ለኮሮና መፍትሄ እንዲገኝ ጀርመን በፀጥታዉ ም/ቤት ግፊት ልታደርግ ነዉ
ሰኞ፣ ሰኔ 22 2012ማስታወቂያ
ዓለም እየተጋፈጠ ያለዉን የኮሮና ወረርሽኝን በተመለከተ በመንግሥታቱ የየፀጥታ ምክር ቤት መፍትሄ እንዲገኝ ለማድረግ ጀርመን ዳግም ግፊት እንደምታደርግ ተገለፀ። የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ እንደተናገሩት የዓለሙ የፀጥታ ምክር ቤት የኮሮና ተኅዋሲን በተመለከተ እስከዛሬ በቅርበት ያለመስራቱ እና የጋራ ዉሳኔ ላይ አለመድረሱ በጣም አሳፋሪ ነዉ ብለዋል። ከፊታችን ረቡዕ ሰኔ 24 ጀምሮ ጀርመን ለአንድ ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ምክር ቤት ሊቀመንበርነትን የምትረከበዉ ጀርመን በዚህ የስልጣን ጊዜያዋ የፀጥታ ምክር ቤቱ ለኮሮና ተኅዋሲ መፍትሄ እንዲያገኝ ጥረት እንደምታደርግ ገልፃለች። የዓለሙ የፀጥታ ምክር ቤት ኮሮና ተኅዋሲ እንዲሁም የዓለም የጤና ድርጅት ያለዉን አስተዋፅኦ በተመለከተ በዩናይትድ ስቴትስ እና በቻይና መካከል ከፍተኛ ዉዝግብ በመቀስቀሱ እስካሁን አንዳች መፍትሄ ላይ አለመድረሱ ተመልክቶአል።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ