ለጤናው ዘርፍ ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ርዳታ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 30 2012በመላው ዓለም በኮቪድ 19 መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር ከ11,5 ሚሊየን በልጧል። በዚህ በሽታ ተይዘው ያገገሙት ደግሞ ከ6,5 ሚሊየን በላይ መሆናቸውን የዓለም የጤና ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ። ካለፈው ታኅሣስ ወር ወዲህ በፍጥነት በመላው ዓለም የተሰራጨው ይህ ወረርሽኝ ከ500 ሺህ በላይ ሰዎችንም ሕይወት ቀጥፏል። ኢትዮጵያ ውስጥ በተሐዋሲው መያዛቸው ከተረጋገጠው ከ6 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ግማሽ ያህሉ ከበሽታው ማገገማቸው ቢገለፅም የታማሚዎቹ ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። የህክምና ባለሙያዎች ሳይቀሩ በኮሮና ተሐዋሲ የመያዛቸው ዜና ከተሰማ ብዙም አልቆየም። ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዚህ መሰናዶ ያቀረብናቸው የህክምና ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ በወረርሽኝ ወቅት በሥራቸው ላይ እንዴት ለበሽታው ሊጋለጡ እንደሚችሉ እማኝነታቸውን እንዳካፈሉን ይታወሳል። ኢትዮጵያ ውስጥ ተሐዋሲውን ለመከላከል አስፈላጊ ቁሳቁሶች እንደልብ በሌሉበት የችግሩ መባባስ ያሳሰባቸው እዚህ ጀርመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በመሰባሰብ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። አቶ ዓለሙ ታደሰ በተለያዩ የጀርመን ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንና ጀርመናውያንን በማስተባበር ጥሬ ገንዘብና ለህክምና ባለሙያዎች መገልገያ ቁሳቁሶችን ማሰባሰብ መቻሉን ይናገራሉ።
የፍራንክፈርት ከተማ አካባቢ ነዋሪው አቶ ዓለሙ በዚህ ጊዜ ውስጥ በርካታ ቁሳቁሶች መሰባሰባቸውን ከእነዚህ መካከልም ለሃኪሞች የሚሆን የፊት መከላከያ ጭንብልና የሙቀት መለኪያዎች እንደሚገኙበት ዘርዝረዋል። ከዚህ በተጨማሪም በንግድ ሥራ የተሰማሩ ወገኖች የአቅማቸውን በማዋጣት ማሽን ገዝተው ለመላክ የሚያስችላቸውን ገንዘብ እያሰባሰቡ መሆኑንም ገልጸዋል። ዶክተሮች ለኢትዮጵያ ወይም በጀርመንኛው አርትስ ፊዩር ኢትዮፕየን የተሰኘውና በደቡብ ኢትዮጵያ ይርጋለም ሆስፒታልን በመርዳት ላይ የሚገኘው ማኅበርም እንዲሁ ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች በሀገር ውስጥ ኮቪድ 19 ተሐዋሲን ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ እየተንቀሳቀሰ ነው። የማኅበሩ መሥራች የሆኑት ወይዘሮ ትዕግሥት ላቀው የሚደረገውን እንዲህ ገልጸውልናል።
ከቁሳቁሱ ርዳታ በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች ኮቪድ 19ን በተመለከተ በኢንተርኔት መስመር ከጀርመን የሙያ አቻዎቻቸው ልምድ የሚለዋወጡበትን መድረክ የማመቻቸት ሃሳብም አላቸው ወይዘሮ ትዕግሥት።
ኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮና ተሐዋሲ የመገኘቱ ዜና ከመነገሩ አስቀድሞ ጥንቃቄ እንዲደረግ ብዙዎች ሲያሳስቡ ነበር። በተለይም ከወራት በፊት በዚህ በሽታ በርካታ ዜጎቿን በሞት የተነጠቀችው የጣሊያን ገጠመኝ ስጋት ያሳደረባቸው ወገኖችም ጥቂት አልነበሩም። በሌሎች ሃገራት የኮቪድ 19 ታማሚዎች ቁጥር ተበራክቶ የተገኘው የመርመር አቅማቸው በመጠናከሩ ነው ብለው የሚያስቡ ወገኖችም ኢትዮጵያ ውስጥ የመመርመሪያ መሣሪያው እንዲበራከት መመኘታቸው አልቀረም። በጀርመኗ የንግድ ማዕከል ፍራንክፈርት ከተማ የሚገኘው የሀመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከ26 ሺህ ዩሮ በላይ ያወጣ ዘመናዊ ኮቪድ 19ኝን ብቻ ሳይሆን ለኤች አይቪ፣ እንዲሁም ሌሎች ተሐዋስያንን መመርመር የሚያስችል መሣሪያ ገዝቶ በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካኝነት ወደ ሀገር ቤት እንዲላክ ማስረከቡን የቤተ ክርስቲያኒቱ ገንዘብ ያዥ የሆኑት አቶ ጥበቡ ኃይሉ ነግረውናል።
ይህን የመመርመሪያ መሣሪያ ይበልጥ ውጤታማ አድርጎ ለመጠቀም አስፈላጊ ግብአቶችን ማግኘት የሚቻልባቸው መንገዶችን ርክክቡ በተከናወነበት ወቅት መጠቆማቸውንም አቶ ጥበቡ ገልጸዋል። አቶ ዓለሙ ታደሰ በበኩላቸው በጀርመንም ሆነ በተለያዩ ሃገራት የሚገኙት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያ በየበኩላቸው ሀገር ቤት የሚገኘው ወገን በኮቪድ 19 ተሐዋሲ እንዳይጎዳ የየበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ቅስቀሳ ያስፈልጋል ይላሉ።
ሸዋዬ ለገሠ