጌ ነበር። ከዝግጅቶቼ መካከል ዋናዉ የኢትዮጵያ ብዝሃነትን የሚገልፅ፤ እና የኢትዮጵያዉያን ኑሮ በጀርመን በሚል በነበር፤ ያቀረብኩትም በጀርመንኛ ነበር። በዝጅግቱ ላይ ብዙ እንግዶች ነበር። በገለፃዬ ላይ የኢትዮጵያን የቋንቋ፤ የባህል፤ የመልከዓምድር፤ የሃይማኖት እና የመሳሰሉትን ብዝሃነት አስረድቻለሁ። እዚህ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን በባህል ልዉዉጥ፤ በእዉቀት ልዉዉጥ ብሎም የግንኙነት ድልድይን በመገንባት ያላቸዉን አስተዋፅኦ ተናግሪያለሁ። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያዉያን ስላለባቸዉ ችግር ለምሳሌ የቋንቋ ችግር፤ ከመጤ ጠሎች የሚደርስባቸዉ ችግር፤ የመኖርያ ቤት አለማግኘት ችግር ስለመሳሰሉትም አንስቻለሁ።»
በሙኒክ የኢትዮጵያዉያን ማኅበር 30ኛ ዓመት ክብረ በዓል መድረክ ላይ ከዶክተር ፀጋዬ ሌላ የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ኃይሉ ማሞ የኢትዮጵያ ባህል እና ታሪክ በፊልም በተደገፈ ንግግር አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ የአካባቢዉ ጀርመናዉያን ባለሥልጣናት፤ ንግግር አድርገዋል ፤ የመድረክ ላይ ዉይይት እና ጥያቄ መልስ ነበር ከቀረቡት ጥቃቄዎች መካከል ይላሉ ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ በመቀጠል፤«እቴሜቴ» የኢትዮ ጀርመን የቤተሰብና የባህል ማኅበር
« አቶ ኃይሉ ማሞ ማህበሩን እየመራ ያለዉ በጣም ጥሩ በሆነ ሁኔታ ነዉ። ለኔ ቀርበዉልኝ ከነበሩት ጥያቄዎች መካከል፤ ኢትዮጵያ ደሃ ነች ዉይ የሚል ነበር። ኢትዮጵያ የገንዘብ ደሃ ብትሆም ፤ ወይም እንደጀርመን ብዙ ገንዘብ ባይኖራትም፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ማዕድናት የበለፀገች መሆንዋን፤ በወጣት የሰዉ ሃይል የበለፀገች መሆንዋን ፤ በተለያዩ ቋንቋዎች እና የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የሚገኙባት መሆንዋን፤ የተለያዩ ሃይማኖቶች መገኛ መሆንዋን ተናግሪያለሁ፤ ኢትዮጵያ የታሪክ ሃብታም መሆንዋንም አክያለሁ።»
ዶክተር ፀጋዪ እንደነገሩን በጀርመን በግምት ወደ 60 ሽህ የሚጠጉ ኢትዮጵያዉያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል ከ 21 ሺህ በላይ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ዜግነትን ይዘዉ የሚኖሩ ናቸዉ። በኢትዮጵያዉያኑ የባህል ማህበር የተደሰቱት የባቫሪያ ግዛት መንግስት የውህደት ኮሚሽነር ሚስተር ካርል ስትራውብ፣ የሙኪክ ከተማና አካባቢዉ የኢትዮጵያዉያን ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ኃይሉ ማሞን የባቫርያ መንግሥት ፓርላማ የዉህደት ምክር ቤት አባል አድርገዉ ሾመዋቸዋል። ጀርመን የተማሩ ኢትዮጵያውያን ማኅበር፤ «የኢትዮ-ጀርመን ግንኙነት ድልድይ»
የተለያዩ ማህበራት የሚሰበሰቡበት በሙኒክ ከተማ የወንጌላዊት የዉህደት ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ጎትፍሪድ ሮሽ ከአራት ዓመት በፊት ጀምሮ ማዕከሉን እየመሩ ናቸዉ። ኢትዮጵያዉያኑ ዝግጅት ሲኖራቸዉ ወደ ስፍራዉ እንደሚመጡ እና ዝግጅቶቻቸዉን እንደሚያካሂዱም ተናግረዋል። ስለኢትዮጵያዉያ የኦርቶዶክስ እምነት በተለይ የመስቀል እና የደመራ በዓልን በተመለከተ ከኢትዮጵያዉያን ጋር ማክበራቸዉ እና በጣም መደሰታቸዉን ተናግረዋል። በርካታ ማህበራት ወደዚህ መዓከል ቢመጡም ተዋህዶ በጋራ ለመስራት የኢትዮጵያዉያኑ የባህል ማኅበር ቀዳሚዉን ስፋራ እንደሚይዝ ነዉ የገለፁት።
«በሙኒክ እና አካባቢዉ በሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የዛሬ 30 ዓመት በተቋቋመዉ የባህል ማዕከል ምስረታ ላይ የክብር እንግዳ ሆኜ በመጋበዜ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል። በባቫርያ ግዛት በወንጌላዊ እምነት ተከታይ በብዛት በሚገኝ ቢሆንም፤ በማዕከላችን ኢትዮጵያዉያን የተለያዩ እምነት የክርስትና ፤ የእስልምና ብሎም ለሃይማኖት እንብዛም ትኩረት የማይሰጡ ግን በማህበሩ የሚሳተፉ በማዕከላችን ዉስጥ ብዙ ሥራን ይሰራሉ። ብዙ ኢትዮጵያዉያን እዚህ ከተማ ኑሮዋቸዉን የመሰረቱ እና ለከተማዋ ሥራን የሚሰሩም ናቸዉ። በምስረታዉ በዓል ላይ የባቫሪያ ግዛት- መንግስት የውህደት ኮሚሽነር እንዲሁም የሙኒክ ከተማ የፍልሰት ጉዳይ አማካሪ እና የቦርድ ሰብሳቢ ግዜ ሰጥተዉ መገኘታቸዉ ትልቅ ጉዳይ ነዉ»
በሙኒክ የኢትዮጵያዉያን የባህል መድረክ 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ የክብር ተጋባዥ የነበሩት ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ እንደሚሉት፤ በዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን እንዲህ አይነት ማኅበር ዉስጥ ታቅፈዉ ራሳቸዉን በመርዳት አገራቸዉን ሊያስተዋዉቁ በሚኖሩበት አካባቢም የተለያዩ ተሳትፎዎችን በማድረግ በቀላሉ ተዋህደዉ መኖር እንደሚችሉም ተናግረዋል።በጀርመን ምርጫ የትዉልደ ኢትዮጵያዉያን ተሳትፎ
የሙኒኩን የኢትዮጵያዉያን ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ኃይሉ ማሞ ብሎም በኢትዮጵያዉያኑ ማኅበር ክብረ በዓል ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ እና ዶ/ር ጎትፍሪድ ሮሽ ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም እናመሰግናለን።
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ