ህወሓት ለምርጫ ቦርድ ውሳኔ የሰጠው መልስና የፓርቲው መታገድ በፖለቲካ ተንታኝ እይታ
ሐሙስ፣ ግንቦት 7 2017ህወሓት በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የተላለፈውን ውሳኔ የፕሪቶርያውን ስምምነት የሚጥስ ሲል ኮንኗል። ህወሓት ዛሬ ባሰራጨው ደብዳቤ የውሉ አፈራራሚዎች ሁኔታውን የሚመለከት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠሩ ጥሪ አቅርቧል። ህወሓት ለአፍሪካ ሕብረት የተለያዩ ተቋማት እና የስምምነቱ አፈፃፀም ተከታዮች በፃፈው ደብዳቤ ህወሓት እና የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሠረት እውቅና ተሰጣጥተዋል ሆኖም የፌደራሉ መንግስት ይህ እየጣሰ ነው ሲል ከሷል።
በህወሓት እና የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ውዝግብ ዙርያ እንዲሁ ተያያዥ ጉዳዮች ሀሳባቸው ያጋሩን የሕግ ምሁሩ እና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙስጠፋ ዓብዱ፥ ከሶስት ወራት በፊት በምርጫ ቦርድ ከተላለፈው ውሳኔ በኃላ ትላንቱ ያወጣው ህወሓትን እንደተሰረዘ የሚያመለክት መግለጫ ሲጠበቅ የነበረ ነው ብለውታል። ከሁለት ዓመት ጦርነት በኃላ የሰላም ስምምነት የተፈራረሙ ህወሓት እና የኢትዮጵያ ፈደራል መንግስት ውሉን በሚገባ ፈፅመው ወደ ሕገመንግስታዊ ስርዓት መመለስ ሲገባቸው እስካሁን ይህ አለመሆኑ የተለያዩ ውዝግቦች መነሻ እየሆነ መሆኑም አቶ ሙስጠፋ ዓብዱ ያነሳሉ።
ህወሓት ከምርጫ ቦርድ እና የፌደራሉ መንግስቱ ጋር ያለው ልዩነት የሌላ ግጭት መነሻ እንዳይሆን የበርከቶች ስጋት የሆነው ህወሓት የሰላም ስምምነቱ ፈራሚ መሆኑ ተከትሎ ነው የሚሉት ተንታኙ፥ የህወሓት በርካታ ስህተቶች እና የፌደራል መንግስት ከፕሪቶርያ ስምምነት ያፈነገጡ ፍላጎቶች ግንኙነቱ አሁን ላይ ወዳለው ሁኔታ መምራቱ ይገልፃሉ። ከዚህ በተጨማሪ የምርጫ ቦርድ ውሳኔየህወሓት እና የፌደራል መንግስትልዩነት እየሰፋ በመጣበት በዚህ ግዜ መምጣቱ በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ ብለውታል።
አሁን ላይ በህወሓት እና ፌደራል መንግስት መካከል ያሉ ልዩነቶች ወደግጭት እንዳይሸጋገሩ እንዲሁም ቀጠናው ወደከፋ ሁኔታ እንዳይመራ በዋነኝነት የፕሪቶርያ ውል ያፈራረሙ አካላት፥ በአጠቃላይ ደግሞ ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ